Site icon ETHIO12.COM

391 ህገወጥ ገንዘብ አዘዋዋሪዎች በህግ ጥላ ስር ናቸው፤ ህገወጦችን ለሚጠቁሙ ወሮታ ይፋ ሆነ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአገሪቱ የሚካሄዱ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን ለመቆጣጠር በጥቆማ ለሚተባበሩ ግለሰቦች የተለያየ መጠን ያለው ወሮታ እንደሚከፍል አስታወቀ።391 ህገወጥ ገንዘብ አዘዋዋሪዎች በህግ ጥላ ስር ናቸው፤ ህገወጥ የሃዋላ ተዋንያኖችን ለሚጠቁሙ ባንኩ ወሮታ እንደሚከፍል ይፋ አደረገ።

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት መግለጫ መንግሥት ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።

በአገሪቱ እየተባባሰ ያለውን የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በሕገወጥ መንገድ የሚካሄዱ የተለያዩ የገንዘብ ዝውውሮችን ለመቆጣጠር ያስችላሉ ያላቸውን እርምጃዎችን አሳውቋል።

በዚህም ምክንያት በባንክ ከተፈቀደው በላይ የገንዘብ መጠን ይዘው የሚገኙ ግለሰቦችን ለጠቆሙ ከተያዘው ገንዘብ 15 በመቶ፣ የውጭ አገር ገንዘብ ዝውውር ለሚጠቁሙ 15 በመቶ፣ ሕገወጥ ሐዋላን ለሚጠቁሙ 25 ሺህ ብር ወሮታ ብሔራዊ ባንክ እንደሚከፍል ገዢው አሳውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የወርቅ ኮንትሮባንድ ለሚጠቁሙ 15 በመቶ የወርቁን ዋጋ፣ የሐሰተኛ የገንዘብ ኖት ህትመትን ለሚጠቁሙ ከ20 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር የሚደርስ ወሮታ እንደሚከፈልም ተገልጿል።

ይህንንም ሕገወጥ ድርጊት ለመጠቆም ተባባሪ የሚሆኑ ሰዎችን ለማበረታታት የሚሰጠውን የወሮታ ክፍያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱንና የጠቋሚዎችም ደኅንነት የተጠበቀ እንደሚሆን የብሔራዊ ባንክ ገዢው ገልጸዋል።

ከአገር ውስጥ ጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪን በመግዛት ከውጭ እቃ እያስገቡ ያሉትን ለመቆጣጠር፣ በፍራንኮ ቫሉታ ከውጭ እቃ የሚያስመጡ ግለሰቦችና ተቋማት በውጭ አገር ያላቸውን የዶላር መጠን የሚያሳውቅ የባንክ ስቴትመንት ለብሔራዊ ባንክ የማቅረብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ እየጨመረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የምንዛሪ ዋጋ ከዚህ በፊት ከነበሩት ሁሉ ከፍተኛው መሆኑን ነጋዴዎች ይናገራሉ።

በዚህም በይፋዊው የባንኮች ግብይት የዶላር የምንዛሪ ዋጋ የአንድ የአሜሪካ ዶላር ዋጋ 52 ብር አካባቢ ሲሆን፣ በጥቁር ገበያ በእጥፍ እንደሚመነዘር ነጋዴዎች ገልጸዋል።

መንግሥትም ይህንን ለመቆጣጠር ሕገወጥ የተባሉትን የውጭ ምንዛሪ አዘዋዋሪዎች ላይ ቁጥጥር በማድረግ በተደጋጋሚ ተጠርጣሪዎችን መያዙን ሲገልጽ ቆይቷል።      

ዶክተር ይናገር ደሴ እንዳሉት ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር መንግሥት እስካሁን በወሰዳቸው እርምጃዎች 391 ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ እና የሐዋላ ሥራ ሲያከናውኑ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በሕግ ተይዟል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በሕገወጥ ድርጊቱ ውስጥ ተባባሪ የሆኑ የባንክ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ላይ ማጣራት በማድረግ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

ብሔራዊ ባንክ ከዚህ በፊት ማንኛውም ግለሰብ ከ100 ሺህ ብር በላይ እንዲሁም ድርጅቶች ደግሞ 200 ሺህ ብር በላይ በእጃቸው ማስቀመጥ እንደማይችሉ ያሳወቀ ሲሆን፣ ከተጠቀሰው በላይ ለሆኑ ግብይቶች በባንኮች በኩል እንዲጠቀሙ ማዘዙ ይታወቃል።

ዜናው የቢቢሲ ነው ርዕስ ተቀይሯል

Exit mobile version