Site icon ETHIO12.COM

ምርጫ ቦርድ ኢሠፓ የቀረበለትን ማመልከቻ ውድቅ አደረገ ድርጅቱ “ጸረ ዲሞክራሲና ወንጀለኛ ድርጅት ነው”

በደርግ ዘመነ መንግስት “በሀገሪቱ በብቸኝነት እንዲንቀሳቀስ እውቅና ተሰጥቶት ከነበረ የፖለቲካ ድርጅት ጋር” የሚመሳሰል እንደሆነ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤው ጠቅሷል። በሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ የነበረው ኢሠፓ በግንቦት 1983 ከስልጣን መውረዱን ተከትሎ፤ የፖለቲካ ድርጅቱ “ጸረ ዲሞክራሲ” እና “ወንጀለኛ ድርጅት ነው” ተብሎ በህግ እንዲፈርስ መደረጉን ምርጫ ቦርድ አስታውሷል።

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ (ኢሠፓ) ለመመስረት የቀረበለትን ማመልከቻ ሳይቀበለው መቅረቱን አስታወቀ። ቦርዱ ማመልከቻውን ያልተቀበለው፤ ሊመሰረት የታሰበው ፓርቲ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መስክ ህያው ከነበረ የፖለቲካ ድርጅት ጋር ተመሳሳይ ስያሜ ያለው በመሆኑ እና ኢሠፓ የተባለው ድርጅት እስካሁንም ጸንቶ ባለ አዋጅ እንዲፈርስ በመደረጉ ምክንያት መሆኑን ገልጿል።

ምርጫ ቦርድ ይህን ያስታወቀው፤ ፓርቲውን ለመመስረት ለቦርዱ ማመመልከቻ ላሰገቡ አስተባባሪዎች ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 17፤ 2014 በጻፈው ደብዳቤ ነው። በደርግ ዘመነ መንግስት ገዢ ፓርቲ የነበረውን ኢሠፓን ዳግም ለማቋቋም የተሰባሰቡ አደራጆች፤ የሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ጊዜያዊ የምዝገባ ፍቃድ እንዲሰጣቸው ለምርጫ ቦርድ ማመልከቻ ያስገቡት ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ነበር።

ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ትላንት ሰኞ ነሐሴ 16 ባደረገው ስብሰባ፤ የፓርቲው አደራጆች ባቀረቡት ማመልከቻ ላይ ውሳኔ አሳልፏል። የአስተባባሪዎቹን ማመልከቻ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ላይ ከተቀመጡ ድንጋጌዎች አንጻር መርመሩን የገለጸው ቦርዱ፤ በአዋጁ መሰረት በ“ኢሠፓ” ስም ሀገራዊ ፓርቲ ለማስመዝገብ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል። 

ቦርዱ ይህን ውሳኔ ለማሳለፍ መሰረት ያደረገው የምርጫ አዋጁ ድንጋጌ፤ “መመዝገብ ስለማይችል የፖለቲካ ፓርቲ” የተዘረዘረበትን ክፍል ነው። በአዋጁ አንቀጽ 69 ላይ የሰፈረው በዚህ ድንጋጌ ላይ፤ ለመመዝገብ ማመልከቻ ያቀረበው የፖለቲካ ፓርቲ “የመረጠው ስም፣ አሕጽሮተ ስም፣ አርማ ወይም የመለያ ምልክት በሌላ ፓርቲ የተያዘ ከሆነ ወይም ከሌላ ፓርቲ ስም፣ አሕጽሮተ ስም፣ አርማ ወይም የመለያ ምልክት ጋር መራጮችን ሊያሳስት በሚችል ደረጃ የሚቀራረብ ከሆነ ቦርዱ አይመዘግበውም” ይላል። 

የምዝገባ ጥያቄ ያቀረበው ፓርቲ የተጠቀመበት ስያሜ፤ በደርግ ዘመነ መንግስት “በሀገሪቱ በብቸኝነት እንዲንቀሳቀስ እውቅና ተሰጥቶት ከነበረ የፖለቲካ ድርጅት ጋር” የሚመሳሰል እንደሆነ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤው ጠቅሷል። በሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ የነበረው ኢሠፓ በግንቦት 1983 ከስልጣን መውረዱን ተከትሎ፤ የፖለቲካ ድርጅቱ “ጸረ ዲሞክራሲ” እና “ወንጀለኛ ድርጅት ነው” ተብሎ በህግ እንዲፈርስ መደረጉን ምርጫ ቦርድ አስታውሷል።

