አቡን ማትያስ [አባ ተክለማርያም አስራት] እንዴት እንመናቸው?

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚናፈሰው ማናቸውም ነገር ፈጥኖ ሱዳን ስለሚደርስ፣ አባ ተክለማርያም ሱዳን ሄደው በቀድሞ ሥማቸው ብፁዕ አቡነ ማትያስ እየተባሉ ወደ ኢትዮጵያ ደርግን የሚያዳክም የራድዮ ፕሮግራም በይፋ ማስተላለፍ ከመጀመራቸው በፊት፣ የፖለቲካ ስበዕና ሊያላብሳቸው የሚችል የፕሮፓጋንዳ ሥራ ….. የዛሬው አቡነ ማትያስ፣ በማናቸውም ታዋቂ የአብነት ትምህርት ቤት ያስመሰከሩት ልዩ የክህነት ሞያ እንዳልነበራቸው፣ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት አባ ሃብተማርያም ወርቅነህ (ማለትም፣ የአሁኑ አቡነ መልከፀዴቅ) በካቴድራሉ ለሚያገለግሉ ካህናት አቋቁመዉት በነበረ ትምህርት ቤት በትርፍ ጊዜያቸው እየተማሩ 5ኛ ክፍል ደርሰው እንደነበር፣ እብራይስጥና ዐረብኛን ጨምሮ የተለያዩ የውጭ ሀገር ቋንቋዎች ይናገራሉ ቢባልላቸውም ኢየሩሳሌም በነበሩት ዘመን ከውጭ ሰዎች ጋር ሐሣብ ይለዋወጡ የነበረው በሾፌራቸው አስተርጓሚነት እንደነበር

(ዐይናለም ግዛው ፡- ከኢየሩሳሌም) ይህን ተጭነው ዋናውን ጽሁፍ ያንብቡ

ማሳሰቢያ፦

ይህ ጽሑፍ በመጀመሪያ ዋሽንግተን ዲ.ሲ. ለሚገኘው የነፃነት ለኢትዮጵያ ራድዮ የተላከው በእኔ ሥም ቢሆንም፣ በኀብረት ያዘጋጀነው ግን ጉዳዩ የከነከነንና ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች የምንገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ከርስቲያን ምዕመናን(ት) ነን፤ ስለሆነም፣ ይህ ዘገባ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ፣ በታላቋ ብሪታንያ፣ በጀርመን፤ በእሥራኤል፣ በስዊትዘርላንድና በዩ. ኤስ. አሜሪካ ከሚገኙ የመረጃ ምንጮች ጋር በመተባበር ነው፡፡ በዘገባው ውስጥ
የተካተቱት ጉዳዮች ሁሉ በአዲስ አበባዎቹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ በደህንነት ጥበቃው መ/ቤትና በጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት፣ እንደዚሁም ደግሞ ቀደም ብለው በተጠቀሱት ስድስት ሀገሮች ውስጥ ከሚኙት የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በተጨማሪ፣ በኢየሩሳሌሙ የመንበረ ጳጳስ ግቢ ቤተ መዘክርና በቆንስላው ጽ/ቤት በሥርዓት ተመዝግበው የተቀመጡ ናቸው፤ በኢየሩሳለሙ የመንበረ ጳጳስ ግቢ የነበረውን ማስረጃ ለማጥፋት አቡነ ማትያስ ዕድል ተሰጥቷቸው ነበር ቢባል እንኳን፣ በሌሎቹ ዘንድ ያሉትን ሊደርሱባቸው ካለመቻላቸውም በላይ በህይወት ያሉ የቃል ምሥክሮችም ጥቂት አለመሆናቸው ሊታወቅ ይገባል ።(ዐ.ግ.)

አባ ተክለማርያም አስራት፣ ማለትም የዛሬው አቡነ ማትያስ፣ በሕ.ወ.ሓ.ት. ለፓትርያርክነት መታጨታቸው እንዳልባሌ ወሬ ለጥቂት ወራት ሲናፈስ ከቆዬ በኋላ ዕውን በመሆኑ፣ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በሚያሳስባቸው የቤተ ክርስቲያኗ ካህናትና መዕመናን ዘንድ እጅግ አነጋጋሪ ሆኗል፤ ከሃያ ዓመታት በላይ የሀገር ዉሰጥና የስደት ቅዱሳን ሲኖዶሶች በሚል ፈሊጥ ጎራ ፈጥረው በመወጋገዝ የተለያዩት ቅዱሳንና ብፁዓን አባቶች፣ ሰጥቶ በመቀበል መርህ እርቀ ሰላም ለመፍጠር ተወካዮቻቸውን በዩ. ኤስ. አሜሪካ የቴክሳስ ክልል ውስጥ ወደምትገኘው የዳላስ ከተማ ልከው በውይይት ላይ እያሉ ለ6ኛው
ፓትርያርክ ምርጫ አዲስ አበባ በይፋ አስመራጭ ኮሚቴ መሰየሙ ብቻ ሳይሆን፣ ፕረዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በሕ.ወ.ሓ.ት. ተጽዕኖ እራሳቸውን ነቅፈው የጻፉትን ደብዳቤ እንዲሽሩ መገደዳቸውና ዕርቅ ፈላጊ የነበሩትና ልዑካንም ያሰማሩት አቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤልም ሸምጥጠው አቋማቸውን እንዲለውጡ መደረጉ፣ የሕ.ወ.ሓ.ት. ጫና ምን ያህል አግጥጦ ረዕሰ ብሔሩንና አቃቤ መንበረ ፓትርያርኩን እስከማርበደበድ መድረሱን የተረዳው ሕዝበ ክርስቲያን አገዛዙ ቤተ ክርስትያኗን ለማሽመድመድ ታጥቆ መነሳቱን ተገንዝቧል።.

ሶስተኛው ፓትሪያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፤ ዓለም ፍጹም የናቁ ፓትርያርክ የባሕታዊ ልብሴን አልለውጥም፣ ጫማ አላደርግም፣ በወርቅና ፈርጥ የተብረቀረቁ መስቀሎችን በደረቴ ላይ አልደረድርም ብለው፣ በአደባባይ ደምቀው እንዲታዩ ሊያደርጓቸው የሚችሉትን ነገሮች ሁሉ አሻፈረኝ ስለአሉና እንዲተባበሩ ሲጠየቁ የሚሰጡት ምላሽም “አታስጨንቁኝ! እምቢ ካላችሁኝ ወደ ምናኔየ እመለሳለሁ!” ማለታቸው ይታወስላቸዋል።


በዚህ ላይ ደግሞ፣ ቀደም ሲል “የዐማራንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ በተ ክርስትያንን የጀርባ አጥንት ሰብረናል” ብለው ሲፎክሩ የተደመጡት አንጋፋው የሕ.ወ.ሓ.ት. ሰው አቶ ስብሃት ነጋ፣ “ለዕርቀ ሰላም ድርድሩ ልዑካንን ወደ አሜሪካ የላኩት ሰዎች መሰቀል ይገባቸዋል!” ብለው በአደባባይ መናገራቸው፣ ሕ.ወ.ሓ.ት. ከምሥረታው አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በተ ክርስትያን አዳክሞ የኢትዮጵያዊነት ማገርነቷን ለማምከን በመጣር ላይ የመሆኑ ማረጋገጫ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና ዕምነት ተከታዮች ይህን ሐቅ ከተረዱት ዓመታትን አስቆጥረዋልና እንግዳ ክስተት ሊሆንባቸው አይችልም። ስለሆነም፣ ለዚህ ዘገባ ቅንብር የተባበሩንና ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙት የመረጃ ምንጮቻችን አቡነ ማትያስን የሚኮንኑት፣ ሕ.ወ.ሓ.ት. የትግራይ ተወላጅነታቸውን መስፈርት አድርጎ “ብፁዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት” በማሰኘት ለዚህ እጅግ በጣም የተከበረ መንፈሣዊ መንበር ከማብቃቱ ይልቅ፣ አቡነ ማትያስ ከ1967 ዓ.ም. ወዲህ ብቻ በነበረው የህይወት ዘመናቸው የፈጸሟቸው ከአንድ መነኩሴ የማይጠበቁ ነውሮችና የሥነ-ምግባር ጉድለቶች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያንን በጣም የሚያዋርድና የመንፈሣዊንትንም ይዘት እጅግ የሚያዘቅጥ ሆኖ ስላገኙት መሆኑን ያሰምሩበታል።


