በስድስት ወራት 2 ቢሊየን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 2 ቢሊየን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በመንግሥትና ህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ተቀዛቅዞ የነበረውን ኢንቨስትመንት በማነቃቃት በርካታ የውጭ ባለሃብቶችን መሳብ ጀምሯል፡፡

በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ፤ የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹና ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ መጠቀም እንዲችሉ በኦንላይንና በገጽ-ለገጽ የማስተዋወቅ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ሕንድ፣ አረብ ኤምሬትስ፣ ቻይና እና ጣሊያን ኮሚሽኑ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የተንቀሳቀሰባቸው ሀገሮች ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 2 ነጥብ 95 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ መታቀዱን ያስታወሱት ኮሚሽነሯ፤ በተለያዩ ችግሮችም ውስጥ አልፈን 2 ቢሊየን ዶላር ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወራት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከተሰጣቸው 115 ባለሃብቶች መካከል 72ቱ የውጭ ባለሃብቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዘርፍ ሲታይ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 84 በመቶ፣ የአገልግሎት ዘርፍ 28 በመቶ እንዲሁም ግብርና 3 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን ካፈሰሱ ባለሃብቶች መካከል ከቻይና በመቀጠል የሕንድ ባለሃብቶች ሰፊውን የኢንቨስትመንት ድርሻ መያዛቸውንም ገልጸዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከተሰጣቸው ባለሃብቶች መካከል 73 ፕሮጀክቶች ከቅድመ ትግበራ ወደ ትግበራ እንዲሁም 76ቱ ደግሞ ወደ ማምረት ተሸጋግረዋል ብለዋል፡፡

በዘንድሮው በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ኢትዮጵያ የገባው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ22 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ እንዳለው የገለጹት ኮሚሽነሯ፤ በመንግሥትና ህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት የጎላ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሃብቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም ባለፈው አንድ ወር ብቻ ከ100 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር እንዲገባ ተደርጓል ነው ያሉት።
በመሆኑም የሰላም ስምምነቱ በሥራ ላይ ላሉ ባለሃብቶች መተማመኛ ከውጭ ለሚመጡት ደግሞ የደኅንነት ዋስትና ሆኗቸዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተሟላ መሰረተ-ልማት፣ የኃይል አቅርቦት፣ ቁርጠኛ መንግሥት እንዲሁም የክትትል ሂደቱን ጠንካራ ማድረግ የሚያስችል የአንድ ማዕከል አገልግሎት ያሏት ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

See also  ኢትዮጵያ መቶ የኢንደስትሪ ፓርኮችን ልትገነባ ነው

Via OBN

Leave a Reply