ቦርዱ በደብዳቤው የጠቀሰው ህግ፤ “ሰላማዊ ሰልፍ እና ህዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ስነ ስርዓትን” በሚመለከት በሽግግር መንግስቱ ወቅት በተቋቋመው የተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት በነሐሴ 1983 የወጣውን አዋጅ ነው። ይህ አዋጅ “የተከለከሉ ሁኔታዎችን” በደነገገበት ክፍሉ ላይ፤ “የኢሠፓና የደህንነት አባላት የተወካዮች ምክር ቤቱ ሌላ ውሳኔ እስካልወሰነ ድረስ በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳይሳተፉ ታግደዋል። ድርጅቶቹም ጸረ-ዴሞክራሲ እና ወንጀለኛ ድርጅቶች ስለሆኑ ፈርሰዋል” ይላል። 

ለምርጫ ቦርድ ማመልከቻ ያስገባውን ፓርቲ በማደራጀት ሂደት ላይ ተሳታፊዎች ከነበሩ ግለሰቦች ውስጥ፤ በኢሠፓ በከፍተኛ አመራርነት ያገለገሉ እና የቀድሞው የፓርቲው አባላት እንደሚገኙበት አደራጆቹ ከዚህ ቀደም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀው ነበር። ኢሠፓን ያፈረሰው እና አባላቱንም ከፖለቲካዊ ተሳትፎ ያገደው አዋጅ “አለመሻሩን” በማስረጃነት የጠቀሰው ምርጫ ቦርድ፤ “አሁንም ጸንቶ ባለ ህግ ወንጀለኛ ተብሎ ብያኔ ካረፈበት የፖለቲካ ድርጅት” ጋር የሚመሳሰል ስያሜ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ እንደማይችል ገልጿል።   

“በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ የምዝገባ ጥያቄውን ቦርዱ ቢቀበል ያልተሻረ ህግ እንደተሻረ እንዲሁም በህግ የፈረሰ ድርጅት የህግ ገደቡ ታልፎ እንደገና እንደተቋቋመ የሚያስመስል የህዝብ ዕይታ (public perception) እንደሚፈጥር ግልጽ ነው” ሲል ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ላይ አስፍሯል። “ይህን አይነት የህዝብ እይታ በምርጫ ወቅት መራጮችን ወደሚያምታታ መረጃ እና አረዳድ ማደጉ አይቀርም” ያለው ቦርዱ፤ ኢሠፓ በሚል ስያሜ ሀገራዊ ፓርቲ ለማስመዘገብ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን አትቷል።  

በምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተፈርሞ የወጣው የዛሬው ደብዳቤ፤ ኢሠፓን ለመመስረት የተደራጁ አስተባባሪዎች “በሌላ ስያሜ አላማቸውን ለማራመድ ፓርቲ የማደራጀት እና በህጉ መሰረት ሲመዘገብም የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማድረግ” መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን አመልክቷል። ቦርዱ የፓርቲው አደራጆች በሌላ ስያሜ ከመጡ ጥያቄያቸውን ለማስተናገድ ዝግጁ  መሆኑን ቢገልጽም፤ የምርጫ አዋጅ ግን በቦርዱ ውሳኔ ላይ ቅሬታ ያለው አካል ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ እንደሚችል ደንግጓል።

በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ መሰረት፤ ምርጫ ቦርድ በሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘ አካል “ውሳኔው በጽሁፍ ከደረሰው ቀን ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ አቤቱታውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል።” ይህ አዋጅ “አቤቱታ ያቀረበው አካል ለዚህ ጉዳይ አፈጻጸም ሕጋዊ ሰውነት እንዳለው” እንደሚቆጠርም አስፍሯል። የፖለቲካ ፓርቲው ህጋዊ ወኪል ሆኖ የሚቆጠረውም፤ “በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ተመርጦ በምዝገባ ማመልከቻው ላይ ፈርሞ ያቀረበው የፓርቲ መሪ” እንደሆነም አዋጁ አብራርቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Exit mobile version