ሕ.ወ.ሓ.ት. የአቡነ ማትያስን ፓትርያርክነት በሚቆጣጠራቸው የብዙሃን መገናኛዎች ሲያውጅ፣ ለራስ ሲቆርሱ – አያሳንሱ እንዲሉ፣ ያልተማሩትን እንደ ተማሩና ያልሆኑትን እንደሆኑ አድርጎ አለሃፍረት በአደባባይ መካቡን የታዘቡት እነዚህ ምንጮቻችን፣ አዲስ አበባ በሚገኘው የመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተራ ቀዳሽ የነበሩት አባ ተክለማርያም አሥራት፣ማለትም የዛሬው አቡነ ማትያስ፣ በማናቸውም ታዋቂ የአብነት ትምህርት ቤት ያስመሰከሩት ልዩ የክህነት ሞያ እንዳልነበራቸው፣ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት አባ ሃብተማርያም ወርቅነህ (ማለትም፣ የአሁኑ አቡነ መልከፀዴቅ) በካቴድራሉ ለሚያገለግሉ ካህናት አቋቁመዉት በነበረ ትምህርት ቤት በትርፍ ጊዜያቸው እየተማሩ 5ኛ ክፍል ደርሰው እንደነበር፣ እብራይስጥና ዐረብኛን ጨምሮ የተለያዩ የውጭ ሀገር ቋንቋዎች ይናገራሉ ቢባልላቸውም ኢየሩሳሌም በነበሩት ዘመን ከውጭ ሰዎች ጋር ሐሣብ ይለዋወጡ የነበረው በሾፌራቸው አስተርጓሚነት እንደነበር አስታውሰው፣ በዕውቀት የማይታሙት የአቡነ ማትያስ ዋና መታወቂያ ሆነው የዘለቁት የተንዠረገገው ጺማቸው፣ዠርጋዳ ቁመናቸው እና አለባበሳቸው ብቻ እንደነበሩ አብራርተዋል፡፡ የተንዠረገገው ጺማቸው የአራት ኪሎንና የግንፍሌን ሕፃናት ይስብ ስለነበር፣ አባ ተክለማርያም በእግራቸው ሲነጉዱ “አባ ጽሕማ” እያሉ ሕፃናት ሲከተሏቸው ይሰማቸው የነበረውን እርካታ የሚያውቋቸው አልዘነጉትም።


የአባ ተክለማርያም አሥራት ተክለ-ሰውነት ከይዘት ይልቅ በቅርጽ ተሸፍኖ ትኩረት ይስብላቸው እንድነበር የሚያስታውሱት የቀድሞ የሥራ ጓደኞቻቸው፣ የኢትዮጵያ አብዮት በተቀጣጠለበት ወቅት በአድማ ሥራ እያቆሙ ለወታደራዊው ደርግ የተበደለናል አቤቱታ ማቅረብ የተለመደ ስለነበር፣ የቅድስት ሥላሴ ካህናትና ዲያቆናት ተሰልፈው ወደ ደርጉ ጽሕፈት ቤት በመሄድ እበሩ ላይ ዘብ አስቁሟቸው እያለ የደርጉ የዘምቻ መምሪያ ኃላፊ፣ ኮሎኔል ዳንኤል አስፋው፣ በመኪናቸው ብቅ ሲሉ አባ ተክለማርያምና ሌሎች የሥራ ጓደኞቻቸው የኮሎኔሉን መኪና ከብበው በመጮኻቸው፣ ኮሎኔሉ አባ ተክለማርያምና ሌሎች ሁለት ካህናትን በመምረጥ እቢሯቸው
ገብተው እንዲያነጋግሯቸው ስለአደርጉ፣ ያች ዕለት የአባ ተክለማርያም አስራትን ህይወት እንደለወጠች የመረጃ ምንጮቻችን በአግራሞት ያስረዳሉ፤ በዚያች አጋጣሚ አባ ተክለማርያም አስራት፣ ማለትም የአሁኑ አቡነ ማትያስ፣ ከኮሎኔል ዳንኤል አስፋው ጋር ተዋውቀውና ተቀራርበው እደርጉ ጽሕፈት ቤት እንደልባቸው መግባትና መውጣት ችለው እንደነበርም በመዘርዘር ይገልጣሉ፡፡


ወታደራዊው ደርግ “ኢትዮጵያ ትቅደም” በሚል ርዕስ የነደፈውን ዓላማ ለማብራራት እና ሀገር ለማረጋጋት በ1969 ዓ.ም. ”የሰላም ልዑካን” የተባሉ ቡድኖችን እያደራጀ በወቅቱ ወደ ነበሩት የኢትዮጵያ 14 ክፍለ- ሀገራት ሲያሰማራ፣ አባ ተክለማርያም አስራት በኮሎኔል ዳንኤል አማካይነት በደርጉ ዘንድ ባተረፉት ዕውቅና “ተራማጅ ካህን” ተብለው የደርጉ የእስረኞች ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ በነበሩት በሻለቃ ካሣዬ አራጋው መሪነት ወደ ጎንደር ክፍለ ሀገር የዘመተው የሰላም ሐዋርያት ቡድን አባል ሆነው በመሰማራትና “የጎንደር ሕዝብ ሆይ! ጊዜያዊው ወታደራዊ መንግሥት የወረሳቸውን ችግሮች በመፍታት ላይ ስለሚገኝ ፋታ አግኝቶ ገና ምንም አላደረገልህ ይሆናል፣ ግን ምን አሳጣህ?” የሚል ይዘት የነበረው ቅስቀሳ በሄሊ-ኮፕተር እየተዘዋወሩ ስለአካሄዱ ከወታደራዊው ደርግ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር መቻላቸውን እነዚሁ የመረጃ ምንጮቻችን ይዘክራሉ፡፡


በሌላ በኩል ደግሞ፣ በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በነበሩት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስና በወታደራዊው አስተዳደር ደርግ መካከል የተፈጠረው ቅራኔ እየተካረረ ሄዶ፣ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀደም ሲል በእንደራሴነትና በኋላም በፓትርያርክነት ለበርካታ ዓመታት የመሩትን ተወዳጅ፣ ባለውለታ፣ ምስጉንና ታላቅ መንፈሣዊ አባት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ወታደራዊው ደርግ በታላቅ ድፍረትና ጭካኔ ዓለም-አቀፍ ዕውቅና ከነበረው ክቡርና ቅዱስ መንበራቸው አውርዶ ሲያስራቸው፣ በምትካቸው አባ መላኩ ይባሉ የነበሩትና በደቡብ ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌል በመስበክ፣አብያተ ክርስትያናትን በማሳነፅ፣ ትምህርት ቤቶችን በማቋቋምና የተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራትን በማከናወን የሚታወቁት ባሕታዊ አባት ተመርጠው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት በመባል በፕትርክናው መንበር መንበር ላይ ከተሰየሙ በኋላ፣ እኚህ ይህን ዓለም ፍጹም የናቁ ፓትርያርክ የባሕታዊ ልብሴን አልለውጥም፣ ጫማ አላደርግም፣ በወርቅና ፈርጥ የተብረቀረቁ መስቀሎችን በደረቴ ላይ አልደረድርም ብለው፣ በአደባባይ ደምቀው እንዲታዩ ሊያደርጓቸው የሚችሉትን ነገሮች ሁሉ አሻፈረኝ ስለአሉና እንዲተባበሩ ሲጠየቁ የሚሰጡት ምላሽም “አታስጨንቁኝ! እምቢ ካላችሁኝ ወደ ምናኔየ እመለሳለሁ!” የሚል ግትር አቋም ስለነበረ፣ በወቅቱ ደርጉንገጥሞት የነበረውን ተግዳሮት ምንጮቻችን ያብራራሉ።


በአደባባይ ሕዝባዊ ስብሰባዎች ሲካሄዱ ከደርጉ ሊቃነመናብርት ቀኝና ግራ በሚገኙት ወንበሮች ላይ ፓትርያሪኩን እና የሚስሊሙን ማኅበረሰብ መሪ ማስቀመጥ በዘመኑ የፕሮቶኮል ደንብ ሆኖ ስለነበር፣ የፓትርያሪክ ተክለሃይማኖትን አቋም ማስለወጥ ካልተቻለ፣ ፓትርያርኩ በሕዝባዊ ስብሰባዎችና የውጭ ሀገር እንግዶች በሚግኙባቸው መድረኮች ላይ ሲገኙ ግርማ ሞገስ ሊያላብሳቸው የሚችል ዘዴ የቤተ ክህነት ጉዳይ ጊዜአዊ ጉባኤ ሰብሳቢ በነበሩት በዶክተር ክነፈ እርግብ አማካኝነት ተጠንቶ እንዲቀርብለት ደርጉ ማዘዙን የሚያስታውሱት የመረጃ ምንጮቻችን፣ ዶክተር ክነፈ እርግብ በኮሚቴ አስጠንተው “በትረ-ፕትርክናቸውን ይዞ የሚከተላቸውና በአደባባይ ሲቀመጡ ረዳታቸው መሆኑን በሚያረጋግጥ ሁኔታ ከኋላቸው እየቆመ የሚያደምቃቸው ግርማ ሞገስ ያለው መነኩሴ ተመርጦ በአቡነ ቀሲስነት ቢመደብላቸው፣ ፓትርያርኩ ከአቡነ ቀሲሳቸው በእጅጉ ኢንደሚበልጡ ስለሚታወቅ በተዘዋዋሪ ግርማ ይጎናጸፋሉ” የሚል ሐሣብ ስለአቀረቡ፣ ከኮሎኔል ዳናኤል አስፋው ጋር ፈጥረውት በነበረው ቅርበት በደርግ ጽ/ቤት በተራማጅ ካህንነት የሚታወቁት፣ የደርጉን ፍላጎት በፓትርያሪኩ ዘንድ ያስፈጽማሉ ተብለው የታመነባቸው፣ አለባበሳቸው፣ ቁመናቸውና ጺማቸው የእነዶክተር ክንፈ እርግብን መስፈርት የሚያሟላው አባ ተክለማርያም፣ የዛሬው አቡነ ማትያስ፣ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት አቡነ ቀሲስ ሆነው እንዲመደቡ ወታደራዊው ደርግ ለዶክተር ክነፈ እርግብ በሰጠው መመሪያ መሰረት አባ ተክለማርያም አስራትከ1970 ዓ.ም. ጀምሮ ለ3 ዓመታት ያህል ፓትርያርክ ተክለሃይማኖትን በአቡነ ቀሲስነት ማገልገላቸውን ዘርዝረው ያስረዳሉ፡፡


