ETHIO12.COM

ለአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 6.7 ቢሊየን ችግኝ መዘጋጀቱ ተገለፀ

ለ2014 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 6.7 ቢሊየን ችግኝ መዘጋጀቱን የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ አሰታወቁ።

በ2013 ዓ.ም 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከለ ታቅዶ 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን መትከል ተችሏል፤ ባለፉት አመታት በተደረገ የችግኝ እንክብካቤ አማካኝ ውጤት 80 ነጥብ5 በመቶ የጽድቀት ደረጃ ሆኖ ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

ለዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን የደን፣ 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ የጥምር ደን ችግኝ፣ 518 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኝ፣ 35 ሚሊዮን የቀርከሃና 800 ሚሊዮን ለእንስሳት መኖ ጥቅም የሚሰጡ ቁጥቋጦዎችና ለከተማ ውበት የሚሆኑ ችግኝ በአጠቃላይ 6 ነጥብ 7 ቢሊየን ችግኝ መዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮዽያን እናልብሳት በሚል የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አላማው የተስተካከለ ስርዓተምህዳርና ስነምህዳር እንዲኖር በማድረግ የአርሶና አርብቶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ታሳቢ ያደረገ ነው።

በመሆኑም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ባለፉት 3 አመታት በእቅድ ተይዞ ሲሰራ በነበረው ስራ በ2011 ዓ.ም 4 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከለ ታቅዶ 4.7 ቢሊዮን ችግኝ መትከል የተቻለ ሲሆን በ2012 ዓ.ም 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ተችሏል፡፡

ከምግብ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ሰፋፊ ዘመቻዎች የተደረጉ ሲሆን ቡና ወደ ውጪ ልኮ ጣውላ ማስገባትን ታሪክ ማድረግ የአረንጓዴ አሻራ አንዱ እሳቤ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የሙቀት አማቂ ጋዞችን ከመቀነስ እና ከመቆጣጠር አንጻር ከሚሰሩ ስራዎች ባሻገር ገቢ ለማስገኘት በስራ እድል ፈጠራ ላይ ወጣቶች ተደራጅተው ችግኝ በማፍላት ለተለያዩ ተቋማት በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

ከበልግ ተከላ ጋር ተያይዞ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በሚሰራበት አካባቢ ሰፋፊ የችግኝ ጣቢያዎች በማቋቋም ለአካባቢው ተስማሚ ዝርያዎችን በመምረጥ ተከላ እንዲካሄድ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ተፋሰሶች ባለቤት ተፈጥሮላቸው ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

እስካሁን ባለው መረጃ ከ3 ቢሊዮን በላይ ጉድጓድ ለተከላ ተዘጋጀ ሲሆን የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ከክልል እስከ ወረዳ ካሉ የቴክኒክ ኮሚቴዎች ጋር በቅንጂት በመስራት ድጋፍ የማድረግና መረጃ የመለዋወጥ ስራ እየተሰራ መሆኑ መግለጻቸውን ከግብር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

OBN

Exit mobile version