Site icon ETHIO12.COM

ጎባጢት ድልድይ


በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩ ቀደምት የንግድ ማዕከላት አንዷ በነበረችው የእንፍራንዝ ከተማ እና በታሪካዊው የጉዛራ ቤተ መንግስት መካከል የጋርኖ ወንዝ ይገኛል፡፡ በቀደመው ጊዜ በዚህ ወንዝ ምክንያት የዐፄ ሰርፀ ድንግል ባለቤት እቴጌ ስነወርቅ ማርያም ከጉዛራ ወደ እንፍራዝ ልደታ ቤተክርስቲያን ለመሄድና ፀሎት ለማድረስ ይቸገሩ ነበር፡፡

ጉዛራና እንፍራዝ ከተማም በቅርብ ርቀት ማዶ ለማዶ ሆነው መተያየት ብቻ ነበር ግንኙነታቸው፤ በተለይም በክረምት ወቅት ወንዙን መሻገር የማይቻል ነበር፡፡ በመሆኑም እቴጌዋ በወንዙ ላይ ድልድይ እንዲሰራ አደረጉ፡፡

ዛሬ ድረስ ‘’ማን ያሻግረኝ ብለሽ እንዳትጨነቂ፣
በጎባጢት ድልድይ በግንቡ ዝለቂ’’ እየተባለ የሚዘፈንለት ድልድይም ተሰራ፡፡ የድልድዩ ስምም ጎባጢት ተባለ፡፡

የጎባጢት ድልድይ በዐፄ ሰርፀ ድንግል ዘመን በ1560ዎቹ የተገነባ ነው፡፡ ከ445 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው ድልድዩ ያለ አንዳች ብረት በኖራ አጣባቂነት ድንጋይን በድንጋይ በማነባበር የተሰራ ነው፡፡ የጎባጢት ድልድይ 12 ሜትር ርዝመት፣ ዘጠኝ ሜትር ቁመት፣ አራት ሜትር ስፋትና አንድ ሜትር ውፍረት አለው፡፡ ግማሽ ክብ ሆኖ መሰራቱም ከባድ መጠነ ቁሶችን ለመሸከም አስችሎታል፡፡ የወቅቱን የሀገራችን የግንባታ ጥበብ ረቂቅነት ምስጢርም አጉልቶ ያሳያል፡፡ በዚህ ረቂቅ ጥበብ በመሰራቱም ነው የጎባጢት ድልድይ ሳይታደስ የነበረውን ገጽታ እንደያዘ አሁንም ድረስ መኖሩ ምስክር ነው፡፡

ከባህር ዳር ጎንደር ከተዘረጋው አስፓልት 200 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የጎባጢት ድልድይ በስተሰሜን አቅጣጫ በጋራ የተከበበና ደቡባዊ ወሰኑ ደግሞ ለጣና ሐይቅ እጅግ የቀረበ ነው፡፡ ከቦታው የእይታ አድማሳችንን ወደ ሰሜናዊ ምስራቅ ካደረግንም ደግሞ ጥንታዊው የጉዛራ ቤተ መንግስት በውስን እርምጃዎች የሚደረስበት መስሎ በቅርብ ርቀት ይታየናል፡፡

Naky hotel
http://nakyhotel.com

Exit mobile version