Site icon ETHIO12.COM

ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት ጀምረሃል በሚል በመጥረቢያ የገደለችው 18 ዓመት ፅኑ እስራት ተወሰነባት

ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት ጀምረሃል በሚል ምክንያት የሶስት ልጆቿን አባት በመጥረቢያ በመምታት የገደለችው ግለሰብ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣቷን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ትዕግስት አዘዘው የተባለቸው ግለሰብ ወንጀሉን የፈፀመችው መስከረም 10 ቀን 2014 ዓ/ም በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው አንቆርጫ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ ተከሳሿ በዕለቱ ከምሽቱ 3 ሰዓት ገደማ የ3 ልጆቿ አባት የሆነው ባለቤቷን ሟች አወቀ ይርዳውን “ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት ጀምረሃል፤የተለያዩ ሴቶችንም በስልክ ታናግራለህ” በሚል ምክንያት ሶፋ ላይ በተኛበት ጭንቅላቱን በመጥረቢያ ደጋግማ በመምታት ህይወቱ እንዲያልፍ ማድረጓን በአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ከሰው መግደል ወንጀል ምርመራ ክፍል የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡


ትዕግስት አዘዘው በፈፀመችው ወንጀል በቁጥጥር ስር ውላ ምርመራ ከተጣራባት እና ክስ ከተመሰረተባት በኋላ ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የከባድ ውንብድና እና ግድያ 1ኛ ወንጀል ችሎት በሰው እና በሰነድ ማስረጃ ጥፋተኛ መሆኗን በማረጋገጥ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ የወሰነባት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በትዳር መካከል አለመግባባቶች በሚያጋጥሙበት ወቅት በመነጋገር ለመፍታት ከመሞከር እና ይህም ካልተሳካ በሰላማዊ መንገድ ከመለያየት በዘለለ በስሜታዊነት እና በቅናት መንፈስ ተነሳስቶ ወንጀል መፈፀም ከሚያስከትለው የህግ ተጠያቂነት ባሻገር በልጆች እና በቤተሰብ ላይ የሚያሳድረው ስነ ልቦናዊ ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት ነገሮችን በሰከነ ሁኔታ ማመዛዘን እንደሚገባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ዘገባ፡- ዋና ኢንስፔክተር ጋሻውበዛ ተስፋዬ

Exit mobile version