Site icon ETHIO12.COM

ሙስና – ሁለቱ የፌ.ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ብይን ተሰጠ

በሙስና ወንጀል የተከሰሱት ሁለቱ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ላይ የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ የመስማት ሂደት ተጠናቆ የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ብይን ተሰጠ፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በዐቃቤ ህግ የቀረቡ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ ሀምሌ 13/2014 ዓ.ም ብይን ሰጥቷል።
በዚህ የክስ መዝገብ ዐቃቤ ህግ በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ የመሰረተባቸው ተከሳሾች በቁጥር ሰባት ሲሆኑ 1ኛ ተከሳሽ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ አዱኛ ነጋሳ 2ኛ ተከሳሽ ዳኛ አክሊሉ ዘሪሁን : 3ኛ ተከሳሽ ረቂቅ ዜናዊ፣ 4ኛ ረቡማ በለጠ፣ 5ኛ ቶፊቅ ሙላት 6ኛ ተከሳሽ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ሬጂስትራር ስሜነህ አለሙ እና 7ኛ የቦሌ ክ/ከ ወረዳ 06 ኗሪዎች መረጃና ማስረጃ አገልግሎት ባለሙያ ከድር ጁንዲ ናቸው።

ይሁንና በመዝገቡ ከተጠቀሱት ተከሳሾች መካከል 3ኛ ተከሳሽ ከሃገር መውጣታቸው በመረጋገጡ እና 5ኛ ተከሳሽን ፖሊስ አፈላልጎ ሊያገኘው ባለቻሉ ክሳቸው ለግዜው የተቋረጠ ሲሆን የተቀሩ ተከሳሾችን በተመለከተ ማስረጃ ሲያደምጥ የቆየው ችሎት ብይን ሰጥቷል፡፡
በ1ኛ ክስ 1ኛ፣ 2ኛ እና 4ኛ ተከሳሾችን በተመለከተ ክሱ የቀረበው 1ኛ ተከሳሽ የ10 ሚሊየን ብር ቼክ እና 4መቶ ሺ ብር በጓደኛቸው የባንክ ሂሳብ በኩል እንዲላክላቸው አድርገው ያልተገባ ጥቅም ከ4ኛ ተከሳሽ በመቀበል አቶ ዳዊት ገብረእግዚያብሄር ቱሉ ጣፋ በሚል ሃሰተኛ ስም ለሚንቀሳቀሰው 5ኛ ተከሳሽ 276 ሚሊየን ብር ከዘጠኝ ፐርሰንት ወለድ እና 250 ሺ ብር የግልግል ዳኝነት ክፍያ ጋር እንዲከፍሉ የተወሰነባቸው መስሎ የተዘጋጀ ሃሰተኛ የግልግል ዳኝነት ውሳኔ ላይ በመመርኮዝ ገንዘቡ ቱሉ ጣፋ በሚል ስም ወደ ተከፈተ የባንክ ሂሳብ እንዲገባ የአፈጻጸም ትዕዛዝ በመስጠታቸው፤ 2ኛ ተከሳሽ 1ኛ ተከሳሽ ከላይ የተገለጸውን የአፈጻጸም ትዕዛዝ እንዲሰጡ በማግባባት ለራሳቸው የአምስት ሚሊየን ብር ቼክ እና አንድ መቶ ሺ ብር በጥሬ ገንዘብ በመቀበል ለ1ኛ ተከሳሽም የአስር ሚሊየኑን ቼክ ያቀባበሉ እና በባንክ ሂሳብ ገቢ የተደረገውንም 4 መቶ ሺ ብር እንዲላክ ያመቻቹ በመሆኑ፤ 4ኛ ተከሳሽ በአቶ ዳዊት ገብረእግዚያብሄር የባንክ ሂሳብ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ለመውሰድ በማሰብ ከላይ የተገለጸውን ሃሰተኛ የግልግል ዳኝነት ውሳኔ በማዘጋጀት፣ 5ኛ ተከሳሽን ቱሉ ጣፋ ሆኖ እንዲቀርብ በመመልመል እና ሃሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያዎች እንዲዘጋጁለት እና የባንክ ሂሳብም እንዲከፈትለት በማድረግ፣ በሃሰተኛ የግልግል ዳኝነቱ አማካኝነት የአፈጻጸም መዝገብ እንዲከፈት በማድረግ እና ከላይ የተገለጸውን ለ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የተሰጡ ያልተገቡ ጥቅሞች በመስጠት ገንዘቡ በቱሉ ጣፋ ስም ወደ ተከፈተው የባንክ ሂሳብ እንዲገባ የአፈጻጸም ትዕዛዝ እንዲሰጥ በማድረጉ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 /2/ን በመተላለፍ በስልጣን አለአግባብ በመገልገል ወንጀል በፌደራል ፍትህ ሚኒስተር በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ክስ ተመስርቶባቸው ክርከር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ሐምሌ 13/2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ተሰምተው እና የሰነድ ማስረጃዎችም ተመርምረው 1ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች በተከሰሱበት ድንጋጌ ስር እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ ወንጀሉን የፈጸሙት በቀጥታ የዳኝነት ስልጣናቸው በጉዳዩ ላይ ውሳኔ በመስጠት ሂደት ተሳትፈው ባለመሆኑ እና ያገኙት ጥቅምም ከፍተኛ ሊባል የማይችል በመሆኑ በሚል የተከሰሱበትን ድንጋጌ በመለወጥ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 16 /1/ /ሐ/ ን በመተላለፍ በስልጣን ወይም በሃላፊነት በመነገድ ወንጀል እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ ተከሳሹ በ20000 ብር ዋስትና ከእስር ተለቀው በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከላሉ ትዕዛዝ ተሰጥተዋል፡፡