ይህ በዚህ እንዳለ፣ በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ማቴዎስ፣ በቅድሚያ ደርግ አለፍርድ የቀዳማዊ ኃለሥላሴን ባለሥልጣኖች መረሸኑን በመቃወም ድምፃቸውን ስላሰሙ፣ ቀጥሎም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በግፍ ሲገደሉ በኢየሩሳሌም ጸሎተ ፍትሐት ስላደረጉ እና በኋላም በነጭና በቀይ ሽብር ስም የተፈጸመውን እልቂት ስለአወገዙ፣ ከኢየሩሳሌም ይነሱ ዘንድ ደርግ ቅዱስ ፓትርያሪኩን ሲያሳስብ መቆየቱን የሚያስታውሱት ምርጮቻችን፣ የሸዋ ተወላጅ የሆኑት አቡነ ማቴዎስ አላስኖር አሉን!” የሚል አቤቱታ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የትግራይ መነኮሳት ለደርጉ በመላካቸው፣ደርግ አቡነ ማቴዎስ ይነሱ ዘንድ በፓትርያሪክ ተክለሃይማኖት ላይ የሚያደርገውን ግፊት እያከረረ ስለሄደና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖትም የትግራይ መነኮሳቱ አቤቱታ በጎ ምላሽ ማግኘት እንደሚገባው ስለአመኑበት፣ በዚያን የቀይ ሽብር ደርጊት በቀዘቀዘበተና ከሶማሊያ ጋር የተደረገው ጦርነትም ተገባድዶ አንፃራዊ መረጋጋት በተፈጠረበት ወቅት ከኢየሩሳሌም መንበራቸው የተነሱት ብፁዕ አቡነ ማቲዎስ፣ በግዞት መልክ በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የበላይ እልቅና ተወስነው አዲስ አበባ እንዲቀመጡ ሲደረግ፣ በምትካቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት በቅርብ ሲያገለግልኝ አውቄዋለሁ ብለው የተማመኑባቸውን አባ ተክለማርያም አሥራትን በአንብሮተ ዕዳቸው ከተራ ምንኩስና ሊቀ ጳጳስ አድርገው ሾመውና ብፁዕ አቡነ ማትያስ ብለው ወደ ኢየሩሳሌም የላኩበትን ሁኔታ ያብራራሉ፡፡

See also  ከአማራ ክልል ብጥብጥ ጀርባ "የኦርቶዶክስ እምነት"ለምን? ደወል የሚስደውሉ አባቶችን ማን ነው የሚመራቸው፣ የሻዕቢያ ዝምታስ?


ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ዘመን “ማዳም ክርስቲያን ፔደርስን” የሚባሉ የዴንማርክ ተወላጅ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ብትሄጂ ዕውነተኛ ክርስቲያን የሆኑ ጥቁሮችን ታገኛለሽ፣ የሚል መንፈስ መርቶኝ መጣሁ! ብለው ከአቡነ ማቴዎስ ጋር መገናኘታቸውን የሚያወሱት እነዚሁ ምንጮቻችን፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ እኚህን ዴኒሽ ወይዘሮ ኢየሩሳሌም በሚገኘው መንበረ ጳጳስ ውስጥ የሚገኘውን ቤተ መጻሕፍት እና ቤተ መዛግብት እያደራጁ ስለ ኦርቶዶክስ ክርስትናም ትምህርት እንዲከታተሉ ካደረጓቸው በኋላ ፣እማሆይ አብርሃም ብለው እንዳመነኮሷቸው በማስረዳት፣ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስን ተክትው ኢየሩሳሌም ሲገቡ በመንበረ ጳጳሱ ግቢ ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን እምሆይ አብርሃምን ስለአገኟቸው እና የግንኙነታቸው ባሕሪ ከዕለት ወደ ዕለት መልኩን እየለወጠ አብረው እስከ ማደር ደርሰዋል የሚል ክስ በኢየሩሳሌም ከሚኖሩ መነኮሳት ወደ ፓትርያሪክ ተክለሃይማኖት ስለተላከ፣ ከሁለት ዓመታት በላይ በአቡነ ማትያስ ላይ ይቀርቡ የነበሩ ሌሎች አቤቱታዎችን ችላ ብለው የቆዩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ ተክለሃይማኖት፣ ይህን ከአንድ ጳጳስ የማይጠበቅ አስነዋሪ ድርጊት በዝምታ ማለፍ ባለመፍቀዳቸው፣ አቡነ ማትያስ ከኢየሩሳሌም ተጠርተው ለቅዱስ ሲኖዶስ ማብራሪያ እንዲሰጡ ማዘዛቸውን ያስታውሳሉ።

አባ ማቲያስ ከፊት ከቆሙት በስተግራ ያሉት ሪዛም ናቸው። ጎንደር ለቅስቀሳ ከደርግ አመራሮች ጋር ባመሩበት ወቅት የተነሱት ፎቶ ነው


ይህ የጥሪ ማዘዣ የደረሳቸው አቡነ ማትያስ ምላሽ ለመስጠት ከመታቀባቸው ባሻገር፣ የአደባባይ ምሥጢር የሆነውን ጉዳይ በአካል አዲስ አበባ ተገኝተው ለቅዱስ ሲኖዶሱ ማስተባበያ ለማሰማት መከጀል ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ ስለአወቁት፣ ከኢየሩሳሌም ወደ ሌላ ሀገር ለመኮብለል ይታደጓቸው ዘንድ የተማጸኑት ቀድሞ እሥራኤል ሀገር ተምረው ኢየሩሳሌም በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጸሐፊና በኋላም ቆንስል የነበሩትን፣ ከዚያም በናይጀርያ አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ለምክክር ቢጠሩ ፈርተው ወደ እሥራኤል በመሰደድ በአንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሎጂስቲክስ ክፍል ውስጥ ይሠሩ የነበሩትን አቶ ዮፍታሔ ዲሜጥሮስን እንደነበር የሚገልጡት እነዚሁ የመረጃ ምንጮቻችን፣ አቶ ዮፍታሔ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ አንድነት (EPDA) የሚባል ድርጅት ሱዳን ሀገር፣ ኡምዱርማን በሚባል ከተማ ውስጥ ከሚገኝ ራድዮ ጣቢያ ወደ ኢትዮጵያ ፕሮግራም ማስተላለፍ ስለጀመረና እርስዎም መንፈሣዊ የቅስቀሳ ፕሮግራም እያዘጋጁ ለማስተላለፍ ፈቃደኛ ከሆኑ ድርጅቱ ሊቅጥርዎት ይችላል የሚል ተስፋ ስለሰጧቸው፣ ውጥናቸውን ሾፈራቸው ለነበሩት ለአቶ ሙሴ ተገኝ፣ አሁን ዶክተር ወይም ፕሮፌሰር፣ ብቻ አጋርተው በምሥጢር ጓዝ መቀርቀብ
ስለጀመሩ፣ ወሬው አፈትልኮ አዲስ አበባ ሊደርስ መቻሉን ምንጮቻችን ያስረዳሉ። መነኮሳቱ የአቡነ ማትያስን ኩብለላ እንደ ግልግል ቢቆጥሩትም፣ ወሬውን ወደ ሀገር ቤት ለማዝለቅ የተገደዱት በመንበረ ጳጳሱ ግቢ በሚገኘው ቤተ መዛግብትና ግምጃ ቤት ውስጥ የሚገኙትን ብርቅዬ ንዋያተ ቅዱሳን እና ሌሎች የተከበሩ ቅርሶች በትልቅ ኮንቴይነር (container) ማጨቅ መጀመራቸው ስለተደረሰበት መሆኑንም አያይዘው ጠቁመዋል።


(በነገራችን ላይ አቶ ዮፍታሔ ዲሜጥሮስ የሥምጥሩው የኢትዮጵያና የኤርትራ አንድነት አርበኛ እና በምክትል ሚኒስትር ማዕረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤት ክርስትያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ታላቅ መንፈሣዊ አባት የንቡረ-ዕድ ዲሜጥሮስ ልጅ ሲሆኑ፣ ዛሬ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዋና ጸሐፊ ሆነው በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ይታውቃል) ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ተክለሃይማኖት፣ አቡነ ማትያስ ለመኮብለል ዝግጅት መጀመራቸውን እንደተረዱ፣ በወቅቱ የቤተ ክህነት ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪስጅ የነበሩት ሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛው፣ ሁለት ጳጳሳት የነበሩበትን ቡድን በመምራት፣ ኢየሩሳሌም ድረስ ሄደው ሁኔታውን በማጣራት ዘገባ እንዲያቅርቡ ስለላኩ፣ ቡድኑ ኢየሩሳሌም ሊገባ አንድ ቀን ሲቀረው አቡነ ማትያስ የኩብለላው ተባባሪ የነበረውን ሾፌራቸውንና አስተርጓሚያቸውን አቶ ሙሴ ተገኝንና ዘመዶቼ ናቸው ያሏቸውን ሁለት ሴት መነኮሳይያት አስከትለውና አብሯቸው በአይሮጵላን ሊሳፈር የሚችለውን ጓዝ ይዘው በገዳማቱ ገንዘብ ወደ ግሪክ በአይሮጵላን ሲበርሩ፣ከበድ ያለውን በኮንተይነር የተቀረቀበ የገዳም ንብረት ደግሞ በመርከብ ይከተላቸው ዘንድ ለእሥራኤል የመርከብ ድርጅት (Israeli Shiping Lines) አስረክበው ኖሮ፣ የገዳማቱ መነኮሳት በኢትዮጵያውያን አይሁዶች ታግዘው ባቀርቡት አቤቱታና በእሥራኤል ፖሊስ ትብብር ከሃይፋ ወደብ (Haifa Port) ከሻንጣዎቻቸው የተረፈውንና በመጠን አብዛኛ የነበረውን የገዳማቱን ሃብት ማትረፍ መቻሉን በትንቅንቁ ተሳታፊ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን አንደበት መስማት ተችሏል።


