Site icon ETHIO12.COM

ዐቃቤ ሕግ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ክስ መሰረተ

የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ የልህቀት ህትመት ኮሙኒኬሽን ብሮድካስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ በሆነው ተመስገን ደሳለኝ ላይ ክስ መሰረተ

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዐቃቤ ሕግ የልህቀት ህትመት ኮሙኒኬሽን ብሮድካስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ በሆነው ተመስገን ደሳለኝ ላይ ክስ መስርቷል፡፡

ዐቃቤ ህግ ሰኔ 22 ቀን 2014 ዓ.ም በተከሳሹ ላይ ክስ የመሰረተው በሶስት የወንጀል ድርጊቶች ሲሆን ክሱን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት አቅርቧል፡፡

የዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው፡-
በ1ኛ ክስ ተከሳሹ የልህቀት ህትመት ኮሙኒኬሽን ብሮድካስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን በስራ አስኪያጅነት እየመራ ባለበት የኢፌደሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 44(1)(2) ስር የተመለከተውን የደራሲው፣ የአመንጪው ወይም የአሳታሚው የወንጀል ኃፊነት እንዲሁም በአንቀጽ 336(1) ስር የተመለከተውን ወታደራዊ ሚስጥሮችን ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ህዝብ መግለፅ ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል፡፡ ተከሳሹ በህዝብ ዘንድ ያልታወቁትንና ክፍተኛ ቁም ነገር በመያዛቸው እንዳይገለፁ በሚስጥር የሚጠበቁትን ወታደራዊ ሚስጥራት ለህዝብ ለመግለፅ በማሰብ ፍትህ በመባል በሚታወቅ መፅሄት በተለያዩ ጊዜያት “ሪፎርም ወይስ ፈረቃ” ፣ “ወታደራዊ አመፅ ያሰጋል”፣ “ክልል ወይስ ሃገር” ፣ “የጀነራሉ ሚስጥሮች” በሚል በተለያዩ ጊዜያት ባወጣቸው እትሞች በሀገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ እና የጦር አመራሮች መካከል የተደረገ ሚስጥራዊ ውይይት እና የሃገሪቱን የጦር ሃይል እና መሳሪያ አቅም ለህዝብ እና ላልተገቡ አካላት እንዲገለፅ በማድረጉ፤

በ2ኛ ክስ ተከሳሹ የኢፌደሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 44(1)(2) እና 337(1) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ወታደሮች ከስነ ስርዓት ውጪ እንዲሆኑ፣ እንዳይታዘዙ እና በህዝብ መካከል ሁከትና አለመረጋጋት እንዲነሳ በማሰብ በፍትህ መፅሄት “መከላከያ ሰራዊት እና የሹም ዘብ” ፣ “ሪፎርም ወይስ ፈረቃ”፣ “ወታደራዊ ጉዳዮች” ፣ “መከላከያ ተቋማዊ ወይስ ኔትዎርክ”፣ “የጀነራሉ ሚስጥሮች” በሚለው እና “የጀነራል ተፈራ መታፈን እና እድምታው” በሚሉ ርዕሶች በተለያዩ ጊዜያት በወጡ እትሞች ላይ ያወጣቸው ድርጊቶቹ እዉነት መሆናቸው በምርመራ ያልተረጋገጡ እና ከሃገር መከላከያ ሰራዊት ተገቢውን ጥረት በማድረግ ማጣራት ሲገባው ሳያጣራ በተከታታይ እትሞች ለህዝብ እንዲሰራጭ በማድረግ ህዝብ አባላቱ በተቋሙ ላይ ጥርጣሬ እንዲያሳድር በማድረጉ በፈፀመው የሀሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ ማሰራጨት ወንጀል፤ እንዲሁም፤

በ3ኛክስ ተከሳሹ የኢፌደሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 44 (1) (2) እና 257(ሠ) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የህዝቡን ሞራል ዝቅ ለማድረግ እና እምነቱን ወይም የመቋቋም ሃይሉን ለማፍረስ በማሰብ በፍትህ መፅሄት “ሪፎርም ወይስ ፈረቃ” በሚል ርዕስ ፣ “ወታደራዊ አመፅ ያሰጋል” ፣ “የጀነራሉ ሚስጥሮች” ፣ “መከላከያ ተቋማዊ ወይስ ኔትዎርክ” ፣ “በወታደራዊ ጉዳዮች” እና “መረጃ መመሪያ አለʔ” በሚል ርዕስ በተለያየ ጊዜ ባወጣቸው እትሞች ላይ በተቀናጀ ዘዴ ትክክለኛ ያልሆነ፣ ጥላቻ የተሞላበት ህዝብ ያለውን አቋም የሚያፈርስ መረጃ በተከታታይ እትሞች ለህዝብ እንዲሰራጭ በማድረጉ በፈፀመው መገፋፋት እና ግዙፍ ያልሆነ ማሰናዳት ተግባር መፈፀም ወንጀል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶበታል፡፡

ተከሳሹ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ከጠበቃው ጋር ቀርቦ ክሱ ከተነበበለት በኋላ የክሱን ማመልከቻ የሚቃወም ስለመሆኑ በፍርድ ቤት ተጠይቆ መቃወሚያውን በፅሁፍ እንደሚያቀርብ ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል የተከሳሽ ጠበቃ የተከሳሽ የዋስትና መብት ተከብሮ ጉዳዩን ከውጪ ሆኖ እንዲከታተል ፍ/ቤቱን የጠየቀ ሲሆን ዐቃቤ ህግም የዋስትና መብቱን በምክንያት አስደግፎ ተቃውሟል፡፡

በመጨረሻም ፍ/ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ በዋስትናው ጉዳይ የቀረቡ አስተያየቶችን መርምሮ ብይን ለመስጠት እና የተከሳሽን የክስ መቃወሚያ ለመጠባበቅ ለሰኔ 24/2014 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Attorney general

Exit mobile version