Site icon ETHIO12.COM

አምባሳደር ስለሺ በሎስ አንጀለስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የአሜሪካ ባለሃብቶች ጋር ተወያዩ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ በሎስ አንጀለስ እና አካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የአሜሪካ ባለሃብቶች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱም አምባሳደር ስለሺ በኢትዮጵያ ስላሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች እና አጠቃላይ የሀገሪቱ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ለተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።

ባለሃብቶቹ ኢትዮጵያ ገብተው መዋዕለንዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሃብቶች ስራቸው የተቃና ይሆን ዘንድ በመንግስት በኩል ካሁን ቀደም የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት በርካታ የኢኮኖሚ ዘርፍ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን መወሰዱን አንስተዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ ለረጅም ዓመታት በመንግስት ስር የነበሩ ኩባንያዎችን ወደ ግል ዘርፍ ማሸጋገር፣ እንደ ፋይናስ፣ ቴሌኮም፣ ኢነርጂ እና መሰል ዘርፎችን የውጭ ባለሃበቶች ገብተው እንዲሰሩ መፈቀድን ለአብነት አንስተዋል።

ከውጭ የሚገባውን የምግብ ነክ አቅርቦት በሀገር ውስጥ አቅም ለመተካት ብሎም ወደወጭ ገበያ ለመቀየር እየተሰራ ነው ያሉት አምባሳደሩ÷ ባለፉት ሶስት ዓመታት በተቀናጀ የስንዴ ምርት ውጤቶች የተያዘው እቅድ እንደሚሳካ አመለካች ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሰፊ የሰው ኃይል፣ አመቺ የአየር ሁኔታ፣ ለገበያ አማካይ የጂኦግራፊ አቀማመጥ፣ ሰፊ የመሬት አቅርቦት፣ በፍጥነት እያደገ የሚገኝ የታዳሽ ኃይል እና መሰል መሰረተ ልማቶች ለባለሃብቶቹ ስራ ስኬት ጉልህ ሚና እንዳላቸውም አስረድተዋል፡፡

በተለይ በአሜሪካ ነዋሪ የዳያስፖራ ወገኖች የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት ከኢንቨስትመንት ተሳትፎነቱ ባለፈ ሀገር ይህን ፈታኝ ወቅት በምታልፈበት ወቅት አለኝታነትን ማረጋገጥ እንደሆነም ነው የገለጹት።

በተሳታፊዎቹ በኩል ከውጭ ምንዛሬ አቅርቦት፣ ወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ፣ የቢሮክራሲ፣ የመንግስት የፖሊሲ እቅዶች እና ተያያዥ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገሪቱን ወደተሻለ የለውጥ ጎዳና ለማራመድ እየሰራ ባለበት ውቅት በጽንፈኛው ቡድን የተደረገበት ወረራ ለመመከት የሀገርን አንድነትን ለማጽናት ተገዶ ወደ ጦርነት መግባቱን አምባሳደር ስለሺ ገልጸዋል።

ጉዳዩ በተቻለ ፍጥነት እልባት እንደሚየገኝ መንግስት ያለውን የሰላም ቁርጠኝነትም ጠቁመው ባለሃብቶቹ ከመነሻው ጀምሮ ወደ ስራ እስኪገቡ ድረስ ኤምባሲው ከሀገር ቤት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በውይይቱ ላይ በግብርና ልማት፣ በውሃና ኢነርጂ፣ በቴሌኮም፣ በጤና፣ በቡና ልማት፣ በሎጂስቲክስ፣ ፋይናንስ፣ በምርምር እና ሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች መሳተፋቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

Exit mobile version