Site icon ETHIO12.COM

መርዛማ ኬሚካል የያዘ በርበሬ የሸጡ ተቀጡ።

በሲዳማ ክልል በሀዋሳ ከተማ መርዛማ ኬሚካል የያዘ በርበሬ የሸጡ ተከሳሾች በገንዘብና በእስራት ተቀጡ።

ግርማ ሀንዳላ እና ገዛኸኝ አሰፋ በተባሉ ተከሳሾች የምግብና የመድሃንት አስተዳደር አዋጅ 1112/11 በመተላለፍ ግንቦት 10/2013 በተደረገ የወፍጮ ቤት ዳሰሳ ስራ ሊፈጭ በተዘጋጀ በርበሬ ውስጥ ባዕድ ነገር ቀላቅለው ለህብረተሰቡ እንዳከፋፈሉ በመጥቀስ ለሐየቅ ዳር ክፍለ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ ያቀረቡ ሲሆን በኢትዮጵያ ምግብ መድሃኒት እና ጤና እንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ከበርበሬው በተወሰደ ናሙና በተደረገ ምርመራ በውስጡ በሻጋታ ምክንያት የሚፈጠር መርዛማ እና በሰው ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርስ አፍላቶክሲን የተባለ ኬሚካል በከፍተኛ መጠን መገኘቱ የተረጋገጠ በመሆኑ ተከሳሾች በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ የተወሰነ ቢሆንም ተከሳሾች ይግባኘ በማለታቸው የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ የሻረ ውሳኔ ሰጥቷል። ሆኖም በውሳኔው ቅር የተሰኘው የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ ተከሳሾች ለፈጸሙት ወንጀል ተመጣጣኝ አይደለም በማለት ለሲዳማ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቀዋል።

የሲዳማ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሲዳማ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ያቀረበውን ይግባኝ መርምሮ ሰኔ 03/2014 ዓ.ም በዋለው የወንጀል ችሎት የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔን በመሻር ተከሳሾችን የስተምራል እንዲሁም ሌሎችን ያስጠነቅቃል ያለዉን አንደኛ ተከሳሽ ግርማ ሀንዳላን በአምስት አመት ጽኑ እስራትና በ166,666 ብር እንድሁም ሁለተኛ ተከሳሽ ገዛኸኝ አሰፋን በአምስት አመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራትና በ166,666 ብር እንዲቀጡ በማለት የሀይቅ ዳር ክፍለ ከተማ ፍርድ ቤት ውሳኔን አጽንቷል።

ዜናውን ያደረሰን የሲዳማ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ነው

Exit mobile version