Site icon ETHIO12.COM

ከሁሉም በላይ ዋናው [ማህበራዊ ትስስሩ መበጠስ] ሬድዋን ሁሴን

አምባሳደር ሬድዋን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የድህነነት አማካሪ ከሆኑ በሁዋላ ከትህነግ ጋር ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት ለዲፕሎማቶችና ለሚዲያዎች፣ እንዲሁም በራሳቸው ቲወተር የሚገልጹበት መንገድ በዜጎች ዘነዳ ቀልብ የሚስቡ በሳል ፖለቲከኛ አድርጓቸዋል። ፓርቲያቸውን የሚጠሉና ዕለት ዕለት ቁጭ ብለው የሚሰድቡ ሳይቀሩ ” ሬድዋንን አለማድነቅ አይቻልም” ሲሉ ተሰምተዋል። በሰላም ድርድሩ ዙሪያም ቁልፍ ሚና ስለመጫወታቸው እየተመሰከረላቸው ነው። ቢቢሲ በትንሹ አናግሯቸዋል።

ቢቢሲ፡ በናይሮቢ በተካሄደው የድርድር ሂደት ላይ ዋና ዋና ፈተናዎች ምን ምን ነበሩ?

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፡– ዋናው የዚህ ሂደት ፈተና ያለመተማመን ነበር። በሦስት ዙር ጦርነት ውስጥ አልፈናል። እንዲሁም ክሶች፣ የመልስ ክሶች ብሎም በርካታ ጉዳዮች ነበሩ። ጥልቅ የሆነ ያለመተማመን ስለነበረ ሁለቱንም ወገኖች የሚያሳስቡ ጉዳዮችን ለማስተካከል ስንሰራ ነበር።

ስለዚህ በመካከላችን የነበረውን ልዩነት ለመሙላት እና ወደ ጋራ መስማማት ለመምጣት የሄድንበት መንገድ ሌላኛው ነበር። በተጨማሪ የፌደራል መንግሥቱም የራሱ የሚወክለው ሕዝብ አለ ሌላኛውም ወገን የወከለው ሕዝብ አለ። ሁለቱም አካላት የወከሉት ሕዝብ ሲጠብቀው የነበረ ነገር አለ። ስለዚህ ትክክል ያልሆነ መልዕክት ሊያስተላልፉ ይችላሉ ያልናቸውን ጉዳዮች በጋራ ማስተካከል ነበረብን።

በዚህ ሂደት እያንዳንዱን ሰነድ መመልከት እና የበለጠ ማስተካከል ነበረብን። ይህንን ማድረጋችን የሰላም ሂደቱ ጸንቶ እንዳይቆም የሚያደርጉ መልዕክቶች እንዳይኖሩት ለማድረግ በቅን ልቦና የተደረገ ነው ግን ፈታኝ ነበር። ምንም እንኳን ይህ ስምምነት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ማስፈጸሚያ ስለሆነ ቀለል ያለ ይሆናል ተብሎ ቢታመንም በነበረው ያለመተማመን የተወሰነ ከባድ አድርጎት ነበር።

ፖለቲካዊ ስምምነት የነበረው የፕሪቶያው ከባዱ እና አስቸጋሪው እርሱ ነበር። ይሔኛው የፕሪቶሪያውን ስምምነት በወታደራዊ እና ደኅንነት ዐይን በመመልከት ለማስፈጸም የወታደራዊ መሪዎች የሚስማሙት ነው። ወታደራዊ አዛዦች ናቸው ለመፈጸም የሚያስቸግረውን እና የማያስቸግረውን የሚረዱት። ነገር ግን ከጅማሬው ጀምሮ ተይዘው የመጡ ያለመተማመኖች ነበሩ።

ለዚያም ነው ረዘም ላለ ጊዜ ተቀምጠን ልዩነቶችን ለማስተካከል የሞከርነው። ነገር ግን በመጨረሻ ይህንን ሁሉ አልፈን ስምምነቱን ፈርመናል። ከዚህ በኋላ ያለው ኃላፊነት የእኛ ነው። ከእኛ የሚጠበቀውን ነገር ተረድተን ማስተካከል፣ በቁርጠኝነት መቀጠል እንዲሁም ይህንን ስምምነት ለማስፈጸም በምናደርገው ጥረት የሚገጥሙ እንቅፋቶችን ማለፍ ያስፈልጋል። ነገር ግን በመጨረሻ ስኬታማ ሆኖ ተጠናቋል።