2ኛ ክስን በተመለከተ በ1ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን ተከሳሾቹ በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ምንጩ እንዳይታወቅ ለማድረግ በማሰብ በባንክ የገባውን 400000 ብር ያልተገባ ጥቅም በ1ኛ ተከሳሽ ጓደኛ የባንክ ሂሳብ እንዲገባ ያደረጉ በመሆኑ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 /1/ ለ/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ክስ የቀረበባቸው ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ ገንዘቡን በጓደኛቸው የባንክ ሂሳብ እንዲገባ ያደረጉት አስቀድሞ ከግለሰቡ የተበደሩት ገንዘብ ያለባቸው መሆኑ በማስረጃ በመረጋገጡ ድርጊቱ የተፈጸመው የገንዘቡን ምንጭ ለመደበቅ ነው ለማለት አይቻልም በሚል ተከሳሾቹ ከ2ኛው ክስ በነጻ እንዲሰናበቱ ብይን ተሰጥቷል፡፡

3ኛ ክስ የቀረበው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሬጂስትራር በሆነው 6ኛ ተከሳሽ ላይ በ1ኛ ክስ ላይ የተገለጸው የአፈጻጸም ፋይል እንዲከፈት ሲቀርብለት በህጉ መሰረት ከቀረበው የግልግል ዳኝነት ጋር ተከራካሪ ወገኖች ጉዳያቸው በግልግል ዳኝነት እንዲታይ የተስማሙበት ስምምነት አብሮ ሳይቀርብ እና የቴምብር ቀረጥም ሳይከፈል መዝገቡ እንዲከፈት በማድርጉ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 /1/ /ሀ/ ላይ የተተደነገገውን በመተላለፍ በስልጣን አለአግባብ በመገልገል ወንጀል ሲሆን በግልግል ዳኝነት ለመዳኘት የሚደረግ ስምምነት ከአፈጻጸም ማመልከቻ ጋር እንዲቀርብ የሚያስገድደው አዋጅ በቅርቡ የወጣ በመሆኑ እና ወደ ኋላ ተመልሶ የማይሰራ በመሆኑ ይሄኛው መከራከሪያ ባለመቀበል የቴምብር ቀረጥ አለመከፈሉ ግን በመረጋገጡ ተከሳሹ የወንጀል ህጉን አንቀጽ 420 /2/ በመተላለፍ ወንጀል እንዲከላከል ብይን ተሰጥቷል፡፡

4ኛ ከስ 7ኛ ተከሳሽ የቦ/ክ/ከ/ወ/06 ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ባለሞያ ሆኖ ሲሰራ 20000 ብር የማይገባ ጥቅም ከ4ኛ ተከሳሽ በመቀበል ቱሉ ጣፋ የሚባል ግለሰብ በሌለበት ሁኔታ በአየር ላይ በኮምፒውተር ላይ ብቻ በመመዝገብ በቱሉ ጣፋ ስም ነዋሪነት መታወቂያ በመስጠቱ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 /1/ /ሀ/ ላይ የተተደነገገውን በመተላለፍ በስልጣን አለአግባብ በመገልገል ወንጀል የቀረበ ሲሆን ተከሳሹ በተከሰሰበት ድንጋጌ ስር እንዲከላከል ብይን ተሰጥቷል፡፡

ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃ አለን በማለታቸው መከላከያ ማስረጃ ለመስማት ለነሃሴ 4፣5፣6፣9 እና 10 2014 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በፍርድ ቤቱ ብይን እና ትዕዛዝ መሰረት በተፈቀደው ዋስትና እና በተለወጠው አንቀጽ ላይ ይገባኝ የሚጠይቅ ከሆነ በቀጣይ የምንገልጽ ይሆናል፡፡

Exit mobile version