Site icon ETHIO12.COM

ተጋድሎ በደጎሎ

ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የውጪም ሆነ የውስጥ ጠላቶች ሲያጋጥሟት ዜጎቿም በአንድ አይነት አስተሳሰብ እና በአንድ አይነት ዓላማ በደም እና በህይወታቸው ቤዛነት የማያልፍ ታሪክ ሰርተው ህዝብና ሀገርን አፅንተዋል።

ህዝቦቿ የሀገርን ሉዓላዊነትን ለመዳፈር ለሚሞክሩ ማንኛውም ፀረ ሠላም ሃይሎች በተባበረ ክንዳቸው “ዶጋመድ” እንደሚያደርጉት ለማወቅ የታሪክ ድርሳናትን ማገላበጥ አይጠበቅብንም። ምክንያቱም በቅርቡ እንኳን አሸባሪው እና ወራሪው የህውሃት ቡድን ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ ሲቋምጥ የሀገራችን ህዝቦች ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከህፃን እስከ አዛውንት ግንባር መዝመታቸው ብቻ ሁነኛ ምስክር መሆን ስለሚችል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በገጠማት ፈተናዎች ሁሉ ቆራጥ ጀግና እና ሀሞተ ኮስታራ ጀግኖች በየዘመኑ ነበሩ አሁንም አሉ ወደ ፊትም ይኖራሉ።

አሸባሪው እና ወራሪው የህውሃት ቡድን ወረራ ባደረገባቸው አንዳንድ የአማራ ክልል ወረዳዎች እንዲሁም በአፋር የተወሰኑ አካባቢዎች ለማመን የሚከብዱ አፀያፊ ተግባራትን መፈፀሙ የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ በጥቁር አሳፋሪ መዝገብ ተከትቧል።

በደቡብ ወሎ ዞን በጃማ ደጎሎ ወረዳ አንድ ወጣት ስለሰራው አስገራሚ ጀብዱ ልነግራችሁ ወደድኩ።

ወጣት ቴዎድሮስ ታደሰ ይባላል ውልደቱም እድገቱም ጃማ ዶጎሎ ነው። ለቤተሰብ ደግሞ የበኩር ልጅ ነው ይህ ወጣት አሸባሪው እና ወራሪው የህውሀት ቡድን በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ድባቅ ተመትቶ ከመሸሹ በፊት በወረራ ይዞት በነበረው ጃማ ዶጎሎ ውስጥ በርካታ ጥፋትን ሲያደርስ እንደነበረ ያነሳል።

ለወጣት ቴዎድሮስ ታደሰ የመጀመሪያ ጥያቄዬን ጠየኩት ጥያቄው ደግሞ ከአሸባሪው የህውሃት ቡድን አባላት ጋር እንዴት ተገናኛችሁ የሚል ነበር?

በሰፈራችን ሁለት የእነሱ ታጣቂዎች መጡ አንደኛው ክላሽ ይዟል ሌላኛው ደግሞ ዱላ ነበር የያዘው እኔ ደግሞ እቤቴ ደጃፍ ቁጭ ብዬ ነበር እዚህ ጠላት ወይም አብዮታዊ አሉ አለኝ “መከላከያ ሠራዊቱን ማለታቸው ነው”። አረ የለም አልኳቸው በመቀጠል ሁለቱ በትግረኛ አውርተው ወደ እኛ ቤት ለመግባት ተስማሙ።

በመቀጠል አንደኛው መሳሪያ የያዘው በረንዳ ላይ ቁጭ አለ አንደኛው ደግሞ ሳሎን ቤት ገብቶ በመበርበር የእህቴን የአንገት ወርቅ እና የጆሮ ጌጥ እንዲሁም 5ሺህ ብር ይዞ ወጣ እና ለጓደኛው የፈለግነውን አግኘተናል አለው። መሳሪያ የያዘው ሌላ ነገር ምን አላችሁ? አለኝ ይላል ወጣት ቴዎድሮስ

እኔም በማስከተል ተጨማሪ ጥያቄ ጠየኩት ምን አልካቸው?

በጓሮ የሚሸጡ በጎች ነበሩን እና ድምፅ ስለሰሙ ከዋሸሁ እንዳይገሉኝ የሚሸጡ በጎች አሉ አልኩት ፍጠን አምጣ አለኝ “ወዲ ዘኸድጊ” እያለ እኔም ከሚሸጡት በጎች መካከል አንዱን አመጣሁ እና ሰጠሁት።

ስንት ብር ነው የሚሸጠው አለኝ 1500 ብር አልኩት እየሳቀ ለመከላከያ ቢሆን ኖሮ በነፃ ነበር የምትሰጠው ብሎ ተፋብኝ እኔም ዝም ብዬ በውስጤ አንድ ሃሳብ እያሰብኩ ነበር።

ክላሽ የያዘው ጓደኛውን ጠርቶ በጉን ያዝ እንሂድ አለው እሱም እሺ አለው እና በጉን ተሸክሞ ወጣ አንደኛው ደግሞ ክላሽ አንግቶ ሊወጣ ሲል መሳሪያውን ከትከሻው ላይ በፍጥነት ቀማሁት በዚህ ጊዜ ሁለቱም እግሬ አውጪኝ ብለው ፈረጠጡ።

ክላሹን ከተቀበልክ በኋላ ምን አደረክ የእኔ ጥያቄ ነበር?

ክላሹ በእጄ ሲገባ አንደኛው በጉን ጥሎ ወደ ግራ ታጠፈ አንደኛው ደግሞ ወደ ቀኝ ታጠፈ እኔም ክላሹን ወደ ቀኝ ወደታጠፈው እየተካስኩ ተከተልኩት ነገር ግን አለገኘሁትም።

ከእነሱ የወሰድኩትን መሳሪያ ይዤ ወደ ጫካ ገባሁ ከዛ በኋላ እነሱን አግኝቻቸው አላውቅም ብሎ ሃሳቡን ያጠቃልላል።

አሸባሪውን እና ወራሪው የህውሃት ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ይህንን የሽብር ቡድን የታጠቃቸውን መሳሪያዎች የዘረፋቸዉን የህዝብ እና የመንግስት ንብረት ይዞ እንዳይወጣ መማረክ እና መደምሰስ እንደሚያስፈልግ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ጀግናው ወጣት ቴዎድሮስ ታደሰ ከአሸባሪው የህውሃት ቡድን የማረከውን መሳሪያ ለሌሎችም ሀገር ወዳድ የአካባቢዉ ወጣቶች ጥሩ አብነት ይሆናል።

ጀግናዉ ቴዎድሮስ ታደሰ በአሁን ሰዓት ከጁንታዉ የማረከዉን ክላሽ ታጥቆት የአካባቢውን ሠላም እያስጠበቀበት ይገኛል።

ለሀገር እና ለህዝብ ክብር መቆም ይሉሃል ይህ ነው። ኢትዮጵያ አሸንፋለች።

ፍፁም ከተማ
ፎቶግራፍ አከለ አባተ Endf fb

Exit mobile version