ይህ በዚህ እንዳለ፣ አቡነ ማትያስ በኮበለሉ ማግሥት በሊቀ መምራን አበባው ይግዛው ተመርቶ ኢየሩሳሌም የደረሰው የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዑካን ቡድን፣ በተሰጠው መመሪያ መሰረት ጠቅላላ ሁኔታውን አጣርቶ በአቡነ ማትያስ ላይ የተነገረው ድክመት መሰረት ያለው መሆኑንና ሌሎች የወንጀል ተግባራትም መፈጸማቸውን በመዘርዘር ዘገባውን ስለ አስደመጠ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ ተክለሃይማኖት ቅዱስ ሲኖዶሱን ሰብስበው በጉዳዩ ላይ የሐሣብ ልውውጥ ከተደረገ በኋላ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ብፁዕ አቡነ ማትያስን አውግዞ ጵጵስናቸውንም እንደሻረ የሚገልጹ የሰነደና የሰው ማስረጃዎች በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ብቻ ሳይሆን በግለሰቦች እጅም ይገኛሉ።ስለሆነም፣ አቡነ ማትያስ በነውረኛ ተግባራቸው ተጋልጠው በውግዘት ከጵጵስናቸው የተሻሩ ካህን ስለነበሩ፣ ግፋ ቢል በቀድሞ የምንኩስና ሥማቸው “አባ ተክለማርያም አስራት” መባል ሲገባቸው፣ የጵጵስና ማዕረግ ልብስ አጥልቀው “ብፁዕ አቡነ ማትያስ” እባላለሁ በማለት ዓመታትን ማስቆጠር መቻላቸው ለሕዝበ ክርስትያኑ ብቻ ሳይሆን ለቤተ ክርስትያኒቱ ቀኖና ጭምር ያላቸው ንቀት መግለጫ ነው የሚሉ ካህናትና ምዕመናን ጥቂት አይደሉም።


በግሪክ ወደተጀመረው የአባ ተክለማርያም አስራት የስደት ጉዞ ስናቀና ደግሞ፣ የመረጃ ምንጮቻችን የሚያረጋግጡት አባ ተክለማርያም ተወግዘው ከጵጵስና ማዕረጋቸው መውረዳቸውን እሳቸውም ሆኑ የኢሕዴአ (EPDA) ተወካዮች የሰሙት አቶ ዮፍታሔ ዲሜጥሮስ ባመቻቹት መሰረት በቀጣሪና በተቀጣሪ መካከል ግሪክ ዉስጥ ግንኙነት ከመደረጉ በፊት እንደነበር ያሚያስታወሱት የመረጃው ምንጮቻችን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚናፈሰው ማናቸውም ነገር ፈጥኖ ሱዳን ስለሚደርስ፣ አባ ተክለማርያም ሱዳን ሄደው በቀድሞ ሥማቸው ብፁዕ አቡነ ማትያስ እየተባሉ ወደ ኢትዮጵያ ደርግን የሚያዳክም የራድዮ ፕሮግራም በይፋ ማስተላለፍ ከመጀመራቸው
በፊት፣ የፖለቲካ ስበዕና ሊያላብሳቸው የሚችል የፕሮፓጋንዳ ሥራ መካሄድ ስለሚኖርበት፣ የድርጅቱ አባል እሆኑት አቶ ዮሐንስ መሸሻ ዘንድ ለንደን ሄደው በመቀመጥ መመሪያ እንዲጠባበቁ ተደርጎ እንደነበር አስርድተዋል።


በዚህ መሰረት የመጀመሪያው የኢሕዴአ የፕሮፓጋንዳ ሥራ፣ በድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በሻምበል አስራት ደፈረሱ “አውግዣለሁ” በሚል ርዕስ በአቡነ ማትያስ ሥም ተደርሶ የተሰራጨው ጽሑፍ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በማስታወቂያ ሚኒስቴር አርማ “ጥብቅ ምሥጢር” የሚል ማኅተም ተደርጎበት በሻምበል አስራት ተደርሶ በየስፍራው የተበተነው ሌላ ጽሑፍ ስለነበር፣ ሁለቱንም በጳጳስ ተብዬው ሥም ሻምብል አስራት የደረሷቸውን ጽሑፎች ከመረጃ ምርጮቻችን አግኝተን ለመመልከት ችለናል። የመጀመሪያው ጽሑፍ ዓላማ የአባ ተክለማርያምን ዘማዊነትና ከኢየሩሳሌም የኮበለሉበትን አሳፋሪ የወንጀል ድርጊት ሸፍኖ፣ ጳጳስ ተብዬው የደርግን ኢሰብአዊ ድርጊቶች በመቃወምና በማውገዝ የኢየሩሳሌሙን የሊቀ ጵጵስና መንበራቸውን በገዛ ፍላጎታቸው ለቅቀው ደርግን ለመታገል መሰደዳቸውን ማብሰር ሲሆን፣ የሁለተኛው ጽሑፍ ዓላማ ደግሞ ሃይማኖት አልባው ወታደራዊ ደርግ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙትን ካቴድራልና ትላልቅ አድባራት ወደ ሙዚየምነት ለመለወጥ በምሥጢር ጥናት መጀመሩን ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማጋለጥ ነበር።


ነገር ግን፣ የረጅም ዘመን ታሪክና የዳበሩ ባህላት ባለቤት የነብረችውን ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ምንም ዓይነት ዝግጁነት ያልነበረው ወታደራዊው ደርግ፣ የወቅቱ ግራ ዘመም ምሁራን ባመላከቱትና በውል ባልተገነዘበው የኅብረተሰብአዊነት ጎዳና እልም ብሎ በመንጎድ የፈጸማቸው ስህተቶች ሊወገዙ የሚገበቸው መሆኑ ባያጠያይቅም፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ መንግሥት ባለሥልጣኖች አለፍርድ ሲረሸኑ፣ አረጋዊው ንጉሠ ነገሥት በግፍ ሲገደሉ፣ በነጭና ቀይ ሽብር ሥም በሺህ የሚቆጠሩት የሀገሪቱ ብርቅዬ ወጣቶች ሲተላለቁና ሲጨፈጨፉ “ተራማጅ ካህን” ተብለውና በለውጥ ሐዋርያነት የሰላም ሉዑክ ሆነው ጎንደር ውስጥ እየተዘዋወሩ የኢትዮጵያ ትቅደምን
ዓላማ በመስበካቸው በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከተራ ምንኩስና ተነስተው ለሊቀ ጵጵስና ማዕረግ የበቁት ሰውዬ፣ በዘማዊነት ተጋልጠው በመወገዝ ማዕረጋቸውን ሲገፈፉ፣ ፀረ-ደርግ መስለው የፖለቲካ ስበእና እንዲላበሱ የተሞከረው የፕሮፓጋንዳ ሥራ፣ አንድም “ጅብ እማያውቅት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል!” አለበለዚያም “የገያ ግርግር ለምንትስ ይበጃል ይሏል ይኸ ነው!” እየተባለ እንዲፌዝባቸው ምክንያት ሆነ እንጂ ለኢ.ሕ.ዴ.አ፣ (EPDA) የፈየደው ነገር እንዳልነበር የመረጃው ምንጮች ያስታውሳሉ።


ሌላው ጅል ሙከራ ደግሞ፣ ደርግን ያዳክም ዘንድ የዩ. ኤስ. አሜሪካ አስተዳደር በማዕከላዊ የመረጃ ድርጅቱ (CIA) አማካይነት ድጎማ ያደርግለት ከነበረው የኢ.ሕ.ዴ.አ. መሪዎች መካከል፣ ዋና ጸሐፊው አቶ ደረጀ ደሬሳና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ሻምበል አሥራት ደፈረሱ ቀደሞ ለማስታወቂያ ሚኒስቴር በነበራቸው ቅርበት ምክንያት እጃቸው ሊገባ በቻለው የሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤት ባለአርማ ሌጣ የደብድቤ መጻጻፊያ ወረቀት ላይ የሚኒስቴሩን መሥሪያ ቤት የማይመለከት ጉዳይ የመንግሥት ጥብቅ ምሥጢር አስመስለው ሕዝብን ሊያሞኙ መከጀላቸው እንደነበርም የመረጃ ምንጩቹ አያይዘው ይገልጣሉ። በእነዚህ ጥረቶቹ የምግባረ ብልሹውን የአባ ተክለማርያም አስራትን፣ ማለትም የዛሬውን የአቡነ ማትያስን፣ ወንጀለኛነት በፀረ-ደርግ የፖለቲካ ታጋይነት ቀይሮ ለፕሮፓጋንዳ ሥራው ወደሱዳን መላክ የተሳነው ኢ.ሕ.ዴ.አ.፣ አባ ተክለማርያም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስርያን ቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው የጵጵስና ማዕረጋቸው መገፈፉን አምኖ ከተቀበለ በኋላ፣ በዘመኑ ከግብፁ ፕሬዚዳንት ሳዳት ጋር በተፈጠረ ግጭት ተግዘው በገዳም ይኖሩ ከነበሩት የኮፕቲክ (የግብፅ) ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስርያን ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ጋር ግንኙነት ተደርጎ “የግብፁ ፓትርያርክ በኢትዮጵያው ቅዱስ ሲኖዶስ አባ ተክለማርያም አስራት ተወግዘው የተገፈፉትን ጵጵስና መልሰው ሾሟቸው” የሚል ለፈፋ ማስተጋባት ጀምሮ እንደነበር የሚያስታውሱት የመረጃ ምንጮች፣ “የቸገረው …… ያገባል” እንዲሉ የአባ ተክለማርያም ጵጵስና ህዳሴ ማስረጃ ነው በሚል በአንዲት ብጣሽ ወረቀት ላይ በዐረብኛ ቋንቋና ፊደል የተጻፈች ማስታዎሻ ይዘው እንዲዘዋወሩ እስክ ማድረግ ደርሶ የነበረ መሆኑን የመረጃ ምንጮቻችን ያስረዳሉ።

