Site icon ETHIO12.COM

በፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለተ.መ.ድ የሰብዓዊ መ.ኮ የአፈጻፀም ሪፖርት አቀረበ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ የአፈጻፀም ሪፖርት አቀረበ፡፡

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግስት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን (ኮንቬንሽን) አፈጻፀምን በሚመለከት ጄኔቫ ፤ሲዉዘርላድ በመገኘት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ ሪፖርት አቀረበ፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (International Covenant on Civil and Political Rights) አባል ሀገር ስትሆን በስምምነቱ ውስጥ የተካተቱ ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር፣ ማስከበር እና የማሟላት ኃላፊነቶችን መወጣት እና በስምምነቱ አንቀጽ 40 በተቀመጠው ግዴታ መሰረት ስለ ስምምነቱ አፈጻፀም በየጊዜው ሪፖርት ማቅረብ ይጠበቅባታል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ውሣኔ ቁጥር 2200 A (XXI) ፀድቆ ለአባል ሀገራት እንዲፈርሙና እንዲያፀድቁት እ.ኤ.አ ዲሴምበር 16 ቀን 1966 ክፍት የተደረገው ዓለም አቀፉ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ተግባራዊ መሆን የጀመረው እ.ኤ.አ ከማርች 23 ቀን 1976 ሲሆን ሀገራችን ስምምነቱን በማፅደቅ አባል የሆነችው ደግሞ እ.ኤ.አ ከጁን 11 ቀን 1993 ነዉ፡፡

ኢትዮጵያ አባል ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ በአንድ ዓመት ጊዜ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ስለተወሰዱ እርምጃዎች መነሻ ወይም ቀዳሚ ሪፖርት (Initial Report)፤ በማስከተልም በስምምነቱ መሠረት የተቋቋመውና አገራት ስምምነቱን ተግባራዊ ስለማድረጋቸዉ እንዲከታተል ስልጣን የተሰጠዉ የተ.መ.ድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ በጠየቀ ጊዜ (ብዙ ጊዜ በየአራት ዓመቱ) ወቅታዊ የአፈጻፀም ፕሮግረስ ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ አለባት፡፡

በዚህም መሰረት ደም ብሎ ተዘጋጅቶ ለኮሚቴዉ የተላከዉን 2ኛውን ሀገራዊ የአፈጻፀም ሪፖርት እና ሪፓርቱ ከተላከ በኋላ በሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ በአገራችን ኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተመዘገቡ መሻሻሎችና ዉጤቶችን በጄኔቫ ሲዉዘርላድ እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 17 እና 18 ቀን 2022 በአካል ሪፖርት በማቅረብ እና ከኮሚቴ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያን መንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን የመሩት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ለኮሚቴዉ አስቀድሞ ስለተላከዉ ሪፖርት ይዘት፣ ሪፖርቱ ከቀረበ በኋላ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ስለተከናወኑ ከስምምነቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሥራዎች፣ ስምምነቱን በመተግበር ሂደት ስለጋጠሙ ችግሮችና ተግዳሮቶች እንዲሁም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለሚጠበቁ የተለያዩ ትብብሮችና ድጋፎች አንስተዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዉ በተለይም በአገራችን የአመራር ለዉጥ መካሄዱን ተከትሎ በዓለም አቀፉ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን ስምምነት የተመለከቱት ሰብዓዊ መብቶችን ጨምሮ አጠቃላይ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማክበር እና ለማስከበር እንዲሁም ለማሟላት ሰፊ የሕግ ማሻሻያ ሥራዎች እንዲሁም ፓለቲካዊ፣ ተቋማዊ እና የአሰራር ስርዓት ለውጦች መደረጋቸውን ፤ ለማሳያነትም አዲሱ የለዉጥ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሺዎች ለሚቆጠሩ እሰረኞች እና ተጠርጣሪዎች ምህረትና ይቅርታ ማድረጉን፣ በፖለቲካ አመለካከታቸዉ ተገደዉ ከአገር እንዲሰደዱ የተደረጉ ብዛት ያላቸዉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባላት፣ጋዜጠኞችና ፀሃፊዎች፣የፖለቲካና የሚዲያ ተቋማት ወደ አገር ዉስጥ ገብተዉ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ መደረጉን ፤ ታግደዉና ተዘግተዉ የነበሩ ብዛት ያላቸዉ ድህረ ገጾችና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንዲከፈቱ መደረጉን ፤ ከፍተኛ በሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ የወቅቱ የፀጥታና የደህንነት መዋቅር አመራሮችና ሠራተኞች ለሕግ መቅረባቸዉንና የማሰቃያ ቦታዎች ተለይተዉ በመንግስት መዘጋታቸዉን ገልጸዋል፡፡

