Site icon ETHIO12.COM

ጣሊያናዊቷ ጋዜጠኛ የአድሃኖምን ሀሰተኛ ክስ አጋለጠች

በቅርቡ የትግራይን ሁኔታ በአካል የተመለከተችው ጣሊያናዊቷ ጋዜጠኛ የቴዎድሮስ አድሃኖምን ሀሰተኛ ክስ አጋለጠች

ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም ከሰሞኑ እየሰጡት ያለው መግለጫ አሁንም ዳግም የህወሓት ሽብር ቡድን ጥብቅናቸውን በገሀድ ያሳዩበት፤ በገለልተኛው ተቋም ውስጥ ገለልተኛ ያልሆኑ ሰው መሆናቸው የተረጋገጠበት ሆኗል።

ዶክተር ቴድሮስ ወደትግራይ በብዛት ያለምንም ችግር እየገባ ያለውን እርዳታ ከቁብ ሳይቆጥሩ ዓለም ትግራይን እንደረሳ በመጥቀስ ጭራሽ ጉዳዩን ከቆዳ ቀለም ጋር ለማያያዝ ሞክረዋል።

ይህ የዳይሬክተሩ ንግግር መሬት ላይ ያለውን እውነት ያላገናዘበ መሆኑን በመጥቀስ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች የዶክተር ቴድሮስን ድብቅ አጀንዳ እያጋለጡ ይገኛሉ።

ከእነዚህ ጋዜጠኞች መካከል ጣሊያናዊቷ ፍራንቼስካ ሮንቺን አንዷ ናት።

ጋዜጠኛዋ ወደ ትግራይ ክልል እየገባ ያለውን የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት በቦታው ተገኝታ በመጎብኘት የሰውዬው ንግግር መሠረተ ቢስ መሆኑን አጋልጣለች።

ጋዜጠኛዋ በየቀኑ ዕርዳታ የጫኑ መኪናዎች ወደ መቀሌ ሲገቡ እንደተመለከተች ገልጻለች። ሰዎችንም አነጋግራ ይሄንኑ አረጋግጣለች።

ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ብቻ አምስት ሺህ 226 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ መግባታቸውን፤ 257 የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሆኑ አውሮፕላኖች በረራ ማድረጋቸው ይህችው ጣሊያናዊት ገልጻለች።

እውነቱ ይሄ በመሆኑም ከጋዜጠኛዋ በተጨማሪ ሌሎች ለእውነታው ቀረቤታ ያላቸው በተለያዩ አገራት ያሉ ሰዎችም ዳይሬክተሩን እየተቿቸው ይገኛል።

ጄ ማይክል ስሚዝ የተባሉ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ሰው በትዊተር ገጻቸው፤ “በሺዎች የሚቆጠሩ የጤና ተቋማት በሽብር ቡድኑ ቢወድሙም የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ግን ይህንን ሃላፊነታቸው ወደ ጎን በመተው ደጋግመው የሚናገሩት አንድ ነገር ነው፤ ለሽብር ቡድኑ ይጠቅማል ያሉትን ጉዳይ ብቻ ማንሳት” ሲሉ ነው የተቹት።

ይህ የዋና ዳይሬክተሩ አቋምና ተግባር ከተመደቡበት ሥራ ጋር ፍጹም የማይገናኝ እንደሆነ በተደጋጋሚ ከሚሰጧቸው መግለጫዎች ዓለም የታዘበው ጉዳይ ነው።

ለዚህም ይመስላል እርሳቸው በድርጅቱ ውስጥ ባይኖሩ ይሻላል የሚል ሃሳብ ከአፍሪካዊያን ሳይቀር እየተሰነዘረ የጀመረው።

ቼፒኪሩይ ባሲሊዮ የተባለ አፍሪካዊ በትዊተር ገጹ ላይ ባስፈረው ጽሁፍ፤ ዓለም ከዶክተር ቴድሮስ አድኀኖም ውጭ የተሻለች ናት፤ አንድ ጊዜ አሸባሪ የሆነ ሰው ምንጊዜም አሸባሪ ነው፤ ዶክተር ቴድሮስ የህወሓት አባል የነበሩ የብሔር የበላይነትን ለማስጠበቅ የቆሙ ናቸው ሲል ገልጿቸዋል።

መንግስት በትግራይ ክልል የነበረውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ካጠናቀቀ በኋላ በትግራይ ክልል የሚገኙ አርሶ አደሮች የእርሻ ስራን ተረጋግተው እንዲያከናውኑ የተናጠል የትኩስ አቁም ውሳኔን አሳልፎ ከትግራይ ቢወጣም የሽብር ቡድኑ ግን ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በአማራ እና በአፋር ክልል ወረራ ፈጽሞ ዶክተር ቴድሮስ አይተው እንዳላዩ ያለፉትን እና ዓለም ያወገዘውን ግፍ ፈጽሟል።

ይህም ሆኖ መንግስት አሁንም ለትግራይ ህዝብ ዘላቂ ጥቅም ሲል የቡድኑን ሤራና ግፍ ወደ ጎን ትቶ እጁን ለሰላም ቢዘረጋም አሁንም ይህ ቡድን የጦርነት ጉሰማ ላይ ተጥምዷል። የዶክተር ቴድሮስ የሰሞኑ ንግግርም የዚህ ተከታይ አጀንዳ መሆኑ ግልጽ ሆኗል።

በአንጻሩ የመንግስት ኮምንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በሰጡት መገለጫ፤ የህወሓት ታጣቂ ቡድን የጦርነት ነጋሪት ቢጎሰምም መንግስት ግን አሁንም ለሰላም ቅድሚያ ይሰጣል” ማለታቸው ይታወሳል።

(ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version