See also  ለማይሞት ታሪክ የሚሰዋ ማንነት


በሌላ በኩል ግን፣ የቤተ ክርስርያንን ቀኖና የሚያውቁ ሊቃውንት፣ በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ አስተናጋጅነት በ325 ዓ.ም. በኒቂያ ተሰብስበው የነበሩት 318 የዘመኑ የክርስትና ዕምነት መሪዎችና ሊቃውንት ቀድመው ከሠሯቸውና እስከ ጊዜያችንም ከዘለቁት ዐቢይ ቀኖናዎች አንዱ የሆነው፣ የማናቸውም ሀገር ፓትርያርክ በሌላው ፓትርያርክ ሀገረ-ስብከት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ የሚያግድ ስለሆነና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያንም ከ1951 ዓ.ም. አንስቶ ከአሌክሳንድርያው መንበር ነፃ ወጥታ በእራሷ ቅዱስ ሲኖዶስና ፓትርያርክ የምትመራ ስለሆነች፣ የአርመንን፣ የሕንድንና የሶርያን አብያተ ክርስትያናት ጨምሮ፣ የኢትዮጵያና የግብፅም
ተዳምረው በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ዕምነታቸው “የኦርየንታል ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያናት” በመባል የጠበቀ የዕምነት ትስስር ያላቸው በመሆኑ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በህይወት መኖርና አለመኖራቸው ሳይረጋገጥ በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ መሾሙ አግባብ አይደለም በሚለው መርህ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖትን ፕትርክና “ከኢትዮጵያ መንግሥት ማራጋገጫ ሳላገኝ አልቀበልም!” በሚል አቋሟ ጸንታ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ተመርጠው የኢትዮጵያ መንግሥት የአቡነ ቴዎፍሎስን ሞት በደብዳቤ ገልጾ እስካስታወቀበት ጊዜ ድረስ ብትዘልቅም፣ የኢትዮጵያው ቅዱስ ሲኖዶስ በተጨባጭ ሕፀፅ አውግዞ የለያቸውን ሰው
ጵጵስና ለማደስ እስከመሄድ ቀርቶ፣ የግብፅ ቤተ ክርስትያን ከኢትዮጵያው ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ሊያቃርናት የሚችል አንዳችም ጣልቃገብነት ሳትሰነዝር ግንኙነቱን በጥንቃቄ ጠብቃ መቆየቷ ስለሚታወቅ እና ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ሺኖዳ በግዞት ከአሌክሳንድርይስ መንበራቸው ወደ ገዳም ተዛውርው ነበር ቢባልም፣ የቆዩበት ገዳም ሁሉ ነገር የተሟላበትና ለቅዱስ ፓትርያርኩ የሚያስፈልገውን አገልግሎት ሁሉ ለማበርከት ብቃት ያለው ከመሆኑ ባሻገር፣ በርካታ ሣይንሣዊ ምርምሮች የሚካሄዱብት፣ የተለያዩ ዘመናዊ የማምረቻ ተቋሞች የሚገኙበት፣ የተደነቀ ሆስፒታል ያለበት፣ እንደዚሁም መንፈሣዊና ዘመናዊ ትምህርት የሚሰጡባቸው ልዩ ልዩ ተቋማትን ያካተተ እንደመሆኑ መጠን፣ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ስለ ገዳሙ ይዞታ በነበረባቸው የግንዛቤ ችግር ካልሆነ በስተቀር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ክብራቸውን የጠበቀ ደብዳቤ መጻፊያ አጥተው በእጅ በተጻፈ ቁራጭ ወረቀት ቀኖና ጥሰው ጵጵስና ያድሳሉ ብሎ መገመት ሊታለም እንደማይገባው የመረጃ ምንጮቻችን ያረጋግጣሉ።


አባ ተክለማርያምና የኩብለላው ተባባሪ የነበረው ሾፌራቸውና አስተርጓሚቸው የዚያን ጊዜው አቶ፣ የዛሬው ዶክተር፣ ሙሴ ተገኝ የተለያዩት ሁለቱም ግሪክ ሀገር ደርሰው አባ ተክለማርያም እጃቸውን ለኢ.ሕ.ዴ.አ. ከሰጡ በኋላ በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ሲሆን፣ አባ ተክለማርያም አስራት አጅበዋቸው ከነበሩት ሁለት መነኮሳይያት (ሴቶች) ጋር በኢ.ሕ.ዴ.አ. ወደ ለንደን ሲላኩ፣ ግሪክ ባገኟቸው የስዊዝ አይሁዳውያን የተረዱት አቶ ሙሴ ተገኝ ያመሩት ወደ ጄኔቭ ስለነበር፣ በተደረገላቸው ዕርዳታ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የጤና ምግብ ሸቀጦች ችርቻሮ መደብር አቋቁምውና ትዳርም መስርተው ጄኔቭ መኖር የጀመሩት አቶ ሙሴ፣ የአባ
ተክለማርያምን እንቅስቃሴዎች በንቃት መከታተላቸውን የሚያስታውሱት የመረጃ ምንጮቻችን፣ ኢ.ሕ.ዴ.አ. አባ ተክለማርያምን “አቡነ ማትያስ” ብሎ እያስተዋወቀ ሕጋዊ ጳጳስ አስመስሎ ለፕሮፓጋርዳ ሥራው ወደ ሱዳን ለመላክ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ውጥኑን በቅድሚያ አውሮጳ ውስጥ በውቅቱ ተቋቁመው በነበሩት ጥቂት ቤተ ክርስትያኖች ዘንድ እየተዘዋወሩ ቡራኬ በመስጥት ተቀባይነት እንዲያገኙ ለማላመድ ባወጣላቸው መርሐ-ግብር አማካኝነት ጀርመን ሀገር በምትገኘው የኮሎኝ ከትማ በተቋቋመችው ቤተ ክርስቲያን ሊቀድሱና ብራኬ ሊሰጡ ፕሮግራም መያዙን ያረጋገጡት አቶ ሙሴ ተገኝ፣ በማለዳ ባቡር ተጉዘው በቤተ ክርስትያኑ በመገኘት፣ አባ
ተክለማርያም የጵጵስና ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ከመቅደሱ መጋረጃ ብቅ ሲሉ “ውግዕዝ!” ብለው በመጮህ የመዕመናኑን ትኩርት ከሳቡ ብኋላ፣ አባ ተክለማርያም አቡነ ማትያስ እየተባሉ በኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስነት በቆዩባቸው ጥቂት ዓመታት ሾፌርና አስተርጓሚያቸው ሆነው ስለአገለገሏቸው በቅርብ እንድሚያውቋቸው፣ አቡነ ማቴዎስ አመንኩሰው እምሆይ አብርሃም ብለው በሰየሟቸው የዴንማርክ ተወላጅ በማዳም ክርስቲያን ፔደርሰን ፍቅር ተነድፈው ግንኙነታቸውን በጥንቃቄ ይይዙ ዘንድ በገዳማቱ አረጋዊ መነኮሳት ቢመከሩ አሻፈረኝ እንዳሉ፣ ይህን ላለማየትና ላለመስማት አንዳንዶቹ አረጋዊ መነኩሴዎች ከኢየሩሳሌም እየሸሹ ቤተ-ልሄምን ወደ መሰሉ ሌሎች ቅዱስን
ሥፍራዎች እየራቁ በመሄድ እስከመቀመጥ እንደደረሱ፣ ለወትሮው በአቡነ ማትያስ ላይ የሚሰነዘሩ ነቀፋዎችን “ከእኔ እኩል የሚያውቀው ስለሌለ ምቀኝነት ከመሆን አይዘልም” እያሉ ሲያጣጥሉላቸው የቆዩት ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ይህን ከአንድ ሊቀ ጳጳስ ቀርቶ ከተራ መነኩሴ የማይጠበቅ አስነዋሪ ተግባር ሰምተው በዝምታ ማለፍ እንዳልቻሉ፣ ስለዚህም በቅዱስ ሲኖዶሱ ፊትን ቀርበው ምላሽ ይሰጡ ዘንድ የደብዳቤ ጥሪ እንደላኩላቸው፣ ሊይስተባብሉት የሚችሉት ክስ ስለአልሆነ ከኢ.ሕ.ዴ.ኣ. ጋር የመሰረቱትን ግንኙነት ከእኔ ጭምር እንድሸሸጉ፣ በአውሮጳና በአፍሪቃ ይህችን ቤተ ክርስቲያን የማስፋፋት ዕቅድ አለኝ በሚል ሰበብ ብዙ ቶን እቃ
የሚይዝ ኮንቴይነር እመኖሪያ ግቢያቸው ውስጥ አስቀርብው በገዳማቱ ንብረቶች ዘመዶቼ ክሚሏቸው መነኮሳይያት ጋር በመተጋገዝ ኮንቴይንሩን ሲሞሉ እንደሰነበቱ፣ በአቶ ዮፍትሔ ዲሜጥሮስ አማካይነት ኮንቴይነሩን በመርከብ አቴንስ እንዲላክላቸው በውድቅት ሌሊት ወደ ሃይፋ እንዳስጫኑ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ኢየሩሳሌም ድረስ ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን እንደሚልኩ ስለ አስታወቋቸው ቡድኑ ኢየሩሳሌም ሊገባ አንድ ቀን ሲቀረው በገዳሙ ገንዘብ ለእራሳቸው፣ ለእኔና ዘመዶቼ ለሚሏቸው ሁለት ሴት መነኮሳይስት የአይሮጵላን ቲኬቶች አስቆርጠው አቴንስ እንደደረሱ፣ መርማሪውን ቡድን ሸሽትው መኮብለላቸውና መርማሪው ቡድንም
ጉዳዩን አጣርቶ የቀረበባቸው ክስ ዕውነትንት ያለው መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ አቡነ ማትያስን አውግዞ ጵጵስናቸውን መሻሩን የኢ.ሕ.ዴ.አ.ን ሹማምንት ለመገናኘት አቴንስ በመጠባበቅ ላይ እያሉ እንደተረዱ እና እንደዚሁም አቴንስ ይደርስልኛል ብለው ይጠብቁት የነበረውን ኮንቴይነር የእሥራኤል ፖሊስ ሕገ-ወጥ ጭነት ነው ብሎ እንዳስቀረው ሲነገራቸው፣ “አንተ ጠቁመህ ነው ያስያዝክብኝ!” ብልው ስለተጣሏቸው ግንኙነታቸው እንድትቋረጠ በመዘርዘር አቶ ሙሴ ስለአስረዱ፣ አባ ተክለማርያም በመቅደሱ መጋርጃ ውስጥ ትሸሽገው አልውጣም በማለታቸው አገልግሎቱ ተቋርጦ ሕዝበ-ክርስትያኑ መበተኑን የመረጃ ምርጮቻችን አብራርተዋል፡፡


