Site icon ETHIO12.COM

በሩብ ዓመቱ ከወጪ ንግድ 976 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከወጪ ንግድ 976 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገለጸ።

በሩብ ዓመቱ ከ420 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ አድል መፈጠሩም ተገልጿል።

የ2015 በጀት አመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚና የዘርፎች አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በግምገማ መድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክትር ፍጹም አሰፋ፤ የሩብ ዓመቱን አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የውጭ ምንዛሬ ፍሰቱ በ14 በመቶ መጨመሩን ባቀረቡት ሪፖርት ጠቅሰዋል።

በሩብ ዓመቱ ከወጪ ንግድ ከተገኘው 976 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ውስጥ 426 ሚሊዮኑ ከግብርና ምርቶች የተገኘ ነው ብለዋል።

የማኑፋክቸሪንግና የማእድን ዘርፎች አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ቅናሽ ማሳየቱን ገልጸው ፤የአበባ ምርቶች ወጪ ንግድ ደግሞ ከፍተኛ መሻሻል ካሰዩ ምርቶች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል።

የኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ የዘርፉ ማነቆዎች መሆናቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ችግሩን ለማሻሻል እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው 67 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉንም ጠቅሰዋል።

በሩብ ዓመቱ የመንግስት ገቢ በ8 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉን ገልጸው ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ምንጮች 93 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ነው ያብራሩት።

ከዚህም 51 ቢሊዮኑ ከገቢ ግብር የተገኘ መሆኑን በመጥቀስ።

እንደ ኢዜአ ዘገባ፤ በሩብ ዓመቱ ትራንስፖርትን ጨምሮ ከአገልግሎት ዘርፍ 1 ነጥብ 2 በሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ420 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

Exit mobile version