አቶ ዓለምአንተ አግደዉ ለኮሚቴዉ ሲያብራሩ ከሕግና ፍትሕ ማሻሻያ እንዲሁም ተቋም ግንባታ አንጻር የተከናወኑ የለዉጥ ሥራዎች ለሰብአዊ መብቶች መከበር ከፍተኛ ድርሻ አላቸዉ ብለዋል፡፡ እንደ ሚኒስትር ዴኤታዉ ገለጻ በሕግ አስከባሪ፣ በደህንነትና ፀጥታ እንዲሁም በዲሞክራሲ ተቋማትና በፍ/ቤቶች በቀጣይ የሚሰሩ ተጨማሪ የማሻሻያ ስራዎች እንደተጠበቁ ሆነዉ ከፍተኛ ለዉጥ የተመዘገበባቸዉ ናቸዉ ፡፡
የፀረ-ሽብር፣የስቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣የአስተዳደር ሥነ-ስርዓት ፣ የስደተኞች ፓሊስና የተጎጅዎች ፈንድ ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብን ጨምሮ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝዉዉር ለመከላከል የወጣዉ አዋጅ ፣ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያያ ዝዉዉር ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ፣ ነጻ የጠበቆች ማህበር እና የጥብቅና ድርጅት ፈቃድ ለመጀመሪያ ጊዜ መስጠት የተቻለበት የጥብቅና አስተዳደር አዋጅ፣ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ፣ የጥላቻ ንግግርና ሃሰተኛ መረጃ ለመከላከል የወጣዉ አዋጅ፣ የፍ/ቤቶች አስተዳደር አዋጆች፣ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ የመከላከያ እና የብሔራዊ መረጃና ደህነት አገልግሎት አዋጆች እንዲሁም የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጆች ላይ የተደረጉ ለዉጦች ሰብአዊ መብቶችን በማክበርና ማስከበር ሂደት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸዉ ናቸዉ፡፡

ነጻና ገለልተኛ የሆነ ምርጫ ቦርድ በማቋቋም በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ነጻና ገለልተኛ የሆነ ምርጫ መደረጉን እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪያዎች ከካቢኔ ሚኒስትርነት ጀምሮ በተለያየ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተመድበዉ አገራቸዉን የሚያገለግሉበት አዲስ የፖለቲካ ባህል መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

የሰብአዊ መብቶችን መከበር በገለልተኝነት የሚያረጋግጥ ተቋም በመፍጠር ረገድም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በአለም አቀፍ ደረጃ እዉቅና ያገኘበትና ከዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ጋር በጋራ በመስራት ያሳዬዉ ብቃትና ገለልተኛነት የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብአዊ መብቶች መከበርና ለተቋማት ግንባታ ላለዉ ቁርጠኝነት ዋና ማሳያ ሆኖ የሚቆጠር ነዉ፡፡

ይሁን እንጅ አሉ አቶ አለምአንተ አግደዉ ይህ የፖለቲካና ዴሞክራሲ ለዉጥ ዉጤት መንግስት በከፍተኛ ተግዳሮት ዉስጥ ሆኖ ያስመዘገበዉ ሲሆን በአገራችን በተደረገዉ የአመራር ለዉጥ እና ይህን ተከትሎ በታወጀዉ አጠቃላይ ማሻሻያ ሥራ ጥቅማችን ይነካል ብለዉ የሰጉ በሙስና፣ በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተሳታፊ የነበሩ የቀድሞዉ የአፈና ሥርዓት ተዋናዮችና የሕወሃት የሽብር ብድን አባላት በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን ላለመስጠት ካደረጉት መከላከል ባሻገር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶችን በማስነሳት እና ኢ-ህገ መንግስታዊ ምርጫ በማድረግ በግላጭ ሕገ-መንግስት መጣሳቸዉን ገልጸዋል፤
ይህም ሆኖ መንግስት በሆደ ሰፊነት በአገር ሽግሌዎች እና በኃይማኖት አባቶች አማካኝነት ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት በተደጋጋሚ ጊዜ ያደረገዉን ጥረት በጀብደኝነት በመግፋት ከሁለት አስርት አመታት በላይ አገሩንና ድንበሩን ሲጠብቅ በነበረዉ የአገር መከላከያ ሠራዊታችን የሰሜን ዕዝ ላይ አሰቃቂ ጥቃት በመፈጸም የመከላከያ አመራሮችን ጨፍጭፏል፣ከከባድ እስከ ቀላል የጦር መሰሪያ ዘርፏል፣ ዋና ዋና መሰረታዊ የልማት አዉታሮችን አዉድሟል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ተገዶ በገባበት በዚህ ጦርነት በአጭር ጊዜ ዉስጥ የሽብር ቡድኑን ይዞታ በመቆጣጠር በትግራይ ክልል ሕግና ስርዓት ማስከበር የቻለ ሲሆን መንግስት የሰብአዊ እርዳታ በአግባቡ እንዲደርስ፣ የአካባቢዉ አርሶ አደር የእርሻ ሥራዉን እንዲሰራ ፤ በሌላም ጊዜ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያደረገዉ ጥረት ባለመቀበል በሦስት የተለያዩ ዙሮች ጦርነቱን ወደ አማራና አፋር ክልሎች በማስፋፋት ለጊዜዉ ተቆጣጥረዋቸዉ በነበሩ ቦታዎች ከፍተኛ ሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ፣ የመንግስትና የግል ተቋማትን የማዉደም የሽብር ተግባር ፈጽመዋል፡፡