በሊቀ ጳጳስ እየተመራ ፋሺሽቱ ደርግ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤት ክርስቲያንን ለማኮላሸት የሚያካሂድውን ሴራ ዘርዝሮ የሚያስጨብጥ መንፈሣዊ የራዲዮ ፕሮግራም በቅርቡ እንደሚጀምር አስታውቆ የነበረው ኢ.ሕ.ዴ.አ.፣ በዕቅዱ መሰረት አባ ተክለማርያምን ወዲያውኑ ወደ ሱዳን አጓጉዞ የተቀጠሩበትን ሥራ ሊያስጀምራቸው ያልደፈረው፣ ሱዳን ለኢትዮጵያ ካላት ቅርበት አንፃር የኢትዮጵያ ራዲዮ ሱዳን ውስጥ የሚደምጥ ከመሆኑ ባሻገር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚናፈሰው ወሬ በተለያዩ መስመሮች ሳይዘገይ ሱዳን እየደረሰ ስለሚራባ፣ አቡነ ማትያስ በቀኖና ጥሰትና በምግባረ ብልሹነት ክስ በቅዱስ ሲኖዶስ ተውግዘው ጵጵስናቸው መገፈፉን
በተጨባጭ ሊያስተባብል የሚችል ግንዛቤ በዘዴ ካልተፈጠረ በስተቀር አንገት የሚያስደፋ ሁኔታ ይፈጠራል ብሎ በመገመቱ እንድነበር የሚያመለክቱት የመረጃ ምንጮቻችን፣ በአውሮጳና በኢ.ሕ.ዴ.አ.ም (EPDA) አካባቢ “የኮሎኝ ቅሌት” ተበሎ መታወቅ ከጀመረው ክስተት በኋላ፣ አባ ተክለማርያምን ሱዳን ወስዶ በራዲዮ ሠራተኛነት ሊጠቀምባቸው የነበረውን ዕቅድ ኢ.ሕ.ዴ.አ. ፈጽሞ መሰረዝ ስለተገደደ፣ አባ ተክለማርያምን ለንደን ውስጥ አስቀምጠው የመንከባከብ ኃላፊነት የተጣለባቸው የኢ.ሕ.ዴ.አ. አባል አቶ ዮሐንስ መሸሻ ከሸክሙ ለመገላገል የሚከተሉትን ዐራት ሐሣቦች ለድርጅታቸው አቅርበው ከአባ ተክለማርያም አስራት ሊገላገሉ መቻላቸውን
አስረድተዋል።

እነዚህም፦
1ኛ. አገልጋይ ካህን አጥተው የተቸገሩ ቤተ ክርስቲያኖች አሜሪካ ስለሚገኙና ሥራ ሊሰጧቸው ስልሚችሉ፣
2ኛ. ኢየሩሳሌም ውስጥ በፈጸሙት አስነዋሪ ድርጊት ምክንያት ተወግዘው ጵጵስናቸው መገፈፉ አሜሪካ ገና ስላልተወራ፣
3ኛ. የኮሎኙ ቅሌት ቢሰማ፣ ይህ የተፈጸመባቸው ደርግን አውግዘው ስለተሰደዱ ነው ብሎ አሜሪካ ማስተባበል ስለሚቀል፣ እና
4ኛ. አሜሪካ በብዛት የሚገኙት የኢ.ሕ.ዴ.አ. እና የኢ.ዴ.ኅ. (EPDA & EDU) አባላት ይህን ጉድ መሸፈን ስለማይሳናቸው፣ የሚሉ ነበሩ።


ገንዘብ ችግሩ ያልነበረው ኢ.ሕ.ዴ.አ. የአቶ ዮሐንስ መሸሻን ምክር ተቀብሎ፣ አባ ተክለማርያም አስራትን ወደ ዩ.ኤስ.አሜሪካ የኒው ጀርሲ ክልል አዛውሮ የኪስ ገንዘብ በመክፈል እንዳስቀመጣቸው፣ አቶ ዮሐንስ መሸሻ ደግሞ “ደርግን አውግዘው የተሰደዱ ጳጳስ ቦዝነው ኒው ጀርሲ ተቀምጠዋልና እንዳያመልጧችሁ!” የሚል መልዕክት ዋሽንግተን ዲሲ ለሚኖሩ የኢ.ሕ.ዴ.አ. አባላትና ለግል ዘመዶቻቸው ስለአደረሱ፣ ዋሽንግተን ዲ.ሲ. ውስጥ ተቋቋሞ ከነበረው የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን መሪዎች አብዛኛዎቹ የወታደራዊውን ደርግ አገዛዝ እስሸሹ የሄዱ በመሆናቸው ወዲያው ግንኙነት ፈጥረው፣ የኢ.ሕ.ዴ.አ. መረጃ ክፍል ሠራተኛ የነበሩትን ሃምሳ አለቃ አሸናፊ
ከበደን ኒው ጀርሲ ልከው አባ ተክለማርያምን ካስመጡ በኋላ፣ ሲልቨር ስፕሪንግ ይገኝ እነበረው የኮሎኔል አስፋው አንዳርጌ ቤት እንዳሳረፏቸው የሚያስታውሱት የመረጃ ምንጮቻችን፣ በሙሉ የጵጵስና ልብሶቻቸው ላይ በአንገት የሚጠልቁ መስቀሎችን ደርድረው ሲልቨር ስፕሪንግ የደረሱት አባ ተክለማርይም፣ ጥቂት ቀናት ኮሎኔል አስፋው ቤት ተቀመጠው “እዚህ የመጣሁት የኮሎኔል አስፋውአንዳርጌ ዳዊት ደጋሚ ልሆን ነው ወይ?” የሚል ስሞታ ለኢ.ሕ.ዴ.አ. ስለአቀረቡ፣ ድርጅቱ ከመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከሚከፈላቸው ደመወዝ በተጨማሪ 600.- ዶላር የወር አበል መድቦላቸው በግላቸው ቤት ተከራይተው የአሜሪካ ኑሮአቸውን
እንደጀመሩ አብራርተዋል።


