Site icon ETHIO12.COM

መንግስት የነዳጅ ድጎማ የማይደረግላቸውን በአንድ ዓመት ውስጥ ከድጎማ ሥርዓት ሊያስወጣ ነው

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በአዲሱ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ሥርአት ተጠቃሚ የማይሆኑ ተቋማትና ተሽከርካሪዎች በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ማለትም በየ3 ወራት የነዳጅ ዋጋ እየተሻሻለ ሲመጣ ቀስ በቀስ ከድጎማ ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ እንዲወጡ እንደሚደረግ አስታወቀ፡፡

ለሚቀጥሉት 3 ወራት መንግስት በድጎማው ውስጥ ያልተካቱት ተሽከርካሪዎች ከሚገዙት ነዳጅ ውስጥ ከ25 እስከ 75 በመቶ ዋጋ እንደሚደጉም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገ/መስቀል ጫላ ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

ከሐምሌ ወር ጀምሮእንደሚስተካከል በታመነበት ዋጋም በመጀምሪያው ወር 25 በመቶ ተጠቃሚው ማለትም በድጎማ ውስጥ ያልተካተቱት እንዲከፍሉ እንደሚደረግና 75 በመቶው በመንግስት እንደሚደጎም ተነግሯል፡፡

ድጎማ ውስጥ የማይካቱት የቤት ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ የግል ድርጅቶች፣ ኢምባሲዎችና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ወደ 1 ሚሊዮንና ከዚያ ላይ የሚደርሱ ተሽከርካሪዎች ያሉ ሲሆን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከድጎማ ሥርዓት እንዲወጡ ይደረጋል ሲሉ አቶ ገ/መስቀል ተናግረዋል።

በሁለተኛው ወር ደግሞ መንግስትና የማይደጎሙ ተሽከርካሪ ተጠቃሚዎች 50፣ 50 በመቶ ዋጋውን በመጋራት ይደጉማሉ፡፡ በሶስተኛው ወር ላይ የማይደጎሙት 75 በመቶውን ወጪ በመክፍል ሲደጉሙ መንግስት 25 በመቶ ይደጉማል፡፡
በአራት ወራት ውስጥም ዋጋውን ሙሉ ለሙሉ የማይደጎሙት ወገኖች ከመንግሥት የሚያገኙት የነዳጅ ድጎማ ሙሉ ለሙሉ ተነስቶ ዋጋውን ራሳቸው እንደሚሸፍኑና ይሄም አሰራር ቀጥሎ በአምት ውስጥ ሁሉንም ከድጎማ ለማስወጣት ዕቅድ ተይዟል፡፡
መንግስት በፖሊሲ ያልታገዘና መደጎም ያለበትንና የሌለበትን በማይለይ ሁኔታ ነዳጅን በአንድ ዋጋ ሁሉም ሲገዛ እንደቆየ አቶ ገብረመስቀል አብራርተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ባለሃብቶችንና የውጭ ድርጅቶችን እንደማሳያነት ገልፀው፣ እነዚህ ግለሰቦችና ተቋማት ነዳጅን በዓለም አቀፍ ዋጋ መግዛት እንደሚችሉና ይሁን እንጂ መደጎም ካለባቸው ጋር ሲደጎሙ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡
መንግስት የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ቢያዘጋጅምና የነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ በሚፈጠርበት ጊዜ የነበረውን ከፍተኛ ዋጋ በመደጎሙ ምክንያት የ146 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እዳ በመንግስት ሲሸፈን መቆየቱንም አንስተዋል፡፡

ይህንን ለማስተካከል በሚል ሁለት ውሳኔዎች ታህሳስ 20/2014 ዓ.ም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነዳጅ ዋጋ ማስተካካያና የትርፍ ህዳግ አፈፃፀም እና የታለመ የድጎማ የአፈጻፀም መመሪያ ውሳኔን ማስተላለፉን አቶ ገ/መስቀል አስታውሰዋል፡፡

👉በሐምሌ 2014 በሚጀመረው የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚነትም ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች በቀን 7 ሊትር ነዳጅ፣
ታክሲ በቀን 25 ሊትር፣
ሚኒ ባስ በቀን 65 ሊትር፣
ሚድ ባስ በቀን 95 ሊትር
የከተማ አውቶቡስ በቀን 102 ሊትር፣
ፐብሊክ ሲቲ ባስ ወይም የፐብሊክ ሰርቪስ በቀን 25 ሊትርና እንዲሁም አገር አቋራጭ አውቶቡሶች በቀን 65 ሊትር በድጎማ ማግኘት እንደሚችሉ በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብዱልበር ሸምሱ አስታውቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም የሚደጎሙት ተሸካርካሪዎች በአምስት አመታት ከድጎማ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ እንደሚወጡና በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት 10 በመቶ ከፍለው ቀሪው 90 በመቶ በመንግስት እንደሚደጎምላቸው፣ በሁለተኛው ስድስት ወራት 20 በመቶ ከፍለው ቀሪውን መንግሥት እንደሚከፍልና የድጎማውን ሙሉ ሽፋን በአምስት አመታት ውስጥ እንደሚጨርሱ አቶ ገ/መስቀል ተናግረዋል፡፡
በአምስት አመታት ውስጥም ከፍተኛ የሆነ የማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ለውጦች እንደሚኖሩና ገበያው ራሱን በራሱ ተቆጣጥሮ የሚሄድበት የማክሮ ኢኮኖሚ (ጥቅል ምጣኔ ሃብት) ትንበያ እንዳለም አንስተዋል፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሰዓረላ አብዱላሂ በበኩላቸው መንግስት በየቀኑ በአማካይ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ወደ ሃገር ውስጥ እያስገባ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
Via (ኢትዮ የንግድና ኢንቨስትመንት መድረክ) Dire tube

Exit mobile version