ETHIO12.COM

ዳንኤል ክብረት ለሶስተኛ ጊዜ – የሚዲያ ቦርድ አመራሮች ተሾሙ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) እና ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባላትን ሹመት በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁ ተሰምቷል። የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሠ ቱሉ የኢቢሲ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ሲሾሙ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ደግሞ ለሶስት ተከታታይ ጊዜ በፕሬስ ድርጅት የቦርድ በአባልነት በመሾም ብቸኛው መሆናቸው ተጠቁሟል።

በሃሚድ አወል

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) እና ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባላትን ሹመት በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ። የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሠ ቱሉ የኢቢሲ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ሲሾሙ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ደግሞ ለሶስት ተከታታይ ጊዜ በፕሬስ ድርጅት የቦርድ በአባልነት በመሾም ብቸኛው ሆነዋል።

የብሔራዊ ቴሌቪዥን እና ሬድዮ ጣቢያዎችን በስሩ ለሚያስተዳድረው ኢቢሲ በቦርድ አባልነት የተሾሙት ግለሰቦች ዘጠኝ ናቸው። ተጠሪነቱ ለተወካዮች ምክር ቤት ለሆነው ኢቢሲ የቦርድ አባላት የሚሰየሙት፤ አግባብነት ካላቸው ተቋማት እና ከልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወጣጥተው መሆኑን በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ሰፍሯል። የቦርድ አባላቱ የሚሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት እንደሆነ በአዋጁ ተደንግጓል።

በሶስት ድምጸ ተዐቅቦ ሹመታቸው ከጸደቀላቸው የአቢሲ ቦርድ አባላት መካከል የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዩሱፍ ኢብራሂም ይገኙበታል። አቶ ዩሱፍ ካለፈው ዓመት መስከረም 2014 ጀምሮ የአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ኃላፊ ሆነው በመስራት ላይ ያሉ ናቸው። 

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቦርድ ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በአባልነት ሲካተቱ የአሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ አይለም። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ከዚህ ቀደም በነበረው ቦርድ ውስጥ አባል ሆነው አገልግለዋል። 

በዛሬው ሹመት፤ የኢቢሲን የስራ አመራር ቦርድ ላለፈው አንድ ዓመት ገደማ በሰብሳቢነት ሲመሩ የቆዩትን ዶ/ር አለሙ ስሜን በመተካት ቦታውን የተረከቡት፤ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሠ ቱሉ ናቸው። የቀድሞው መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትር የነበሩት አቶ አህመድ ሽዴ እና ጌታቸው ረዳም እንዲሁ በተለያዩ ጊዜያት የኮርፖሬሽኑን ቦርድ በሰብሳቢነት መርተዋል። 

በዛሬው የኢቢሲ ቦርድ አባላት ሹመት ዝርዝር ውስጥ አዳዲስ ተሿሚዎች ተካትተዋል። የፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተርን ለ19 ዓመታት የመሩት የሚዲያ ባለሙያው ዶ/ር ንጉሴ ተፈራ ከተሿሚዎቹ አንዱ ናቸው። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቋንቋዎች ጥናት መምህሯ ዶ/ር ሙና አቡበከር፣ የትምህርት ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዋ ወ/ሮ አመለወርቅ ህዝቄል በቦርድ አባልነት ከተሾሙት ውስጥ ይገኙበታል። 

በዛሬው የፓርላማ ውሎ፤ ከኢቢሲ በተጨማሪ ዕለታዊዎቹን “አዲስ ዘመን” እና “ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ” ጋዜጦች የሚያሳትመው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ዘጠኝ የቦርድ አባላት ተሹመውለታል። የፕሬስ ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ምህረት ደበበ ናቸው።