አባ ተክለማርያም አስራት የዋሺንግተኑን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከኒው ዮርክ በየሣምንቱ እየተመላለሱ ያገለግሉ በነበሩት መልአከ ገነት ውቡ ላይ ያሳድሩት የንበረውን አግባብ የለሽ ተፅእኖና እራሳቸው ከኬንያ ድረስ አስመጥተዋቸው ከነበሩት ድያቆን አስትርአይ ፅጌ ጋር የነበራቸውን አለመግባባት፣ የቤተ ክርስቲያኑን አስትዳደር ቦርድ ሚና አሳንሰው ማናቸውንም የደብሩን ጉዳይ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራራቸው ውስጥ ለማድረግ ከነበራቸው ውጥን ጋር አዛምደው የሚያስታውሱትና በምን ምክንያትና በምን ዓይነት ሁኔታ እንደተወገዙና እንዴትስ ለቤተ ክርስቲያናቸው እልቅና እንደበቁ ለማጣራት ያልሞከሩት ምዕመናን፣ አባ ተክለማርያምን ብፁዕ አቡነ ማትያስ እያሉ በማክበር ቢዘልቁም፣ ከቤተ ክርስትያኑ ምዕመናት መካከል በተለይ ከአንዷ ሴተ-ላጤ ጋር መነኩሴ መሳዩ መንፈሣዊ አባት-ተብዬ በነበራቸው ቅጡ የጠፋ ግንኙነት ምዕመናኑ እጅግ ይሳቀቁ እንደነበር የሚገልጹት በከፍተኛ ሀፍረት መሆኑን የሚያወሱት የመረጃ ምንጮቻችን፣ለአባ ተክለማርያም ዐይን ያወጣ ዘማዊነት እንደማስረጃ ከሚጠቅሷቸው ነገሮች መካከል ዘመዶቼ ናቸው ብለው ከኢየሩሳሌም ካስኮበለሏቸው ሁለት መነኮሳይያት መካከል አንዷ ነገሩ ስለአጣማቸው ቀደም ብለው መለየታቸውን፣ አብረው የዘለቁት መነኩሲት ደግሞ ከዚቹ ከሴተ-ላጤ ጓደኛቸው ጋር እስከ መደባደብ ከደረሱ በኋላ ቤቱን ለእሷ ለቅቀው ወደ ሌላ ስፍራ መሸሻቸውን፣
ምዕመናኑ በዚቹ ሴተ-ላጤ ቤት አጠገብ አንድ የፈረጠመ ጥቁር አሜሪካዊ ቁምጣ ሱሪ ለብሶ የግቢዋን ሳር ሲያጭድ ዓይተው ጠጋ ብለው ቢመለከቱት አባ ትክለማርያም፣ ማለትም የዛሬው አቡነ ማትያስ፣ ሆነው ስለአገኟቸው ተደናግጠው ከአካባቢው በሩጫ መሰወራቸውን የመሳሰሉት ድርጊቶች ይግኙበታል።

See also  Kim Jong Un Urges Officials to Overcome the Country’s ‘Grim Situation’


ከፍ ብለው በተዘረዘሩት ሁኔታዎች፣ ለውግዘትና ጵጵስናቸውንም እስከማጣት ያደረሷቸውን ምግባረ-ብልሹነትና የወንጀል ታሪካቸውን በማይመለከታቸው የፀረ-ደርግነት ጀብዱ ሸፍነው እምብዛም ሳይነቃባቸው የተወሰኑ ዓመታትን እዋሺንግተን ዲ.ሲ. ውስጥ አድፍጠው ለማሳልፍ የቻሉት አባ ተክለማርያም፣ ወያኔና ሻዕቢያ በኅብረት ደርግን አስወግደው ሥልጣን እንደጨበጡ ወደ አዲስ አበባ በመገስገስ፣ አንዴ ሲያስተባብሉትና አለበለዚያም ግብፆች ሽርውልኛል ይሉት የነበረው ውግዘት፣ ለማንም ግልጽ ሊሆን ባልቻለ ሁኔታ በእነ አቡነ ዜና ማርቆስ እንድተነሳላቸውና በአቡነ ጳውሎስ በሰሜን አሜርካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሆነው
መሾማቸውን፣ በእልቅና ይመሩት የነበረውን የዋሽንግተን ዲ.ሲ.ውን ደብረ ገነት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንን ሰብስበው ከገለጹ በኋላ፣ “እንኳን ደስ ያለዎት! ሹመት ያዳብር!” የሚል ማበረታቻ ሲጠብቁ፣ ብዙኃኑ የቤተ ክርስርያኑ ምዕመናን “በገለልተኛነት አቋማችን የምንቀጥል ስለሆን ከእርስዎ ጋር የነበረን ተቋረጠ ማለት ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ በማንሳት እንዳስደነገጧቸው የገለጡት የመረጃ ምንጮች፣ የምዕመናኑን አቋም ወዲያው የተገነዘቡት አባ ተክለማርያም ወይም አቡነ ማትያስ እስከዚያን ጊዜ ድረስ በተውሶና በኪራይ ቤተ ክርስቲያን ሲገለገሉ የኖሩት የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን መዕመናን ቤተ ክርስቲያን ለማሠሪያ እያዋጡ በባንክ
አጠራቅመውት የነበረውን ከሦሥት መቶ ሺህ ዶላር በላይ የነበር ገንዘብ ከባንክ ሒሣቡ ሙልጭ አድርገው በማውጣት ወደ ግል የባንክ ሒሣባቸው በጥድፊያ ማዛወራቸውን ያስረዳሉ።


ይህን የወንጀል ድርጊት የተረዳው እና በአቶ አንዳርገህ በላቸው ይመራ የነበረው የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳድር ቦርድ “ በሕገወጥ መንገድ ገንዘባችንን ተቀማን!” የሚል ክስ በፍርድ ቤት ቢመሠርትም፣ በመላው የሰሜን አሜሪካ የሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት ሁሉ የበላይ ሊቀ ጳጳስ እኔ ስለሆንኩ፣ በማናቸውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሀብት የማዘዝ መብት ያለኝ ብቸኛ ባለሥልጣን ነኝ የሚል ሙግት በማቅረብ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየተጓተተ ቤተ ክርስቲያኑ ለጠበቃ የሚያወጣው ገንዘብ ተዳምሮ ምዕመናኑን እሚያስጨንቅበት ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር የገለጡት የመረጃ ምንጮች፣ የተሻለ አማራጭ ያጡት የቤተ ክርስቲያኑ
ምዕመናን በሽማግሌ ተደራድረው መቶ ሺ ዶላር ለአባ ተክለማርያም ወይም ለአቡነ ማትያስ በመልቀቅ ቀሪውን ብቻ እንዳስመለሱ ያብራራሉ፡፡

አዲስ ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ተቃርበው የነበሩት ምዕመናን ካጠራቀሙት ገንዘብ አንድ ሦሥተኛውን ከመነጠቃቸውም ባሻገር፣ ካስመለሱት ገንዘብም ግማሽ ያህሉን ለጥብቅና ክፍያ ማዋል ስለተገደዱ፣ እኚሁ አባት ተብዬ ባካሄዱባቸው ዘረፋ ሳቢያ ለቤተ ክርስቲይኑ ማሠሪያ የሚይስፈልገውን ገንዘብ ለማሟላት ወደ አሥር ዓመት የሚጠጋ ተጨማሪ ጊዜ እንደፈጀባቸውም ማወቅ ተችሏል። ይህ በዚህ እንዳለ፣ “ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች” እንዲሉ፣ አቡነ ማትያስም ከአንድ መነኩሴ የማይተበቅ አስነዋሪ ተግባር እና አሳፋሪ የወንጀል ድርጊት ወደ ፈጸሙባት ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ዳግም ሊቀ ጳጳስ ተብለው መመለሳቸውን በአግራሞት
የሚያነሱት የመረጃ ምንጮች፣ አቡነ ማትያስ “ጎረምሳው ጳጳስ!” እየተባሉ ይሾፍባቸው በነበረው ዘመን በኢየሩሳሌምና አካባቢዋ ባሉት ገዳማት ይኖሩ የነበሩት መነኮሳት በዘር መስፈርት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በመደረጉና ብዙዎችም በዕድሜ መግፋትና ብጉስቁልና በሞት ስለተለዩ፣ የአቡነ ማትያስን አስነዋሪ እና አሳፋሪ ተግባሮች ጠንቅቀው ከሚያውቁት አረጋዊ መነኮሳት መካከል በህይወት የሚገኙት አባ ላዕከ ( አቡነ ሕርያቆስ) እና አባ አምዴ ብቻ መሆናቸውን ይገልጣሉ፡፡


“ይባስ አታምጣ እንዲሉ” እኚህ ጉደኛ ሰው ዋሺንግተን ዲ.ሲ. ውስጥ ዕውነተኛ ማንነታቸውን በሸፍጥ ደብቀው ሳይነቃባቸው ዓመታትን ማስቆጠራቸው፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ውግዘት የተሻረ ጵጵስናቸውን ያስመለሱበት ሁኔት በውል አለመታውቁና ተሾመው ነው ቢባል እንኳን ዐይን አውጥተው በሊቀ ጵጵስና ኢየሩሳሌም ለመመለስ መድፈራቸው የብዙሃን መነጋገርያ ሆኖ እያለ፣ ጠልቀው የተማሩ ደናግልት ጳጳሳትና ብቃት ያላቸው ሌሎት መነኮሳት ባልገደዱባት ኢትዮጵያ “አቡነ ማትያስን በድርጊቶቻቸው ተዋርደው ከወደቁበት አንስቶ በተከበረው መንፈሣዊና ቅዱስ መንበረ ፓትርያርክ ላይ ማስቀመጥ ለምን አስፈለገ?” የሚል ጥያቄ የሚያነሱት የመረጃ
ምንጮቻችን፣ አሁንም ቀኖና ተቀበለው በንሥሐ ጸድተዋል ሊያሰኟቸው ከማይችሉት ሕፀፆቻቸው ማካከል ያልተማሩትን ተምሬአለሁ፣ የማያውቋቸውን ቋንቋዎች እናገራለሁ፣ ለፕትርክና መታጨቴን ፍጹም አላውቅም ነበር፣ የፓትርያሪክ ምርጫው ታዳሚ ከነበሩት መራጮች የአምስት መቶውን ድምፅ ስላገኘሁ ሹመቱን ተቀበልኩ፣ ወዘተ….በማለት በብዙኃን መገናኛዎች ጭምር ያስትጋቧቸው መግለጫዎች በእብለት የታጀሉ እንደነበሩ አስትውለው በመኮነን ነው።


