ETHIO12.COM

 “ትህነግ አልወከለንም፣ ትህነግ አልፈረም … መግለጫው ልክ ነው” አቶ ጌታቸው

 …ህወሓት አልፈረመም፣ ህወሓት አልፈረመም! የትግራይ መንግሥት ነው የሄደው። የትግራይን መንግሥት ስለማናውቀው ህወሓት እንላችኋለን አሉን። እኛ ሰላም ነው የምንፈልገው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የትግራይ መንግሥት በሉን ሕዝብ መርጦናል ብለን ብንከራከር የአፍሪካ ኅብረት አይሰማ፣ ማንም አይሰማ። በሕግ አናወቃችሁም አሉ

አቶ ጌታቸው መቀለ ከገቡ በሁዋላ ለቢቢሲ ሰፊ መግለጫ ሰጥተዋል እንዳለ ቀርቧል።

በደቡብ አፍሪካ የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት የተኩስ አቁም፣ ትጥቅ መፍታት እና ሌሎች ጉዳዮችን ያካተተ ባለ 12 ነጥብ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በኬንያ የተደረገው ውይይት ባለፈው አርብ ተጠናቋል።

ሁለቱ ወገኖች በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ቅዳሜ ኅዳር 03/2015 ዓ.ም. በናይሮቢ ተፈራርመዋል።

ህወሓትን ወክለው የፕሪቶሪያን ስምምነት ከተፈራረሙት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ባለፈው ዕሁድ ናይሮቢ ውስጥ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የልዑካን ቡድኑ “የትግራይን መንግሥት” እንጂ ህወሓት የሚወክል አይደለም ይላሉ።

ከአቶ ጌታቸው ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል።

ቢቢሲ፡ በትግራይ አሁን ተኩስ ሙሉ በሙሉ ቆሟል?

አቶ ጌታቸው፡ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ቆሟል። ትናንት (ቅዳሜ) በፀለምቲ አንዳንድ አካባቢዎች የአማራ ልዩ ኃይል እንቅስቃሴ እንደነበር አውቃለሁ። ማደናቀፍ ይሁን ወይስ ሌላ የምናየው ይሆናል። ቢያንስ ግን በማዕከላዊ መንግሥት እና በትግራይ መንግሥት መካከል ያለው ግጭት ቆሟል።

ቢቢሲ፡ በፕሪቶሪያ እና ናይሮቢ የተደረጉት ድርድሮች በተደጋጋሚ ሲራዘሙ ነበር። ስምምነት ላይ ለመድረስ እንቅፋቶች ነበሩ?

አቶ ጌታቸው፡ ነበሩ፤ በሁለት ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው ድርድር ከዘገየ ያልተስማማንበት ነገር ነበር ማለት ነው። ዋናው የአመለካከት ነው። ወደ ፕሪቶሪያ ስንሄድ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል መቀሌ እየገባሁ ነው ወይም መቀሌ እገባለሁ የሚል ተስፋ ነበር።

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ኃይሎች እንቅስቃሴያቸው እንደዛ ነበር። ስለዚህ የመከራከር ፍላጎታችንን የመቀነስ ፍላጎት የነበረ ይመስላል። በየቀኑ የሚለወጡ ነገሮችም ነበሩ። ሀሳቦች በየቀኑ ይለወጣሉ። ለማንኛውም መቶ በመቶ ለማግኘት ነው የሄድነው፤ ግን ሁሉንም ነገር አታገኝም።

በጦርነቱ ውስጥ የውጭ ኃይሎች ስለመኖራቸው ጥያቄ ይነሳ ነበር። ተኩስ እናቆማለን ይሉና፣ በተኩስ አቁም ደረጃ ውስጥ መነሳት የሌለባቸውን ብዙ ነገሮችን ያነሳሉ። በጊዜ ሂደት ሊነሱ የሚገባቸው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ያነሳሉ፣ እኛም እናነሳለን። በሆነ ምክንያት ውድቅ ይሆናል። እንደገና ይቀጥላል።

ለማንኛውም ካለው ሁኔታ አንጻር የወሰንነው፣ ለትግራይ ሕዝብ እና መንግሥት የተሻለ የመደራደር አቅም ለመፍጠር ይበጃል ያልነውን ነው። መቶ በመቶ የተስማማንበት ነው ማለት አይደለም። ነገር ግን ከተስማማን በኋላ ትግበራቸው የሚታይ ጉዳዮች የራሳቸው ትርጉም ስለሚኖራቸው ብዙ የሚያከራክሩ ነገሮች ነበሩ።

ቢቢሲ፡ ስምምነቱ በቀጥታ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል። በዚህም መሰረት የትግራይ ኃይሎች በ30 ቀናት ውስጥ ትጥቅ እንደሚፈቱ ተጠቅሷል። በአንጻሩ በሰብአዊ እርዳታ ሌሎች ጉዳዮች ላይ የጊዜ ገደብ አልተቀመጠም። ሰብአዊ እርዳታ መቼ ነው የሚገባው? የጊዜ ገደብ እንዲቀመጥ ምን አደረጋችሁ?

