Site icon ETHIO12.COM

አቶ ምትኩ ካሳ ላይ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰረት በፍርድ ቤት ተወሰነ

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩት የቀድሞው የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ላይ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰረት ውሳኔ አስተላለፈ። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው፤ የፌደራል ዐቃቤ ህግ ክስ ለመመስረቻ የጠየቀውን ጊዜ በመቀበል እና የአቶ ምትኩ ጠበቃ በድጋሚ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ነው።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በዛሬ አርብ ነሐሴ 6፤ 2014 ውሎው በመጀመሪያ ያደመጠው፤ በተጠርጣሪው ላይ ምርመራ ሲያካሄድ የቆየው የፌደራል ፖሊስ የደረሰበትን ደረጃ ነው። የፌደራል ፖሊስ በአቶ ምትኩ ላይ ሲያከናው ን የነበረውን ምርመራ አጠናቅቆ መዝገቡን ለዐቃቤ ህግ ማስተላለፉን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል። 

የምርመራ መዝገቡን በዛሬው ዕለት ከፖሊስ መረከቡን ያረጋገጠው ዐቃቤ ህግ፤ ክስ ለመመስረት የሚያስችሉት 15 ቀናት እንዲሰጡት ለችሎቱ አመልክቷል። በተጠርጣሪው ላይ ክስ እስኪመሰረትባቸው ድረስ በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ እንዲሰጥለትም ፍርድ ቤቱን በተጨማሪነት ጠይቋል።

የፌደራል ዐቃቤ ህግ ለዚህ ያቀረበው መከራከሪያ ተጠርጣሪው “ከደረሰው ጉዳት አንጻር እርሳቸውም ሊሸሹ፤ ሌሎች ተጠርጣሪዎችንም ሊያሸሹ ይችላሉ” የሚል ነው። ዐቃቤ ህግ፤ የቀድሞው ኮሚሽነር “ሊሸሹ የሚችሉበትን” አመክንዮ ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው “ሊከሰሱ ከሚችሉበት ወንጀል አንጸር ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ሲያውቁ ሊጠፉ ይችላሉ” በሚል አገላለጽ ነው።

የተጠርጣሪው ጠበቃ አቶ ሀብተማሪያም ጸጋዬ በበኩላቸው “ደንበኛዬ እንዲህ አይነት ስብዕና ያላቸው አይደሉም። የመንግስት ኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩ ናቸው” ሲሉ ተጠርጣሪው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ለችሎቱ ጥያቄ አቅርበዋል። ዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ምትኩ በችሎቱ ባደረጉት ንግግር፤ ተመሳሳይ ሀሳብ ሰንዝረዋል። 

ለ14 ዓመታት እስከ ሚኒስትር ዴኤታነት በደረሰ የመንግስት የኃላፊነት ቦታ ማገልገላቸውን የጠቀሱት አቶ ምትኩ፤  በዋስትና ከእስር ቢለቀቁ “ከሀገር እንደማይወጡ” ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። የተጠረጠሩበትን ወንጀልም በተመለከተም “ከገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በተጻፈ ደብዳቤ እንጂ፤ ስልጣኔን በመጠቀም ያደረግኩት ነገር የለም” ሲሉ በፖሊስ ሲቀርብባቸው የነበረውን ውንጀላ አጣጥለዋል። 

የቀድሞው የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር በቁጥጥር ስር በዋሉበት ቀን ፖሊስ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ በሌሉ ተረጂዎች ስም እና የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን “ለኤልሻዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት 472 ሚሊዮን ብር እንዲሰጥ አድርገዋል” ሲል ወንጅሏቸው ነበር። ከዚህ በተጨማሪም፤ “ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚገመት 512 ሺህ ኩንታል ስንዴ እንዲሁም ሌሎች ምግብ ነክ ቁሳቁሶች ከተራድኦ ድርጅቱ ጋር በመመሳጠር ለግል ጥቅም አውለዋል” በሚል አቶ ምትኩን እንደጠረጠራቸው ፖሊስ በወቅቱ ማስታወቁ ይታወሳል።

አቶ ምትኩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ከአንድ ወር በፊት ሐምሌ 6፤ 2014 ሲሆን ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት ለሶስተኛ ጊዜ ነው። የቀድሞው ኮሚሽነር ጠበቃ በዛሬው የችሎት ውሎ፤ የደንበኛቸው የዋስትና መብት የማይከበር ከሆነ ለዐቃቤ ህግ የሚሰጠው የክስ መመስረቻ ጊዜ ያጠረ እንዲሆን ጠይቀው ነበር። “ክሱን ጽፎ ለማቅረብ 15 ቀን አይጠይቅም” ያሉት አቶ ሀብተማሪያም፤ “ምርመራውን ዐቃቤ ሀግ ይመራው ስለነበር አጭር ጊዜ በቂ ነው” ሲሉ ተከራክረዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ አቶ ምትኩ እና ጠበቃቸው ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለዐቃቤ ህግ የክስ መመስረቻ 15 ቀናትን ፈቅዷል። ችሎቱ ዋስትናውን ውድቅ ያደረገው “ተፈጸመ በተባለው ወንጀል የደረሰውን ውድመት፣ የወንጀሉን ውስብስብነት እና በፖሊስ በርካታ ማስረጃዎች መሰብሳባቸውን” ምክንያት በማድረግ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር

Exit mobile version