ሕ.ወ.ሓ.ት. አቡነ ማትያስን ለፓትርያርክነት ያበቃቸው በትግራይ ተወላጅነታቸው ብቻ ነው ለማለት አንድፍርም የሚሉት የመረጃ ምንጮቻችን፣ የትግራይ ማህጸን እጅግ የተደነቁና የተከበሩ መንፈሣዊ አባቶችን ያፈራች መሆኗ በስሚም ቢሆን በሕ.ወ.ሓ.ት. ዘንድ ሳይታውቅ አለመቅረቱ ላይ በማተኮር፣ ከጀርባው ሌላ ሤራ ከሌለ በስተቀር ሕ.ወ.ሓ.ት. ይህን ያህል ወርዶ እኚህን በውሸታምነታቸው የታወቁ፣ በሕፀፅ የተሞሉ፣ ስብእና የጎደላቸውና ምግባረ ብልሹ ግለሰብ በሀገራችን አንጋፋና ግዙፏ የሃይማኖት ተቋም አናት ላይ ሊያስቀምጥ አይችልም ነበር የሚል ግምታቸውን ያስደምጣሉ።


ለፓትርያርክነት መታጨቴን አላውቅም ነበር እና በቤተ ክርስቲያናችን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ሊቃውንት፣ ካህናት፣ ምዕመናንና የሰንበት ተማሪዎች በከፍተኛ የድምፅ ብልጫ ተመረጥኩ ብለው ሊያጃጅሉን የሚማስኑትን አቡነ ማትያስን ለማጋለጥ የሚከተሉትን ሁለት ነጥቦች በማንሳት ብቻ መታዘብ ይቻላል ያሉን የመረጃ ምንጮች፣
አንደኛ፡- አቡነ ማትያስ በፓትርያሪክ ምርጫው ላይ ለመወዳደር ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ በተነሱበት ጊዜ፣ በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች የሆኑትን የገዳማቱን መነኮሳት ሰብስበው ለማጽናናት ባደረጉት ንግግር ፣ “አይዟችሁ! መልካም አባት ይሾምላችኋል!” አሉ እንጂ፣ በምርጫው ቢሺነፉ ሊመለሱ ስለመቻላቸው ምንም ዓነት ፍንጭ አልሰጡም፤ በመመረጡ እርግጠኛ ካልሆነ ሰው ይህን አባባል ማድመጥ ይቻላል ወይ?
ሁለተኛ፡- ከኢየሩሳሌም ሸሽትው በአውሮጳ ወደ አሜሪካ የተሻገሩት አቡነ ማትያስ በደርጉም ሆነ በወያኔው የአገዛዝ ዘመናት አሜሪካዊ እንጂ ኢትዮጵያዊ አልነበሩም፤ የአሜሪካን ዜግነታቸውን በመተው ወደ ኢትዮጵያዊነታቸው መመለሳቸው ተረጋገጠላቸው የተባለው አቡነ ጳውሎስ በሞቱበት ባለፈው ሐምሌ ወር ነው፤ ከዓለም አቅፍ ሕግ አንፃር ያለው አጠያያቂ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ “የኢትዮጵያ ዜግነት የሌለው ሊመረጥ አይገባውም መባል በተጀመረበት ወቅት” የአቡነ ማትያስ የአሜሪካ
ዜግነት፣ ላዩም ከኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተጻፈ ደብዳቤ ብቻ፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸው በአስቸኳይ እንዲማለስላቸው እንዴትና ለምን ተደረገ? የእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች መልስ በርካታ ሁነቶችን ገላጭ እንደሆነ ያማላከቱን የመረጃ ምንጮች፣ አቡነ ማትያስ በተገለጠው ሁኔታ ፓትርያርክ ለመባል የበቁት እሳቸውና ግብረ-አበሮቻቸው ሊያጃጅሉን እንደሚሞክሩት ለምርጫው በተሰለፉት ሊቃነ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ሊቃውንት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ የሰንበት ተማሪዎችና የቤተ ክህነቱ የአስትዳደር ሠራተኞች ተመርጠው ሳይሆን፣ በሕ.ወ.ሓ.ት. ቀዳሚ ውሳኔ ስለተመደቡ መሆኑ አያጠያይቅም በማለት የሚያረጋግጡልን የመረጃ ምንጮች፣ አያይዘውም፣ ሕ.ወ.ሓ.ት. ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል አቡነ ማትያስን ቀኖናን በጣሰ ሁኔታ መርጦ በፓትርያርክነት ሊመድብ
የበቃበት ምክንያት ቀጥለው ከሰፈሩት ሦሥት ነጥቦች በአንዱ ወይም በሁሉም ከመሆን እንደማይዘል አብራርተውልናል። እነዚህም፡-


1ኛ. የአቡነ ማትያስን ምግባረ ብልሹነት ዘርዝረው የሚያረጋግጡ መረጃዎች በሕ.ወ.ሓ.ት. የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና በውጭ ሀገራት ባሉት የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች በሚገባ ተሰባስበውና ተጠርዘው ስለሚገኙ፣ አቡነ ማትያስ በሕ.ወ.ሓ.ት. የሚሰጣቸውን ማናቸውንም ግዳጆች ለመፈጸም የማይተጉ ወይም አንገታቸውን ቀና እያደረጉ ለማንገራገር የሚከጅሉ ቢሆኑ፣ እነዚህን ሰንዶች በመምዘዝና በማስፈራራት ምንጊዜም የሕ.ወ.ሓ.ት. ፍላጎት ፈጻሚና አስፈጻሚ አድርጎ በመሣሪያነት ሊጠቅምባቸው እንደሚችል እርግጠኛ ስለሆነ፤
2ኛ. የዐማራና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የጀርባ አጥንት ሰብረናል ከሚለው ወያኔያዊ ፉከራ አኳያ፣ በታላቁ የቤተ ክርስቲያን መንበር ላይ ምግባረ-ብልሹ ሰው ማስቀመጥ የምዕመናኑን ቅስም ከመስበር ባሻገር ቤተ ክርስቲያኗን ይበልጥ ያዳክምልናል ብሎ ሕ.ወ.ሓ.ት. ስለአመነ፤ እና
3ኛ. የትግራይ ተወላጆች በእኛ ተይዞ የነበረው ፓትርያሪክነት ለምን በሌሎች ተወሰደብን ብለው እንዳይቆጡ የአቡነ ማትያስ ትግራዋይነት በትግራይ ሕዝብ ዘንድ እርካታን ይፈጥርልኛል ብሎ ሕ.ወ.ሓ.ት. ስለገመተ፤ነው የሚሉ ናቸው።


ይህን ዘገባ መቋጨት የምንሻው፣ የወያኔው አገዛዝ ርዕዮት ከእነድክመቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አንድ ለምንኩስና በቅቻለሁ የሚል ሰብአዊ ፍጡር፡- ሲያሰኘው መነኩሴ – ያዋጣል ካለም አብዮተኛ፣ ሲደላው የኢትዮጵያ -አልሆን ሲለው የግብፅ ጳጳስ፣ መሸወድ ሲችል ዓለማዊ፣ ሲነቃበት መንፈሣዊ፣ ለምቾት አሜሪካዊ – ለሹመት ኢትዮጵያዊ፣ እያለ እንዲገለባበጥ እንዴት ኅሊናው ይፈቅድለታል? የሚል ጥያቄ በማንሳት ሲሆን፣ ይህ ጥያቄ የሚነሳውም ማናቸውም ሰብአዊ ፍጡር ይብዛም ይነስም ኅሊና የሚባለው ነገር በውስጡ ሳይኖር አይቀርም በሚል ግምት ነው፡፡


ከሁሉም ይልቅ የሚያበግነው ግን፣ በኢትዮጵያችን እንዲህ ዓይነቱ አቋምና በጎ ምግባር የለሽ ግለሰብ፣ የኦርቶዶክስ ተውሕዶ ክርስትና እምነት ተከታይ እሆኑት ዜጎች አናት ላይ ጉብ ብሎ፣ ከ40 ሚልዮን በላይ የሆኑት ምዕማናን ቅስም ይሰበር ዘንድ የሕ.ወ.ሓ.ት. አገዛዝ መሻቱ የሚያንፀባርቀው የጥላቻና የንቀት ዕውነታ መጠን፣ ማንም ሊሸከመው ከሚችለው በላይ መግዘፉ እንደሆነ መታውቅ አለበት።

ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ!

ዝግጅት ክፍሉ – ይህን ጽሁፍ አድራሻና ስም ጠቅሰው የላኩልን ኩሩቤል ሃይሌ ናቸው። “ለግንዛቤ ቢረዳ፣ ደግሞም እንዳይረሳ” ሲሉ ሕዝበ ክርስቲያኑ ይህን መረጃ ቢያነብ እንደሚተቅም አስበው በተቆርቋሪነት ስሜት እንድናትምላቸው ጠይቀውማል። ጽሁፉ የጸሃፊዎቹና የላኩልን ሰው አሳብ ብቻ የሚወክል እንደሆነ ለመጠቆም እንወዳለን። ምላሽ የሚሆን ወይም የሚደግፍ አሳብ ካለ እናስተናግዳለን።

ሐመረ ኖኅ Sedpsonrtoa0fa4m501 83 lMyua93aft2a,490gu1aaf22lfi81hh43796u  

Leave a Reply