ቢቢሲ፡ በፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ እንደተጠቀሰው የሽግግር ፍትህ የሂደቱ አካል ይሆናል። ነገር ግን ይህ የፖለቲካ ሂደት የፍትህ ሂደቱን እንዳይሸፍን ስጋት አለ። በዚህ ጦርነት ከፍተኛ የመብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ዜጎች ፍትህ ብሎም ካሳ እንዲያገኙ የፌደራል መንግሥቱ ምን ያህል ቁርጠኛ ነው?

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፡ በዚህ ጦርነት አረመኔያዊ ድርጊቶች ተፈጽመዋል። አንዳንዶቹ በማስረጃ መደገፍ ይገባቸዋል። ሌሎቹ ሰፊውን ምስል መመልከት ይጠይቃሉ። ዋናው ችግር እነዚህ አረመኒያዊ ድርጊቶች ብቻ አይደሉም። ነገር ግን የተጎዳው ማኅበራዊ ትስስር ነው።

ባለፉት 30 ዓመታት ብዝሃነትን ከልክ በላይ ፖለቲካዊ በማድረግ እና የጋራ ማንነታችንን እና ጥቅሞቻችንን በመዘንጋት የተጎዳውን ይህንን ማኅበራዊ ትስስር በመጠገን ነው ይህንን መፍታት የምንችለው። ይህንን መፍታት የምንችለው ማኅበረሰቡ በራሱ መንገድ የራሱን የጋራ ኢትዮጵያዊነት ፈልጎ እንዲያገኝ በማድረግ ነው።

ነገር ግን በርግጥም የተፈጸሙ ወንጀሎች በማስረጃ መደገፍ፣ ብሎም ከፍተኛ ወንጀሎችን የፈጸሙ አጥፊዎች በፍርድ ቤት ቀርበው ተጠያቂ መሆን ይገባቸዋል። ይህ ብቻ ግን አይደልም። በርካታ የጥቃት ሰለባዎች በፍርድ ቤት እና በይቅር መባባል ሂደት ብቻ ሳይሆን መካስ ብሎም ያጡትን ኖሯቸውን ለመመለስ መሰራት አለበት።

ከዕለት ተዕለት ኖሯቸው መጎዳት ባለፈም የሥነ ልቦና ጠባሳም ገጥሟቿል። ስለዚህ ይህ [በስምምነቱ ላይ የተጠቀሰው] የፍትህ ሂደት ማኅበራዊ ቁስሎቻችን ለማሻር ብቻ ሳይሆን ወንጀለኞችን ወደ ፍርድ ቤት በማቅረብ ፍትህን ማሰጠትን ያጠቃልላል።

ቢቢሲ፡ በዚህ የሰላም ስምምነት ሂደት ውስጥ ቀጣዩ ሂደት ምንድነው? ቀጣይ ፈተናዎች ይሆናሉ ብላችሁ የምትጠብቁት ምንድነው?

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፡ ይህንን ሰላም ማምጣት መቻላችን በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ ችግሮችን ለመፈታት ዕድል ይሰጠናል። እንዲሁም ይህንን ችግር መፍታት ከቻልን በቀጣይ አገራችንን መልሶ ለመገንባት ዕድል እሰጠናል። ይህ በቀጣይ ልዩነቶቻችን ወደ ግጭት አጣብቂኝ ከመግባታችን ቀደም ብለን እንዴት መፍታት እንዳለብን ትምህርት ይሰጠናል ብዬ አስባለሁ።

ይህ የሰላም ሂደት ኢትዮጵያዊያን ይህንን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ችግሮቻቸውን በአካታች ፖለቲካዊ ውይይት መፍታት እንደሚገባ ምሳሌ ይሆናል። ሁሉም አካል ሊሰማበት የሚችልበትን መድረክ በመክፈት ልዩነትን መፍታት እንደሚቻል ያሳያል።

Exit mobile version