ይህ ግጭት በህ.ወ.ሃ.ት አሸባሪ ቡድን ስለመቀስቀሱ በራሱ የህወኃት አመራሮች ጥቃቱ በተፈፀመበት ጊዜ አካባቢ በማን አለብኝነትና ጀብደኝነት ይገለጽ የነበረ ሲሆን ግጭቱን ተከትሎ የተከሰቱ የሰብዓዊ መብቶችና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕጎች ጥሰቶችን ለመመርመር በተ.መ.ድ. የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተቋቋመው ጥምር የምርመራ ቡድን (Joint Investigation Team) ባወጣው ሪፖርት ላይ በማያሻማ ሁኔታ ያረጋገጠው እውነታ መሆኑን፣ ኢትዮጵያ ጥምር የምርመራ ቡድኑ ያወጣውን ሪፖርት በመቀበል አስፈላጊ ቀጣይ ስራዎችን ለማከናውን የሚኒስትሮች ግብረሃይል በመመስረትና ሴክሬታሪያት በማደራጀት በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደች ቢሆንም የጥምር ምርመራ ቡድኑን ግኝቶችና ምክረ-ሃሳቦች ወደጎን በመተው የሰብዓዊ መብቶችን ጉዳይ ለፖለቲካ አጀንዳ ለመጠቀም የሚፈልጉ ወገኖች ባደረጉት ግፊት እና ባስከተሉት ጫና በተ.መ.ድ. የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ሌላ ኮሚሽን መቋቋሙንም ሆነ የኮሚሽኑን ገለልተኝነት የጎደለው በመረጃ ላይ ያልተመሰረተ ሪፖርት ሀገራችን የማትቀበለው ስለመሆኑ፣ በኢትየጵያ መንግስት በኩል ግጭቱ በሰላም እንዲፈታ ከፍተኛ ፍላጎትና ዝግጁነት ቢኖርም በአሁኑ ወቅት ሶስተኛ ዙር ግጭት በኅወኃት ሀይሎች መከሰቱን እና ይህም ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሚሆን በሚኒስትር ድኤታዉ ተገልጿል፡፡

ከመክፈቻ ንግግሩ በኋላ በሁለት ዙር በተካሄደው የጥያቄና ምላሽ የመስጠት ሂደት ከዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን ኮሚቴ አባላት በርካታ ጥያቄዎች በልዑካን ቡድኑ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በመጨረሻም ሚኒስትር ዴኤታዉ አቶ ዓለምአንተ አግደዉ ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ መብቶችን ለማክበርና ማስከበር የሚያስችሉ ሰፊ የለዉጥ ሥራዎችን መስራቱን ገልጸዉ በቀጣይ የሰብአዊ መብት ኮሚቴዉን ጨምሮ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር ሁሉ ተባብሮ በመስራት የተሻለ ዉጤት ማስመዝገብ እንደሚጠበቅበት ገልጸዉ የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን የሚያደርገዉ ቁርጠኛ የለዉጥ መንግስት በመሆኑና ዜጎቹ ሰብአዊ መብታቸዉና ክብራቸዉ ተጠብቆ መኖር የሚገባቸዉ መሆኑን በፅኑ የሚያምን በመሆኑ እንጅ ማንንም ለማስደስት አለመሆኑን ጠቅሰዉ በዚህ ረገድ የሚደረግን ከፖለቲካ ፍላጎት የሚመነጭ ጣልቃ ገብነት አገራቸዉ እንደማትቀበልና እነደማታስተናግድ ገልጸዋል፡፡

በክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የተመራው የኢትየጰያ የልዑካን ቡድን ጄኔቫ የሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ቋሚ መልዕክተኛ ጽ/ቤት ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አቶ ዘነበ ከበደን ጨምሮ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችን እንዲሁም የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርን ያካተተ ነበር፡፡

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፍትሕ ሚኒስቴር

Exit mobile version