ETHIO12.COM

ጎርጎራ – የመጻዒው ዘመን ሙሽራ!

በዘመናት መካከል ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ስልጣን ርካብ የተቆናጠጡ ሁሉ ዐይናቸውን ከዚህ አካባቢ አይነቅሉም ነበር አሉ፡፡ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ አንጥረኛ እና ጥበበኛ የሆኑት ቋረኛው ንጉስ የመሪነት ጥበብ ስንቃቸውን የቋጠሩት፣ የታላቅነት ራዕይ ህልማቸውን የወጠኑት እና የልጅነት ትምህርት ጊዜያቸውን ያሳለፉት በዚሁ አካባቢ በሚገኘው ቸንከር ተክለ ኃይማኖት ገዳም ውስጥ ነበር፡፡

ለዘመነ መሳፍንት ማክተም ምክንያት ከሆኑ ቦታዎች አንዱ ነው፡፡ ከህገ ልቦና እስከ ህገ ኦሪት፣ ከንጉሰ ነገስት እስከ ወታደራዊ መንግሥት፣ ከጥንታዊው እስከ ዘመናዊው፣ ከተዘመረለት እስካልተዘመረለት የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሃገረ መንግስት ምስረታ ጉዞ ያላየውም ያላስተናገደውም የኢትዮጵያ ታሪክ የለም፡፡

ድርቡሽ ኢትዮጵያን ሊወጋ ወደ መሃል ሀገር በደንቢያ በኩል ሲገባ ንጉሰ ነገስቱም ጠላትን ለመመከት ወደቦታው አቀንተው ክፉና በጎን አይተውበታል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያዊያኑን ተዋጊዎች አጋር ማጣት ያየ ምርኮኛ ‹‹ወገራ አሳላፊ ደንቢያ እንጀራ ጣይ፤
ተበላህ ጎንደሬ አትነሳም ወይ›› ሲል መቀኘቱ የአካባቢውን አኩሪ የተጋድሎ ታሪክ ሚዛን ማሳያ ነው፡፡

በዚሁ ተዓምረኛ እና ጥበበኛ አካባቢ አፄ ሱስንዮስ ኢትዮጵያ የሮማን ሐይማኖት እንድትቀበል አዋጅ አስነግረውበትም ነበር፡፡ ግራኝ አህመድ ደንቢያን መርጦ ጣና ዳርቻ ዋና መዲናውን ለማድረግ እንዳሰበ ሁሉ፤ የእንግሊዝ ተስፋፊዎች፣ የፖርቹጋል አሳሾች፣ የሮም ቀሳውስት እና የግሪክ መልዕክተኞች ቦታውን በትኩረት አስሰውታል፡፡ ፋሺሽት ጣሊያን ደግሞ ጎርጎራን እና ማሩ ቀመስ ደንቢያን ዋና መናገሻው ለማድረግ ዳድቶት ነበር ይባላል፡፡

አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራም የዮዲት መዲና ደንቢያ ነበር ብለውናል፡፡ ሐማሴኖች ትናንታችን ደንቢያ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፤ የዘር ሃረጋቸው ከዚሁ ስፍራ ይመዘዛልና፡፡ ደንቢያ ተረከዙ ተከዜንም አልፎ ከሃማሴን ዘር እንደ ሀረግ ይማዘዛል፡፡ ‹‹አትውረድ አላልኩም ከአዘዞ በታች፤ ደንቢያ ከብት ያለምዳል እንኳን የሰው ልጅ›› እንዲል የጎንደር አዝማሪ ደንቢያ በውኃ ያጠምቃል፤ በፍቅር ያጠልቃል፡፡

የጣና ሃይቅ ወደብ፤ የደንቢያዎች መደብ የሆነችው ጎርጎራ ከረጂም ዘመን ጀምሮ በዋሻዎቿ የሰው ልጅ ይኖርባት እንደነበር ቢነገርም እንደ ቋሚ መቀመጫነት የተመሰረተችው ግን በአፄ አምደፅዮን ዘመነ ንግስና ከ700 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ የአካባቢውን ደህንነት ለማስጠበቅ ወደ ቦታው ያቀኑት ንጉሱ ፀጥታዋን አስከብረው፣ ደብረ ሲና ማሪያምን አቋቁመው እና ሕዝቡን በአካባቢው አጽንተው እንደተመለሱ ታሪክ ይነግረናል፡፡

የጎርጎራ ውበት፤ የደንቢያ በረከት የማረካቸው ከአፄ አምደ ፅዮን እስከ ሰርፀ ድንግል፤ ከአፄ ፋሲል እስከ አፄ ሱስንዮስ፤ ከግራኝ አህመድ እስከ ፋሺሽት ጣሊያን፣ ከአፄ ኃይለ ስላሴ እስከ ኮሎኔል መንግስቱ በጎርጎራ አሻራቸውን አሳርፈው አልፈዋል፡፡ የጣሊያን የመቆጣጠሪያ ማማ እና የጀልባ ጥገና፣ የጃንሆይ የጦር ሰፈር እና ትምህርት ቤት እንዲሁም የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም መዝናኛ ማዕከል ለጎርጎራ የተበረከቱ ገጸ በረከቶች ነበሩ፡፡

ከጎንደር እስከ ባሕር ዳር፣ ከጣና ገዳማት እስከ ጉዛራ ቤተ መንግስት፣ ከአላጥሽ እስከ ስሜን ብሔራዊ ፓርክ፣ ከደብረ ሲና እስከ ገሊላ፣ ከአትማረኝ የተራራ ሰንሰለት እስከ ሱስንዮስ ቤተ መንግስት፣ ከፈረስ ግንብ እስከ ጉርአምባ፣ ከታሪካዊው አንጋራ ተክለ ሐይማኖት እስከ ማንዳባ ገዳም፣ ከሞሶሎኒ ሐውልት እስከ ቸንከር ተክለ ሐይማኖት ጎርጎራ ለቱሪስት መዳረሻ ቀለበት የሆነች ወደብ ናት፡፡

ከኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም የስልጣን ዘመን ማክተም በኋላ የጎርጎራ ወደብ የመረሳት ዘመን ሆነ፡፡ እንግዶች ለእረፍት፤ መሪዎች ለስክነት የሚመርጧት ጎርጎራ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ አስፈሪ የጽሞና ጊዜያትን አሳለፈች፡፡ እንግዲህ “ለሁሉም ጊዜ አለው” እንዲል መጽሃፍ የመጻዒው ዘመን ሙሽራ የሆነችው ጎርጎራ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ያለፉትን ሁለት ዓመታት በግንባታ አሳልፋለች፡፡

ከሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሚኒስትሮቻቸው ጉብኝት ደግሞ የገበታ ለሀገር አንድ አካል የሆነው የጎርጎራ ፕሮጀክት አፈጻጸሙ በጥሩ ሂደት ላይ ነው ተብሏል፡፡ የወጡ ፎቶዎችም የፕሮጀክቱን መልካም አፈጻጸም የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ቀጣዩ የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግሩ፣ ሀገርን እና ታሪክን የሚጠቅሙ ሌሎች መዳረሻዎችን በባለሃብቶች፣ በክልሉ መንግስት እና በፌደራል ፕሮጀክቶች እንዲለሙ ጎርጎራ መልካም ምሳሌ ትሆናለች ብለን እናስባለን፡፡

(ከማሻሻያ ጋር በድጋሜ ተዘጋጅቶ የቀረበ) (አሚኮ)

Exit mobile version