አቶ ጌታቸው፡ ትጥቅ በ30 ቀናት ውስጥ ይወርዳል ወይስ አይወርድም? ሌላ ጉዳይ ነው። በፕሪቶሪያ የ30 ቀን ሀሳብ አቅርበው፣ ስድስት ወር ወይም አስር ወር ማለቱ ብዙም ትርጉም ስለሌለው ሁለቱም አዛዦች በተግባር አጥንተው ምን ያህል ቀናት እንደሚያስፈልግ ይወስናሉ።

ትጥቅ የምንፈታው ሕዝባችንን ለማዳን ነው። ትጥቅ አንስተን ሕዝባችንን የምንታደግበትን ዕድል አይተናል፤ ታግለናል። ጥሩ ሥራ ሰርተናል። እስከነ ትጥቃችን ሕዝቡ የዘር ማጥፋት የሚፈጸምበትን ሁኔታ ካየን ይህንን ማስወገድ ስላለብን በሰላማዊ መንገድ ሰዎች የሚታደጉበት ሁኔታ ካየን ወደ ሰላም የማንመጣበት ምንም ምክንያት የለም ብለን ነው ወደዚህ ጉዳይ የገባነው።

ስለዚህ ትጥቅ መፍታት ከምንም በላይ ከትግራይ ደኅንነት ጋር መያያዝ አለበት የሚል ጥያቄ አነሳን። እናም በዚሁ ጸናን። ከትግራይ አንጻር የተሰለፈው ኃይል ብዙ ነው። የአካባቢ ኃይሎች አሉ። የፌዴራል መንግሥት የሚባል ኃይል አለ። የኤርትራ ኃይል አለ። ስለዚህ እኛ የትጥቅ ፍላጎት [ኖሮን] አይደለም፤ የሕዝባችንን ደኅንነት ለመጠበቅ ነው። ስለዚህ የወገኖቻችን ደኅንነት በአንዳቸው የሚጠበቅ ከሆነ ትጥቅ መፍታት እጅ እንደመስጠት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም።

ግን ዋናው ነገር ሕዝባችን በሰላም መኖር ይችላል ወይ? ወደ ነበረው መመለስ ይቻላል ወይ? የሚል ነው። ስለዚህ እነዚህ በየቀኑ መሳርያ የሚያወዛውዙ ሕዝባችንን የሚጨፈጭፉ ኃይሎች እዚያ አለመኖራቸውን ማረጋገጥ አለብን። ስለዚህ እኛ ራሳችን እናስወጣቸዋለን ካሉ እስከነ ትጥቃችን የምንቀጥልበት ምንም ምክንያት የለም። ነገር ግን ሁኔታው ​​በአንድ ወር ወይም በዓመት ውስጥ ያበቃል የሚለው ሰዎቹ ሲገናኙ የሚያደርጉት ይሆናል።

የሰብአዊ እርዳታ ከትናንት በስቲያ (አርብ) መጀመር ነበረበት። ሰብአዊ እርዳታ የፖለቲካ መሳሪያ የሚሆንበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም ነበር። ስለዚህ ግጭቱ የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ የሚገታ ከነበረ አሁን ግጭቱ ስለቆመ መጀመር ይችላሉ። ተስማምተናል። እንደእኔ ከሆነ ዛሬ (ቅዳሜ) መንቀሳቀስ እንሚጀምሩ ነው።

በተለይ በናይሮቢ የሰብዓዊ ዕርዳታ ኤጀንሲዎች የውይይቱ አካል ነበሩ ማለት ይቻላል። ስለዚህ አውሮፕላኖች ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ፤ የትግራይ እና የፌደራል ኃይሎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተወያይተዋል። ስለዚህ በእኔ እምነት እርዳት ለመጀመር የሚከለክል ነገር የለም።

ቢቢሲ፡ ለምን ዘገየ ብለው ያምናሉ?

