ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ሰደድ – የኢትዮጵያ ሰበር ዜና “ችግኝ”

ኢትዮጵያ አረንጓዴ ሰደድ እየተፋፋመባት ነው። ኢትዮጵያ አረንጓዴ እንድትሆን ዜጎቿ ከዳር እስከዳር 500 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ወገባቸው አስረው እየደከሙ ነው። ልጅ፣ አዋቂ፣ ሴት፣ወንድ ሳይለይ ለኢትዮጵያ ችግኝ እያበረከቱላት ነው። ይህ የአረንጓዴ አብዮት ለኢትዮጵያ ” ሰበር ዜናዋ” ይህ በሆነ ነበር የሚሉ አሳቢ ዜጋዎች ድምጽ ይሰማል።

በየትኛውም ዜና ስር የሚርመጠመጡ ደግሞ “ኢትዮጵያ 500 ሚሊዮን ችግኝ ትተክላለች” በሚለው ዜና ስር ስድብና እርግማን ይለጥፋሉ። ችግኝ መትከልን ይረግማሉ። እንደ አቅሚቲ ይቀሰቅሳሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ 120 ሚሊዮን መሆኑንን ዘንግተው በድል ስሜት ይናኛሉ። አገር ስትወረር “ወታደርነት አትቀጠሩ” ሲሉ እንደነበሩት ሟርተኞች ማፈራቸው ላይቀር ዛሬም ይህንኑ ክፉ ምኞታቸውን ያንጸባርቃሉ።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቅጥ አምባሩ የጠፋ፣ ለመረዳት ሲሞክሩት አጥወልውሎ የሚጥል፣ የዛሬዋን የወንበር ቅዠት ብቻ የሚያይ፣ ሆድ አምላኩ፣ ነገን አስቦ የማያቅድ፣ የዓለምንም ሆነ የጎረቤት አገራትን ወቅታዊ ሁኔታ የማያገናዝብ … የጨቀየ ነው። የዚህ የጨቀየ ፖለቲካ አጨማላቂዎች እንኳን አማራጭ ሊሆኑ እዚህ ግቡ የማይባሉ በመሆናቸው ህዝብ ተራ ለቅሶና ሙሾ ከማድመጥ በቀር ከችግር ሊያወጣው የሚችል ተስፈኛ መሪ ሊታየው አልቻለም። ኢትዮጵያ ያሏት ምርጥ ልጆቿ ዝም ማለታቸው አጨማላቂዎች በተቃዋሚም ሆነ በመንግስትነት እንዲፈነጩ አድርጓል።

ችግኝ የሚተከልበትን ቀን ጠብቀው በዜማ ሊያጠለሹት ከሚመኙት ተስፈኞችና ከአቅማቸው በላይ የሚያስቡ ሱሰኞች፣ በኢትዮጵያ ባንዲራ አሸብርቀው ማታ ማታ ስድብ የሚረጩ ጨለምተኞች፣ ሁሉንም ጉዳይ በዘር የሚለውሱ ክፉዎች ዓየሩን ባይቆጣጠሩት ኖሮ ችግኝ ተከላና የስንዴ አብዮት ለኢትዮጵያ የምስጋናና የወደፊት ተስፋዋ መነጋገሪያቸው በሆነ ነበር።

“የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዳይ ኢትዮጵያን የመጠበቅ፣ የማክበርና የማበልጸግ፣ ታሪክ የመቀየር፣ ለትውልድ የማትረፍ ጉዳይ ነው” እንደተባለው የጎደለውን በመንቀስ፣ የተበላሸውን በማሳየት፣ የተሻለ አሳብ በማቅረብ፣ የተተከለው እንዲጸድቅና እንዲያድግ ህዝብ በያለበት እንዲንከባከብ ግንዛቤን ከማስፋት ይልቅ ስንዴ ለምን ተመረተ ብለው የሚያለቅሱ፣ ችግኝ ፖለቲካ ነው ብለው የሚራገቡ “ቡዳ” ሚዲያዎች ደጋግመው ለሚጠሯት አገር ምን እንደሚመኙላት መረዳት ያስቸግራል።

መንግስትን እስኪያስነጥሰው መተቸትና አበጥሮ ህዝብ ፊት ማንጠፍ የሚቻልባቸው እጅግ ብዙ ጉዳዮች እያሉ መከላከያ ዘመን፣ አየር ሃይል ተመነደገ፣ ባህር ሃይል በአዲስ መልኩ ተደራጀ፣ ለህጻናት የመዝናኛና መጫወቻ ቦታዎች ተዘጋጁላቸው የሚሉና መሰል ደግ ዜናዎችን ማራከስ ” ወዴት ወዴት እየሄድን ነው” ያሰኛል። እውነትም ወዴት እየሄድን ነው? “የህዳሴ ግድብ ተሸጠ” ሲሉ የነበሩ ተቀላቢ ሚዲያዎች ዛሬም ሃሰት ሲረጩ ከልካይ የላቸውም። እነሱም አይፍሩም።

