Site icon ETHIO12.COM

333 የሸኔ የሽብር ቡድን አባላት መደምሰሳቸውና 671 መማረካቸው ታወቀ

በአልሸባብ የሽብር ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በተሳካ መልኩ እየተከናወነ ነው

ሐምሌ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአልሸባብ የሽብር ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በተሳካ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በምስራቅ በኩል የኢትዮጵያን ድንበር ሰርጎ በመግባት ጥፋት ሊፈፅም በነበረው የአልሸባብ የሽብር ቡድን ላይ የተሳካ ወታደራዊ ኦፕሬሽን መካሄዱን ተናግረዋል።

ኦፕሬሽኑ የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የሱማሌ ክልል ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻና በህብረተሰቡ ተሳትፎ መካሄዱን ገልጸዋል።

በዚህም በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት መማረካቸውንና መደምሰሳቸውን ተናግረዋል።

ኦፕሬሽኑ በአጠቃላይ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለው የወታደራዊ ዲፕሎማሲም ትልቅ ውጤት ያመጣ መሆኑን በአልሸባብ ላይ የተገኘው ውጤት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሁለቱ አገራት የጋራ ጠላታቸው የሆነውን የአልሸባብ የሽብር ቡድን ለማስወገድ በጋራ መስራታቸው ከምንጊዜውም በላይ የሁለቱን አገሮች ጠንካራ የትብብር መንፈስም በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አንስተዋል።

የጸጥታ ኃይሉ እስካሁን በወሰደው እርምጃ 24 የአልሸባብ አመራሮችን ጨምሮ ከ800 በላይ የሽብር ቡድኑ ተዋጊዎች መደምሰሳቸውን ጊዜያዊ የጸጥታ ኮማንድ ፖስት መግለጹ ይታወሳል።

በሌላ መልኩ ከሀምሌ 16 እስከ 22 ቀን 2014 ዓ.ም በጸጥታ ሃይሉ በተቀናጀ መልኩ በተወሰደው እርምጃ 333 የሸኔ የሽብር ቡድን አባላት ላይ እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ‘ሱሉላ ፊንጫ’ አካባቢ በተወሰደው እርምጃ የቡድኑ አባላት የተደመሰሱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም 671 የአሸባሪው አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረው፤ የሸኔ ሽብር ቡድን ይጠቀምባቸው የነበሩ በርካታ የጦር መሳሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የሽብር ቡድኑ ይጠቀምባቸው የነበሩ 69 የመሳሪያ ማከማቻ መጋዘኖች በፀጥታ ኃይሉ መውደማቸውን ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ እና በአዋሳኝ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የሽብር ተግባር እየፈፀመ ባለው የሸኔ የሽብር ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል። ENA

Exit mobile version