Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ ሲያጣጥር “ተኩስ አቁሙ” ሲሉ የአሜሪካ ባለስልጣን አስፈራሩ

በሰሜን ኢትዮጵያ ያገረሸው ጦርነት በአስቸኳይ ካልቆመ ጠንከር ወዳለ እርምጃ እንደሚገቡ የአሜሪካ ባለስልጣን ተናገሩ።

የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ የተኩስ አቁም በሌለበት ሁኔታ ጦርነቱን ለማስቆም እና ለደረሱ ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖር ተጽዕኖ ይፈጥራል የተባለውን ረቂቅ ህግ ሴኔቱ እንዲያሳልፈው እገፋለሁ ብለዋል።

ሴናተሩ የጠቀሱት የአሜሪካ ሴኔት በኢትዮጵያ ሰላም እና ዲሞክራሲ ለማበረታታት ወይም ኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዲሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2021 በሚል ያወጣውን ኤስ3199 የተሰኘው ረቂቅ ሕግን ነው።

ሴናተሩ ህጉ ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት የሚያስተጓጉሉ እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ ተፋላሚ ለሆኑ ወገኖች የጦር መሳሪያ አቅርቦት በሚያደርጉ አካላት ላይ የቅጣት እርምጃ የሚወስድ ነው ብለዋል።

 “በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ ያሉ ተፋላሚ ወገኖች ሁሉ ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ፤  የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኤርትራ ቅጥረኞችን ከኢትዮጵያ እንዲያስወጡ እና በትግራይ ላይ የጣሉትን ጭካኔ የተሞላበት እገዳ እንዲያነሱ። የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ህወሓት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ሰላም ውይይቱ እንዲመለሱ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የህወሃት ባለስልጣናት ሴናተሩ ቅዳሜ መስከረም 5፣2015 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ ላይ ያሉት ነገር የለም።

የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ስምምነቱ ለአምስት ወራት ያህል ከዘለቀ በኋላ ጦርነቱ አገርሽቶ በተለያዩ ግንባሮች መካሄዱን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት ሴናተሩ አስቸኳይ የሆነ ተኩስ አቁም እንዲደረስና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲሆኑም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

“ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ በጦርነቱ፣ በረሃብ እና በህክምና እጦት በትግራይ ብቻ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ህይወት አልፏል። ለአጭር ጊዜ የቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት የበርካታ ኢትጵያውያን ህይወት አደጋ ላይ ጥሏል” ብለዋል።  

ጦርነቱን ተከትሎ የወጣው ይህ ረቂቅ ሕግ በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት፣ ሰላም እና መረጋጋትን ለመደገፍ የአሜሪካ አስተዳደር ዲፕሎማሲያዊ፣ ልማታዊ እና ሕጋዊ ምላሽ እንዲሰጥ የሚጠይቅና ይህንንም ሂደት እያደናቀፉ ያሉ አካላት ላይ አስተዳደሩ ማዕቀብ የሚጥልበትን ማዕቀፍ ለመፍጠር ማለሙንም አሜሪካ አስታውቃለች። 

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ በተቀሰቀሰው ጦርነት ላይ ጥሰቶችን ፈጽመዋል የተባሉ አካላት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ መስከረም 07/2014 ዓ.ም. መፈረማቸው ይታወሳል።

ትዕዛዙ ጦርነቱ እንዲራዘም አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን ያደናቀፉ፣ ተኩስ አቁም እንዳይደረግ እንቅፋት በመሆን በቀጥታ ተጠያቂ የሆኑ ወይም ተባባሪዎቻቸው ላይ ዕቀባ እንዲጣል የሚፈቅድ ነው።

ፕሬዝዳንቱ የፈረሙት ትዕዛዝ በዋናነት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥታት ባለሥልጣናት እንዲሁም በአማራ ክልል አስተዳደር እና በህወሓት አባላት ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ተገልጾ ነበር።

ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስጋት ነው የተባለውና ኢትዮጵያን በሚመለከት የወጣው የብሔራዊ አስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ቁጥር 14046  ባለበት እንዲቀጥል በቅርቡ መወሰኑም ይታወሳል።

“ጦርነቱ ባገረሸበትና ጥሰቶች መፈጸም በጀመሩበት ሁኔታ እስካሁን ማዕቀቦች እንዳልተጣሉ” ያወሱት ሴናተሩ አክለውም

“የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ከጦር ወንጀሎች፣ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ጋር በተያያዘ ሳይዘገይ ውሳኔ መስጠት እና ይህንን ድርጊቶች የፈጸሙ ላይ አፋጣኝ ማዕቀብ መጣል አለበት ብለዋል። በጦርነቱ ወቅት ጥሰት የፈጸሙ አካላት ያለ ምንም መዘግየት በህግ መጠየቅ አለባቸው” ማለታቸውም ሰፍሯል። 

ይህ ህግ አሜሪካ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚሰጠውን የጸጥታ ድጋፍ ከማገድ በተጨማሪ ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያደናቅፉ እና ከጦርነቱ ለማትረፍ በሚሞክሩና ለጦርነቱ ቁሳዊ ድጋፍ የሚያደርጉ ግለሰቦችና አካላት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ እንዲጣልም ያዛል። 

በተመሳሳይ ሌላ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን የተመለከተ ረቂቅ ሕግ በአሜሪካ ምክር ቤት መተዋወቁ ይታወሳል።

ይህ ረቂቅ ሕግ ኤችአር 6600 የሚባል ሲሆን በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ከግጭት ጋር ተያይዞ ለደረሱ በደሎች ተጠያቂ ናቸው በተባሉ ግለሶች ላይ ማዕቀብ መጣል ያስችላል።

እነዚህ ረቂቅ ሕጎች ኢትዮጵያውያንን የሚጎዱ እና ጦርነቱን ለማብቃት የሚደረጉትን የሰላም ጥረቶች የሚያደናቅፉ ከመሆናቸው በተጨማሪ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ሙከራዎች ናቸው በማለት የኢትዮጵያ መንግሥት አጥብቆ ተቃውሟቸው ነበር።

እንዲሁም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሕጎቹ እንዳይጸድቁ ጥረትና የተቃውሞ ሰልፎች ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሕጎቹን መጽደቅ የሚደግፉ ኢትዮጵያውያንም ግፊት አድርገዋል።

ከሰሞኑ በተጨማሪ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከንየኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት በትግራይ ውስጥ የሚያካሂዱትን “የጋራ ወታደራዊ ጥቃት” እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በትግራይ ኃይሎች በኩልም “የጠብ አጫሪነት ተግባራትን” የክልሉ ባለሥልጣናት ከመፈጸም እንዲቆጠቡ የውጭ ጉዳይ ኃላፊው አሳስበዋል።  

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫም ግጭቱ እየተባባሰ መሆኑን እና በሰው እና በንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳትን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች መውጣታቸው በጥልቅ አሳስቧታል ብሏል።

BBC Amharic

Exit mobile version