ለትህነግ ሊተላለፍ ነበረ የተባለ ነዳጅ ተያዘ፤ 215 እርዳታ የጫኑ ከባድ መኪኖች ወደ መቀለ አቅንተዋል

ዛሬ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና የአፋር ኮሙኒከጭን ቢሮ ሁለት ዜናዎችን አሰምተዋል። “በአፋር ክልል ለአሸባሪው ለትህነግ ቡድን ሊተላለፍ የነበረ ከ3 ሺህ 800 ሊትር በላይ ቤንዚን ተያዘ” የሚለው ዜና በተሰማበት ቅጽበት፤ አሶሼትድ ፕሬስን ጨምሮ በርካታ ሚዲያዎች 215 ከባድ የጭነት መኪኖች እርዳታ ጭነው ከአፋር መነሳታቸውንና መንግስት እርዳታ እንዲገባ እያሳየ ያለውን ድጋፍ ጨምረው ገልጸዋል።

ከዕርዳታው እህልና መድሃኔት ጋር መንግስት ነዳጅ እየላከ መሆኑንን የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ የሚመለከታቸው ወኪሎቻቸው ቢገልጹም፣ ነዳጅና መሳሪያ ወደ ትግራይ በኮንትሮባንድ እየገባ እንደሆነ ጭምጭምታ ነበር። በተለይ በአማራ ክልል ከተራ ኮንትሮባንድ ጀምሮ ከፍተኛ የመሳሪያ ሽያጭ የሚያከናውኑት የሚታወቁ ሃብታም የሚባሉና በተለያየ አደረጃጀት ስም የሚዲያ ሽፋን ያላቸው ስለመሆናቸው ስለጉዳዩ የሚያውቁ ሲወተውቱ ቆይተዋል።

በአፋር ክልል ለአሸባሪው የትህነግ ቡድን ሊተላላፍ የነበረ ከ3 ሺህ 800 ሊትር በላይ ቤንዚን መያዙን በሰመራ-ሎጊያ ከተማ አስተዳደር የሰመራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ናስታወቁን የመንግስት ሚዲያዎች አመልክተዋል።

የክፍለ ከተማው ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር ኢብራሂም መሀመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከሰመራ ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ወጣ ብሎ በሚገኝ ልዩ ስሙ “ኡድሃዩ” በሚባል አካባቢ በቁጥቋጦና ድልድይ ስር የተደበቀ 154 ባለ 25 ሊትር ጄሪካን ቤንዚን ትናንት በሕብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ውሏል።

የተያዘው ቤንዚን ከ150 ሺህ ብር በላይ እንደሚያወጣ ተናግረዋል።

በአካባቢዉ ቤንዚኑን ያዘዋውሩ ነበር ተብለዉ የተጠረጠሩ ሶስት ሰዎች ከአንድ ታርጋና ቦሎ ከሌለው ቶዮታ መኪናና አንድ ክላሽንኮቭ ጋር መያዛቸውን አመልክተዋል።

መነሻውን ከሰመራ-ሎግያ ከተማ አድርጎ በኮንትሮባንድ ንግድ ለሕወሓት የሚተላለፉ እቃዎች መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመጨረ መምጣቱን የገለጹት አዛዡ፤ ባለፉት ስድስት ወራት በፈንቲ ረሱ ዞን በኩል ለሽብር ቡድኑ ሊተላለፍ የነበረ ከ25 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን መያዙን አስታውሰዋል።

ቤንዚን፣ ጨዉ፣ ስኳር፣ ቡና፣ ኦሞና ካሜራ ከእቃዎቹ መካከል እንደሚገኙበትም ገልጸዋል። ፖሊስና ሚሊሻ ለሽብር ቡድኑ የኮንትሮባንድ እቃዎች እንዳይተላለፉ ቁጥጥርና ክትትል እያደረጉ እንደሚገኙም ረዳት ኢንስፔክተር ኢብራሂም ተናግረዋል። የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው መውጫና መግቢያ ቦታዎችን በመለየት ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተከናወነ ይገኛልም ብለዋል።

ይህ ዜና በተሰማ ቅጽበት “ሰብዓዊ ዕርዳታ የጫኑ 215 ተሽከርካሪዎች ከአፋር ወደ ትግራይ አቀኑ” ሲል አሶሺየትድ ፕሬስ የዓለም የምግብ ድርጅትን ጠቅሶ ዘግቧል።

መንግስት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ማቆሙን ይፋ ካደረገ ወዲህ ወዲህ ከፍተኛ የተባለ ሰብዓዊ ዕርዳታ ወደ ትግራይ እየተጓጓዘ መሆኑንን የዓለም የምግብ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሰሞኑንን አስታውቀዋል። የትግራይ ሕዝብ በከፋ ችግር ውስጥ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ መሰነበቱ፣ ህዝቡ ችግር ላይ ቢሆንም በመቀለ በርዳታ የሚገባ መድሃኒት በአዳዲስ ፋርማሲዎች ውስጥ ለገበያ እየዋለ መሆኑ፣ እርዳታ ለታጣቂዎች ብቻ እንደሚሰጥና ይህንኑም ዶክተር ደብረጽዮእን ” ጦሩ ካልበላ አይዋጋም ሰጥተናል” ሲሉ መናገራቸው የተለያዩ ሚዲያዎች የራሳቸውን ምንጭና የትግርኛ ንግግር እየተረጎሙ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ለትግራይ የሚገባው ዕርዳታ በቂ ባይሆንም የግብረ ሰናይ ሰራተኞች የፌድራል መንግሥት ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም ወደ ትግራይ በሚጓዘው ሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ ተግባራዊ አድርገዋቸው የነበሩ ገደቦችን እንዳላሉ መናገራቸውን አሶሼትድ ፕሬስን ጠቅሶ የጀርመን ድምጽ አስታውቋል።


Leave a Reply