Site icon ETHIO12.COM

መንግስ በግፍ ለተጨፈጨፉ ስርዓት ሊያከናውን ነው፤ አማራና ኦሮሚያ ክልል ህብረት መፍጠራቸውን አስታወቁ

ምስራቅ ወለጋ

መንግስት በማንነታቸው በግፍ ለተጨፈጨፉ ወገኖች አስፈላጊዎች የሃዘን አዋጅ አላውጀም በሚል ቅሬታ ስለሚሰማ ሳይሆን፣ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ በክብር ዜጎቹን ለማሰብና በተጓዳኝ የተወሰዱ እርምጃዎችን ለሕዝብ በግልጽ ለማሳየት በዝግጅት ላይ መሆኑ ተሰማ። የአማራና ኦሮሞ ክልል መሪዎች ሁለቱ ታላላቅ ሕዝቦች በተደገሰላቸው ወጥመድ ውስጥ ሳይገቡ በጋራ ክንዳቸውን በሸኔ ላይ በማንሳት እየሰሩ መሆናቸውን አመለከቱ።

ስማቸውን ያልገለጹ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳሉት መንግስት በፖለቲካ አመራሮች፣ በአካባቢው መዋቅርና ጭፍጨፋውን በፈጸሙት የኦነግ ሸኔ ታታቂዎች ላይ እርምጃ ወስዷል። እየወሰደም ነው። በተጓዳኝ በቁጥጥር ስር ባዋላቸው አካላት ላይ እያካሄደ ባለው ምርመራ አቅጣጫ ሰጪነት ሰፊ የክትትልና የአደን ስራ በመስራት ውጤት አግኝቷል።

በግፍ የተጨፈጨፉ ዜጎች ጉዳይ ሕዝብን በጅጉ ያበሳጨና ያሳዘነ መሆኑን፣ ሕዝብ ሃዘን እንዲታወጅና ብሄራዊ አመክሮ እንዲደረግ መጠየቁ አግባብነት እንዳለው ያመለከቱት ሃላፊው ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች በቅርቡ መረጃ እንደሚሰጡ አመልክተዋል። በተያያዘ ዜና “አሸባሪዎችን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት በጋራ አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።

የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ውይይት ባደረጉበት ወቅት የአሸባሪዎች ፍላጎት እና ጥፋት የሁለቱን ሕዝቦች አንድነት አይሸረሽረውም ብለዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ የተጨፈጨፉት ንጹኀን ወገኖች በመጀመሪያ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ ናቸው፤ ይህን ደግሞ በጋራ አውግዘናል ነው ያሉት።

ሸኔ የአማራ ብቻ ጠላት አለመሆኑንና የጋራ የኢትዮጵያውያን ጠላት እንደሆነም ገልጸዋል። ሸኔን ከማጥፋት ውጭ አማራጭ እንደሌለ ተወያይተናል፤ አቅጣጫም አስቀምጠናል ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ።

አሸባሪው ሕወሃት ጦርነት እየጎሰመ ነው ያሉት ዶክተር ይልቃል ይህንንም መመከት የምንችለው በጋራ ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከዚህ በፊት የሁለቱ ሕዝቦች አብሮነት እየተገመደ እንጅ እየላላ አልሄደም፤ አሸባሪው ህወሓት ሲነሳ አንድነታችን ጠንክሮ በአንድ ጉድጓድ እንደተቀበርን አሸባሪው ሸኔ ሲነሳም አንድነታችን የበለጠ እንዲጠናከር አድርጎታል ብለዋል።

ሸኔ ጊምቢ ላይ ጥቃት የፈፀመው ሦስት ዓላማዎችን ይዞ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ አንደኛ የአማራና የኦሮሞ ሕዝብን ለመለያየት ሲሆን ይህ ትላንት ሕወሓትም አስቦ ያልተሳካለት ሸኔም ዛሬ የማይሳካለት በእኛ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የማይሆን ነው ብለዋል።

ሁለተኛው ፍርሐትን በሀገሪቱ ማንገስ ሲኾን ሦስተኛው ደግሞ ማሸበር ነው ብለዋል። ይህ እንዳይሳካ በጋራ ርምጃ እየወሰድን ነው ብለዋል።

ሁለቱ ሕዝቦች ትላንትም ዛሬም በጋራ መቆም እንደሚቻል ያሳዩ በመሆኑ ሸኔን መዋጋት አይከብዳቸውም ነው ያሉት።

ዛሬ አንድነታችንን የምናሳየው ጽንፈኝነትን በመዋጋት ነው ብለዋል። ለሕዝባችን ለዓላማችን ስንል ትላንት መስዋእትነት እንደከፈልነው ነገም መስዋእትነት ከፍለን ኢትዮጵያን የተሻለች ሀገር እናደርጋለን ነው ያሉት።

ሸኔን ሽፋንና መረማመጃ አድርገው በአመራሩ ላይ የሚዘምቱ አመራሩን ለመከፋፈል የሚጥሩ አይሳካላቸውም ብለዋል።

የሁለቱ ክልል የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች አቶ ግርማ የሽጥላ እና አቶ ፍቃዱ ተሰማ ትላንት ወያኔ እሳት እና ጭድ ናቸው ብሎ በአንድነታችን ቢሳለቅም በጋራ እንደጣልነው ሁሉ የመከፋፈል ዓላማ ያለውን ሸኔን በጋራ እናጠፋዋለን ብለዋል።

ዘጋቢ:–አንዷለም መናን

Exit mobile version