Site icon ETHIO12.COM

የመቃወም አዚም!

defence and olympic team

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ፒኤችዲ) ያስተላለፉትን ጥሪ ተከትሎ፤ ሃይማኖት፣ ብሔር፣ ጾታ እና የፖለቲካ አመለካከት ሳይለይ እጅግ በጣም ብዙ ኢትዮጵያዊ የሚያመልከውን አምላክ በማመስገን ላይ ይገኛል።

ማመስገን በሁሉም እምነቶች አስተምህሮ ቀዳሚ ተግባር ከመሆኑም ባሻገር ከኢትዮጵያዊ እሴቶች መካከል አንዱ ነው።

አዕምሮው በትክክል የሚሰራ ሰው አይደለም ነብሱ በእጁ የምትገኝን አምላኩን ይቅርና መንገድ ጠፍቶት ያመላከተውን ሰው አለማመስገን ንፉግነት ነው።

በእርግጥ የተደረገለትን የሚገነዘብ ልቦና እና ለዚህም የሚያመሰግን አንደበት ከፈጣሪ ያልተሰጠው ሰው “ተመስገን” የምትለውን ቃል ከአንደበቱ ማውጣት ረጂም አቀበት የመውጣት ያህል ይከብደዋል።

ማመስገን የተሳናቸው ሰዎች በተቃራኒው “አማራሪ” ስለሚሆኑ ስራቸው ሁሉ ማማረርና መማረር ይሆናል።

ከተደረገላቸው ትልቅ ነገር ይልቅ የጎደለባቸውነገር ገዝፎ ስለሚታያቸው እንደዚህ ያሉ ሰዎች ለፈጠራቸው ፍጡራን ሁሉ በእኩል ደረጃ የሚያስበውን፣ የሚያዝነውን እና የሚራራውን አምላክ ሲያማርሩ ይስተዋላሉ፡፡

ከሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠራው የምስጋና መርሃ ግብርን መቃወም ግን ምን የሚሉት ክፉ መንፈስ ይሆን? ይህ የፖለቲካ ተቃርኖ ወይስ ሁሉን ነገር የመቃወምና የመተቸት አባዜ?

በርግጥ ኢትዮጵያ የበርካታ ዜጎቿን ህይወት በነጠቁ፣ የሚሊየኖችን ህይወት ባመሰቃቀሉ እና ንብረትን ባወደሙ ውስብስብ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች መሆኑ አይካድም።

ከኢትዮጵያ ፈተናዎቿ መካከል ደግሞ የውጭ ጠላቶቿ እና የውስጥ ባንዳዎቿ የሚደገሱላት ጥፋቶች ምንግዚም ቢሆን ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙ ሲሆን ድርቅ እና ወረርሽኝ ተጨምረው በእጅጉ ጎድተዋታል። ከፈተናዎቻችን በተቃራኒው ፈጣሪ ለዚህች ሀገርና ህዝብ ምን ያላደረገው ነገር አለ?

በሌላው የዓለም ክፍል የተከሰተው ኮቪድ 19 በሚሊየን የሚቆጠሩ የአሜሪካ፣ የህንድና ብራዚል ዜጎችን ህይወት ሲቀጥፍ እኛን ኢትዮጵያውያን እንደ ጉንፋን ያለፈን በፈጣሪ ምህረት እንጂ ሚጥሚጣ የምንበላ ህዝቦች ስለሆንን አይደለም።

ዛሬ ላይ በጦር መሳሪያ እና በኢኮኖሚ እድገታቸው ዓለምን እየዘወሩ የሚገኙት የኃያላን ሀገራት እስካሁን አይተው በማያውቁት ከፍተኛ ሙቀት እየነደዱ ሳለ እኛ ይኸው በፈጣሪ ምህረት በዝናብ ተንበሽብሸናል፡፡
ከዝናቡ በምናገኘው ውሃም፤ ወዲህ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንሞላለን ወዲያ ደግሞ አርሶ አደሩ ህዝባችን የተለመደ የክረምት ተግባሩን ያከናውንበታል።

ታዲያ ይህን ሁሎ ድሎት እና ጸጋን የዋለልን ፈጣሪ ያልተመሰገነ ማን ሊመሰገን ነው?

ማመስገን አለመቻል በሰውም ሆነ በፈጣሪ ዘንድ የተጠላ ተግባር ሆኖ ሳለ “እስኪ እናመስግን” የሚሉትን እና አመስጋኞችን መተቸት እና መወንጀል ደግሞ ክፉ መንፈስ ነው፡፡

የአቅመ ደካሞች ቤት ሲታደስ መተቸት፣ ለአቅመ ደካሞች የማዕድ ማጋራት መርኃግብር ሲደረግ አቃቂር ማውጣት፣ በትምህርት ቤቶች የምግባ አገልግሎት ተግባራዊ ሲሆን ማሽሟጠጥ ወዘተ ባለፉት ጊዜያት የተጠናወቱን አባዜዎቻችን ናቸው፡፡

እንጂማ ከላይ በተጠቀሱት መርኃግብሮች እጅግ በርካታ አቅመ ደካሞችና ጧሪ የሌላቸው ወገኖች ተጠቃሚ ሆነዋል።

ይህ ክፉ አባዜ ግን ከመቃወም ወይም ከመተቸት ሱስ ብቻ የመነጨ ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡

በውጫዊ እና ውስጣዊ ጠላቶቻችን የተደገሰልን የመንግስትን መልካም ተግባር ጥላሸት መቀባት የመንግስትን ተቀባይነት ይቀንሳል የሚል የፖለቲካ ቀመር አካል መሆኑን ለመረዳት ነብይ መሆንን አይጠይቅም፡፡

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስለ አስለቃሽ እና አጽናኝ ያነሱትን ሃሳብ እዚህ ላይ አስታውሰን ጽሁፉን ብንቋጭ ጥሩ ይሆናል፡፡

“አስለቃሽ ሁል ጊዜም ዋነኛ ስራው ማስለቀስ ነው፡፡ የሃዘንተኞችን ልብ ኮርኩሮ እና ሃዘናቸውን አባብሶ ማስለቀስ የሰርክ ተግባሩ ነው፡፡”

“ከአስለቃሹ በተቃራኒው ደግሞ አጽናኝ አለ፡፡ አጽናኙ ሃዘንተኛውን የሚያጠነክሩ እና ሃዘኑን የሚያስረሱ ቃላትን በመጠቀም ለማጽናናት ጥረት ያደርጋል፡፡”

በሀገራችንም እየተስተዋለ ያለው ነገር ተመሳሳይ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስለቃሹ ቁጥር ግን በጣም ብዙ እንደሆነ አስረድተው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ጠላቶች ምንም ይበሉ ምን እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን ትላንትን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያሳለፈንን እንዲሁም ነገን አሳምሮ የሚሰራልንን ፈጣሪያችንን እናመሰግናለን።

ተመስገን!

በነስረዲን ኑሩ – walata

Exit mobile version