Site icon ETHIO12.COM

አማራ ፓይፕ ፋብሪካ በ2014 በጀት ዓመት ከ189 ሚሊዬን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ


– ፋብሪካው በ2015 በጀት ዓመትም የተጣራ 265 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ማቀዱንም አስታውቋል

አማራ ፓይፕ ፋብሪካ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በ2014 በጀት ዓመት ያከናወነውን ተግባራት ግምገማና የ2015 ዓ.ም የእቅድ ትውውቅ አድርጓል።
ፋብሪካው በ2015 በጀት ዓመትም የተጣራ 265 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ማቀዱንም አስታውቋል።

የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ወርቁ ባየ ፋብሪካው በባለፈው በጀት ዓመት 1 ነጥብ 2 ቢሊዬን ብር ገቢ ለማግኘት በማቀድ 953 ነጥብ 8 ሚሊዬን ብር ገቢ ማግኘቱን አስረድተዋል። ከ2013 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃጸር 300 ሚሊዬን ብር በላይ ብልጫ ማግኘቱን ነው አቶ ወርቁ ያስረዱት። ዋና ሥራ አሥኪያጁ እንዳሉት ፋብሪካው ይህን ውጤት ማስመዝገብ የቻለው ሀገሪቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ነው።

በባለፈው በጀት ዓመት189 ሚሊዬን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘት እንደተቻለ ዋና ሥራ አሥኪያጁ ገልጸዋል።

አቶ ወርቁ እንዳሉት ፋብሪካው በተከታታይ ዓመታት ትርፋማ ሲኾን ታማኝ ግብር ከፋይ በመኾኑ በተደጋጋሚ ተሸላሚ መኾን ችሏል።

ፋብሪካው ከክልሉ ባለፈም በመላ ሀገሪቱ ተደራሽ በመኾን እያገለገለ እንደሚገኝ አቶ ወርቁ አንስተዋል። ፋብሪካው ማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይም አስተዋጽኦ በማድረግ የበጎ አድራጎት ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ፋብሪካው 10 ሺህ ሜትሪክ ቶን ለማምረት አቅዷል ነው ያሉት። በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 59 ቢሊዬን ብር ሽያጭ ለማከናወን ማቀዱንም ዋና ሥራ አሥኪያጁ አብራርተዋል። እቅዳቸውን ለማሳካት የኀይል መቆራረጥና የውጭ ምንዛሬ ችግር ተግዳሮት ሊገጥማቸው እንደሚችል እንደ ስጋት አቶ ወርቁ አንስተዋል።

የፋብሪካው የቦርድ የሥራ አመራር አባላት የፋብሪካውን የውስጥ ችግር በመለየት መፍትሔ እንዲሰጡ ጠይቀዋል። ሠራተኞቹ ፋብሪካው ጥቅማጥቅማቸውን ሊያስጠብቅና ሊያከብር እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የቦርድ ሥራ አመራር ሰብሳቢ ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር) የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ የበለጠ ትርፋማ እንደሚኾን ቦርዱ ያምናል ብለዋል። ለዚኽም ቦርዱ የሚሠራውን ለይቷል ነው ያሉት።

ፋብሪካው ለረዥም ጊዜ የሠራ በመኾኑ ማሽኖችን ማደስ ያስፈልጋል ብለዋል። ማሽኖችን የመተካትና የማስፋፋት ሥራን ለመሥራት የሥራ አመራር ቦርዱ የልየታ ሥራ መሥራቱን ዶክተር ሰማ ጠቁመዋል።

ፋብሪካው ምርቱን በተሻለ ወደ ውጭ እንዲልክ ቦርዱ ጠንክሮ እንደሚሠራም ነው የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢው የጠቆሙት። “ፋብሪካው ግቡን እንዲያሳካ የፋብሪካው ሠራተኞች ደስተኛ መኾን ስላለባቸው የሥራ አመራር ቦርዱ በጥናት ላይ የተመሰረተ ምላሽ ይሰጣል” ብለዋል።

ፋብሪካው ቀጣይነት ሲኖረው ሠራተኞችም ተጠቃሚ ስለሚኾኑ ፋብሪካውን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

ዶክተር ሰማ የፋብሪካው ሠራተኞች የበለጠ በሥራቸው በመትጋት ፋብሪካውንም ኾነ ራሳቸውን እንዲያሳድጉ ጠይቀዋል።

ከፋብሪካው ሠራተኞች መካከል በታታሪነታቸው ተሸላሚ ከኾኑት አንዱ አቶ አበራ ሞገስ ሠራተኞች በታታሪነታቸው ቀንና ማታ እንደሚሠሩ ተናግረዋል። ሽልማቱ የበለጠ ተነሳሽነትን እንደሚፈጥርላቸውም ጠቁመዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል።

Exit mobile version