See also  የኢትዮጵያ መንግስት በሁለት መጠለያ ጣቢያዎች ላሉ ኤርትራውያን ስደተኞች “የከተማ ስደተኝነት” እውቅና ሊሰጥ ነው

ትናንት በየባለስልጣኑ ቢሮ ምቹ ወንበር ላይ ሆነው ከካድሬ በላይ ሲሰብኩ የነበሩ ምን ጎድሎባቸው እንዳኮረፉ ባይታወቅም ዛሬ መርዶ አውራጅ፣ ለቅሶ ደርዳሪ፣ መረገምት ሰፋሪ ሆነዋል። እንደነሱ አሳብ ኢትዮጵያ ፈርሳለች። ተበትናለች። ዳሩ ግን በከርሳቸው የምትለካው ኢትዮጵያ እንደሚያስቧት እሳት ሳይሆን፣ አረንጓዴ ሰደድ እያዳረሳት ነው።

ላለፉት አራት ዓመታት በመጀመሪያው የአረንጓዴ ሌጋሲ 25 ቢሊዮን ችግኝ ተተክሏል። በቀጣዮ ምዕራፍ ሌላ 25 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዛሬ የ500 ሚሊዮኑ ተከላ በመላው አገሪቱ ተጀምሯል። ይህ ከሰበርም በላር ሰበር ነው። ታሪኳ ሙሉ ረሃብ ለሆነ አገር፣ ጠኔና ችጋር መለያችን በመሆኑ የደረሰብንንና የሚደርስብን ችግር ለሚረዳ ይህ ዜና ትልቅ ነው።

ረሃብ ስለጠናብን፣ በረሃብ አሳበው እንዳሻቸው የሚንጡንን አካላት ሴራና ተንኮል ለሚያውቁ ዜጎች የስንዴና የአረንጓዴ አብዮት ዛሬም ነገም ወደፊትም ዜናቸው ነው። ሰበራቸው ነው። ችግኝ ተከላን ማራከስ ማንም ይሆን ማን አይቻለውም። ቢሞክርም አይሆንም። ወታደር እንዳይመለመል ሲቀሰቅሱ የነበሩ አፍረዋል። ዛሬም በችግኝ ተከላው ያፍራሉ።

በወጉ ሌሎች ዓለማት እንዳሉ ተቀናቃኞችና ህየተቀናቃኞች ሚዲያ ሰልጠን ማለት ያስፈልጋል። መልካሙን የሚያደንቅ የተበላሸውን ሲተች ይሰማልና። እንደ ኮማሪ እየተቆናጁ ማታ ማታ ስድብና ጨላማን ህዝብ ላይ የሚጠሩ ወደ ልባቸው ቢመለሱ ይበጃል። ” አበሌን አትርሱ፣ በሱፐር ቻት ጣል ጣል አድርጉባት” የሚሉ ዲጂታል ለማኞች የጀመሩት የችግኝ አትከሉ ፖለቲካ ዛሬ ህዝብ ከዳር እስከዳር ወጥቶ እንዳከሸፈው ማታ ሪፖርት ሲቀርብ መጠበቅ አያስፈልግም።

አገር ውስጥም ሆነ ውጭ ያሉ ሚዲያዎች ሌባ ባለስልጣናትን፣ ተቧድነው ኮንትሮባንድ ላይ የተሰማሩትን፣ ወዳጅ መስለው የኢትዮጵያን ዶላር የሚያጥቡትን፣ አፈናና ግድያ የሚፈጽሙትን ወዘተ ላይ መረባቸውን በመጣልና በማሰስ ማጋለጥ ላይ ከማተኮርና ለትውልድ ከመስራት ይልቅ ቁጭ ብለው የከፋቸውን፣ ያኮረፉትን፣ ምርጫ ለመወዳደር ሞክረው አንድ ድምጽ ለዚያውን የሚስታቸውን ብቻ ያገኙ አላዛኞችን ቃለ ምልልስ በማድረግ እስከመቼ ተመራጭ የስራ መስክ ይሆናል? የብልጽግናን መንግስት በበርካታ ጉዳዮች ወጥሮ መያዝ እየተቻለ እስከመቼ በዚህ መልኩ ተራ ስድብ እያዝጎደጎዱ ይቀጠላል? ….

Leave a Reply