የፕሬስ ድርጅትን ቦርድ በሰብሳቢነት ሲመሩ የቆዩት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲ ነበሩ። ከአቶ አወሉ በፊት የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ካሳሁን ጎፌ በተመሳሳይ ቦርዱን በሰብሳቢነት መርተውታል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ፍሬህይወት አያሌውም የቦርዱ ሰብሳቢ ነበሩ።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለሶስት ተከታታይ ጊዜያት በፕሬስ ድርጅት ቦርድ አባልነት በመሾም ብቸኛ ሆነዋል። ዲያቆን ዳንኤል ለመጀመሪያ ጊዜ የተሾሙት በሐምሌ 2010 ዓ.ም ነበር። በተመሳሳይ ከሁለት ዓመት በፊት በመጋቢት 2012 የተቋሙ የቦርድ አባላት ሲሾሙ፤ ዲያቆን ዳንኤል ለሁለተኛ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አቅራቢነት ተሹመዋል። 

የዲያቆን ዳንኤል ሹመት በወቅቱ ሲጸድቅ ባልተመለደ መልኩ ከፓርላማ አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። ሹመቱ በቀረበት ዕለት ስብሰባውን ከታደሙ የፓርላማ አባላት መካከል 129 ያህሉ የተቃውሞ ድምጻቸውን የሰጡ ሲሆን 27 የፓርላማ አባላት ደግሞ ድምጽ ከመስጠት ታቅበው ነበር። አከራካሪው የዲያቆን ሹመት በወቅቱ የጸደቀው በ146 የፓርላማ አባላት ድጋፍ፣ በአብላጫ ድምጽ እንደነበር ይታወሳል። 

የፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባላት ሹመት ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ በፊት ይህን መሰሉን ተቃውሞ ቢያስተናግድም፤ በዛሬው የፓርላማ ውሎ ግን ከአንዲት የምክር ቤት አባል ድምጽ ተዐቅቦ በስተቀር በሹመቱ ላይ ተቃራኒ አስተያየት እንኳ አልቀረበም። በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ከተገኙ 244 የፓርላማ አባላት መካከል 243ቱ ለቦርዱ አባላቱ ሹመት ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን እና የኢቢሲ የስራ አመራር ቦርድ አባላት ሹመት “ከጾታ ስብጥር” አንጻር የገመገሙ አንድ የፓርላማ አባል፤ የሴቶች ድርሻ መስተካከል እንዳለበት አሳስበዋል። ተስፋነሽ ተፈሪ የተባሉት እኚሁ የምክር ቤት አባል ለፓርላማ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት የቦርድ አባላት ሹመት ላይ የሴቶች ቁጥር ማነሱን አንስተው፤ “የሴቶች ድርሻ ሃምሳ በመቶ መሆን አለበት” የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪው አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤ የሁለቱ መስሪያ ቤቶች የቦርድ አባላት ምልመላ ሲደረግ ታሳቢ ከተደረጉ ነጥቦች መካከል “የወጣቶችና ሴቶችን ተሳትፎ እና ውክልና” አንዱ መሆኑን ለአባላቱ ተናግረዋል።

ፕ/ር መሐመድ አብዶ የተባሉ ሌላ የፓርላማ አባል “ሹመቶች ሲጸድቁ በጅምላ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ስም እየተጠራ ቢሆን፤ አንዱ አንዱ ላይ ተደርቦ፣ ጠንካራ ያልሆነው ጠንካራው ላይ ተደርቦ እንዳያልፍ ይጠቅማል” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። ፕ/ር መሐመድ የፓርላማ አባላት ለሹመት በቀረቡ “በእያንዳንዱ ዕጩዎች ላይ አስተያየት ሊሰጡ ይገባል” የሚል ሃሳባቸውን አንጸባርቀዋል።

የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፤ ፕ/ር መሐመድ ላነሱት አስተያየት በሰጡት ማብራሪያ “የሚያከራክር ጉዳይ ካለ ባከራከረው ተሿሚ ግለሰብ ላይ ለብቻው ድምጽ ይሰጥበታል። በዛሬው ላይ በተለየ መልኩ የቀረበ ባለመኖሩ ነው። በተለየ መልኩ ከቀረበ [ግን] በተለየ መልኩ ጉዳዩ በቀረበበት አካል ላይ ለብቻው ድምጽ ይሰጣል” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Exit mobile version