አቶ ጌታቸው፡ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ድርድር መግባት አልነበረበትም። ነሐሴ 18 ግጭት ሲያነሱ የቆመ ነገር አለ። እርዳታው በሚመጣበት አፋር አካባቢ ምንም ዓይነት ግጭት አልነበረም። ቆሞ ነው። ስለዚህ ጥሪ ነው ልታቀርብ የምትችለው። እጅህ ላይ ለሌለ ነገር ጥሪ ከማቅረብ በቀር ምን ማድረግ ትችላለህ? ስለዚህ ለምን ተቋረጠ? እርዳታን የጦር መሣሪያ ለማድረግ ካለው ፍላጎት የተነሳ ተቋርጧል ብዬ አምናለሁ። አሁን ስምምነት ላይ ደርሰናል። እንልካለን ብለዋል፤ እናያለን።

ቢቢሲ፡ ግን የመዘግየቱ ምክንያት ምንድን ነው? የኢትዮጵያ መንግሥትም ብዙ እርዳታ እየገባ ነው እያለ ነው?

አቶ ጌታቸው፡ ይህ ስህተት ነው፤ እውነታው ሰብአዊ እርዳታ የሚሰጡት በደንብ የሚየውቁት ነው። እንዲህ አይነት ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። እኛ ግን ብዙ መናገር አልፈለግንም። የናይሮቢው ድርድር እስኪጠናቀቅ ድረስ፥ ለትግራይ ሕዝብ በተወሰነ ደረጃ እርዳታ እንዲደርስ፣ ተኩስ እንዲቆም፣ አካሄዱ የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ እድል እንዲፈጠር፣ ምንም እንኳን ሕዝባችን የመረጃ እጥረት እያለው እንኳ ብዙ ሀሳብ ቢያቀርብም ብዙ መናገር አልፈለግንም። ይህ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሊውል እንደሚችል እንረዳለን።

አሁን ግን ዋናው ትኩረታችን ይህ ጉዳይ ይሰራል ወይስ አይሰራም የሚለው ነው። ዞሮ ዞሮ ለትግራይ ሕዝብ ህልውና እና ደኅንነት የማይጠቅም ከሆነ እኔ ስላልኩት ወይም ፊርማው ስለተፈረመ መቆየት ይችላል ተብሎ ሊታሰብ አይገባም።

ቢቢሲ- የኤርትራ ጦር በትግራይ ስለመኖሩና ስለመውጣቱ በስምምነቱ ላይ በይፋ የተገለጸ ነገር የለም። ምን ስለተስማማችሁ ነው እንዲገለጽ ያልተፈለገው?

አቶ ጌታቸው፡ በይፋ የኤርትራ ጦር እንዳለ እናውቃለን፤ እነሱም ያውቃሉ። የውጭ ኃይሎች በሚል የተቀመጠ ነገር አለ፣ የኤርትራ ደግሞ የውጭ ኃይል ነው። ስለዚህ በዚያ እንደሚካተት እናምናለን። ከዚህ በላይ ምን እንላለን።

ስለዚህ ስምምነቱ የውጭም ሆነ የመከላከያ ያልሆኑ ኃይሎች ትግራይን ለቀው እንዲወጡ ነው። የኤርትራን አይነሳም ካሉ እንዳይነሳ የሚፈልጉበት ምክንያት አይታየኝም። የውጭ ኃይሎች ይውጡ ከተባለ ከእኛ ጋር የሚዋጋ [ሌላ] የውጭ ኃይል ስለሌለ ምንም የሚያስጨንቀን ነገር የለም። ያለው የውጭ ኃይል የኤርትራ ነው ብለን እናምናለን። በግልጽ እንዲጠቀሱ ጸንተን እንጠይቃለን።

ሌላኛውን ወገን [ለምን እንዲጠቀስ እንዳልፈለጉ] መገመት አልችልም። የሚያገባኝ ስምምነቱ ለትግራይ የሚጠቅም ነው አይደለም የሚለው ነው። ምክንያቱም (የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝደንት) ኡሁሩ እንዳሉት ዋናው ራስ ምታት ኤርትራ የሚለው ቃል መጠቀሱና አለመጠቀሱ ብዙም ግድ የለኝም። መውጣት አለባቸው፥ መውጣት አለባቸው…

ቢቢሲ፡ ስምምነቱ በህወሓት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ነበር። የትግራይ ኃይሎች እና ህወሓት የተለያዩ ተቋማት ናቸው፣ ህወሓት የፖለቲካ ድርጅት ነው ያም ራሱን የቻለ ተቋም ስለሆነ በትግራይ ኃይሎች ፋንታ ህወሓት እንዴት ፈረመ?

