Site icon ETHIO12.COM

ህይወት በማጥፋት ወደ ኬኒያ ሸሽተው የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የአንድ ቻይናዊ ዜጋን ህይወት በማጥፋት ወደ ኬኒያ ሸሽተው የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ቦታው መስቀል ፍላወር ቶሎሳ ለገሰ ሆቴል 5ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው የቻይና ሬስቶራንት ውስጥ ቻይናዊውን ሚስተር ፉ(Fu) ሁይ (Hui) የተባለውን ግለሰብ ህይወት በማጥፋት ወንጀል ሲፈለጉ የነበሩት አራት ቻይናዊያን በኬንያ በቁጥጥር ስር ውለው ለኢትዮጵያው ፌደራል ፖሊስ ብሔራዊ ኢንተርፖል በዛሬው ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡

ሁዋምግ ዝሂፔንግ፣ ሊቭ ጂ፣ ዋምግ ሚንግ እና ቻዎ ፉ ዚኡዛኦንግ የተባሉት ተጠርጣሪዎች ወንጀሉን ከፈፀሙ በኋላ ወደ ኬንያ አምልጠው ነበር።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኢንተርፖል ዳይሬክተር ኮማንደር ፀጋዬ ሀይሌ እንደገለጹት፤ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ምርመራውን በፍጥነት በማካሄድ ተጠርጣሪዎቹ ላይ ዓለም አቀፍ የኢንተርፖል ቀይ ማስታወቂያ (Red Notice) አውጥቶባቸው ሲፈለጉ ነበርም፡፡

ሃያ አራት ሰዓት በተደረገ የመረጃ ልውውጥ ኬንያ መግባታቸውን መረጃ ያገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኢንተርፖል ከኬንያ ብሔራዊ ኢንተርፖል ጋር በጥምረት በመስራት ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ብለዋል፡፡

አራቱም ቻይናውያን ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው ወደ ተጠረጠሩበት ኢትዮጵያ ገብተው ምርመራ እንዲጣራባቸው ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተላልፈው ተሰጥተዋል ያሉት ኮማንደር ፀጋዬ፤ ማንኛውም ሰው ወንጀል ፈፅሞ ከህግ ማምለጥም ሆነ የትም ሀገር መደበቅ እንደማይችል በዓለም አቀፉ የፖሊስ ህብረት ኢንተርፖል ተፈልጎ ህግ ፊት የሚቀርብ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ማለታቸውን የፌዴራል ፓሊስ አስታውቋል። (ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version