Site icon ETHIO12.COM

በቀጣይ አመት ስንዴን ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው -አቶ ሽመልስ

በቀጣዩ ዓመት ስንዴን ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ የሚያስችሉ ስራዎች በመኸር እርሻ እየተከናወኑ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ ።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦራና ዱግዳ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማውን የስንዴ ማሳ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደተናገሩት በክልሉ በአጠቃላይ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት እየተሰራ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ስንዴን ጨምሮ በተለያዩ ዋና ዋና ሰብሎች በኩታ ገጠም ለማልማት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በስንዴ ብቻ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ለማልማት ርብርብ እየተደረገ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በእስከ አሁኑ ሂደት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በስንዴ ብቻ ተሸፍኗል ብለዋል።

አሁን በዘር በመሸፈን ላይ ያሉትን የምስራቅ ባሌና ባሌ ዞኖች፣ የምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖችን ጨምሮ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከመኽር በተጨማሪ በቀጣዩ ዓመት በበጋ የስንዴ ልማት አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት የዘር ብዜት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አቶ ሽመልስ ተናግረዋል።

እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ሙሉ በሙሉ በማስቀረት የስንዴ ምርት ወደ ውጭ መላክ ያስችላሉ ብለዋል።

የኦሮሚያ የግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው ስንዴ፣ገብስ፣ጤፍ፣በቆሎና ጥራጥሬ ሰብሎችን ጨምሮ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በአዳዲስ የቴክኖሎጂ ግብዓት በመታገዝ በኩታ ገጠም መልማቱን አብራርተዋል።

በ2014/15 ዓ.ም የምርት ዘመን በክልሉ በዋና ዋና ሰብሎች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የሀገሪቱ የግብርና ምርት የወጭ ንግድ ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር አቶ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው በዞኑ በዘር ለመሸፈን ከታቀደው 439ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 280 ሺህ የሚሆነውን በኩታ ገጠም መልማቱን ጠቅስው ከዚህ ውስጥ 188ሺህ የሚሆነው በስንዴ ብቻ መሸፈኑን ገልጸዋል።

በተለይ አርሶ አደሩን በማሳመን የተበጣጠሰ ማሳውን አንድ ላይ በማድረግ በኩታ ገጠም ተመሳሳይ ቴክኖሎጂና ግብዓት ተጠቅሞ እንዲዘራ በማድረግ ረገድ የተሳካ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በክልሉ በዘር ለመሸፈን ከተዘጋጀው 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ እስከ አሁን በኩታ ገጠም የለማውን ጨምሮ 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሚሆነው በዘር መሸፈኑ ተመላክቷል።

(ኢዜአ)

Exit mobile version