አቶ ጌታቸው፡ ህወሓት አልፈረመም፣ ህወሓት አልፈረመም! የትግራይ መንግሥት ነው የሄደው። የትግራይን መንግሥት ስለማናውቀው ህወሓት እንላችኋለን አሉን። እኛ ሰላም ነው የምንፈልገው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የትግራይ መንግሥት በሉን ሕዝብ መርጦናል ብለን ብንከራከር የአፍሪካ ኅብረት አይሰማ፣ ማንም አይሰማ። በሕግ አናወቃችሁም አሉ።

ስለሆነም ስማችንን ስላልተቀበላችሁ የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገውን እርዳታ፣ የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገውን ሰላም፣ ገደል ይግባ ብለን አንቀበልም ማለት አልፈለግንም። በቡድኑ ውስጥ ያለነው የህወሓት አባላት እኔና አንድ ሰው ብቻ ነን፤ ሌሎቹ የህወሓት አባላት አይደሉም። የትግራይ መንግሥት ተወካዮች ናቸው። ስለዚህ አንዱ ወገን የትግራይን መንግሥት አላውቅም አለ። ስለዚህ የትግራይን መንግሥት ስለማያውቅ የኛ ትኩረት ተኩስ መቆም አለበት፤ ዕርዳታ መምጣት መቻል አለበት፤ አገልግሎት መቀጠል አለበት ነው።

አሁን በዚህ ጉዳይ ‘ኖ፣ አይ የትግራይ መንግሥት ብላችሁ እውቅና ካልሰጣችሁን ትግላችንን እንቀጥላለን’ ማለት ነው የሚያዋጣው ወይስ የምትሉንን በሉን ለሕዝቡ የሚጠቅም እንሰራ የሚል ነው። እና አሁን፣ ደጋግመን እየነገርናቸው ነው፣ ህወሓት ሠራዊት የለውም ትጥቅ ፍቱ ሊባል አይችልም ሥራችንን እያከበዳችሁት ነው። . . . ትጥቅ የማስፈታት ምናምን የሚለው አሰራር እንዲጀመር የትግራይ መንግሥት ኃላፊነት ይውሰድ። ስለዚህ ህወሓት የፈረመበትን አባባል እናንተም ማረም አለባችሁ።

እኔ የማወራው ስለ ህወሓት አይደለም። . . . ዋናው ነገር የልዑካኑን የላከው የትግራይ መንግሥት ነው። አንደኛው ወገን የትግራይ መንግሥት የሚባል አላውቅም ሲል፣ የአፍሪካ ኅብረት ተደራዳሪዎች ‘እና በዚህ ታፈርሱታላችሁ፤ የሆነ ስም ይስጣችሁ’ [አሉን]። ሼክስፒር ምን ይላል: “በውስጡ ጥሩ ነገር ካለ፥ የሮዝ አበባ ሌላ ስም ብትሰጣትም ጥሩ ጣዕም ይኖራታል” ይላል። ለእኔ፣ ብዙ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል አውቃለሁ። እኔ ህወሓትን ወክዬ አይደለም ወደ ፕሪቶሪያ የሄድኩት፤ የትግራይን መንግሥት ወክዬ ነው።

ቢቢሲ፡ ሰነዱን መሰረት በማድረግ ነው እየተደራደራችሁ ስላላችሁ፥ በፓርቲ መሰረት ሲተገበርና እንደ መንግሥት ተብሎ ሲተገበር አተገባበሩ ላይ ተጽእኖ አይኖረውም?

አቶ ጌታቸው፡ ሁለቱም አይደል የሚስማሙት. . . እኔ እከሌ ብዬ ነው የማውቅህ ይላል። ግደይ እንደሆንክ ነው የማውቅህ፥ በቁምነገሩ ላይ ግን እንግባባ አለኝ። እሺ እኔ ጌታቸው ነኝ፣ ግደይ ብትለኝም ቁምነገሮቹ ላይ እንስማማ አልኩት።

አሁን ትጥቅ የማስፈታት ሥራ የሕዝብን ደኅንነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ ነው ሊፈጸም የሚችለው። የትግራይ መንግሥት በሚል ቢስማሙም እኮ የትግራይ ሕዝብ ደኅንነትን ባልተጠበቀበት ሁኔታ ትጥቅ ሊፈታ አይችልም። አሁን በዚህ ህወሓት፣ መንግሥት በሚል ጨዋታ ውስጥ ለምን ትገባለህ? እውነት ነው። ይገባኛል በተደጋጋሚ ስለሚነሳ ህወሓት ወደ ፕሪቶሪያ አልሄደም፤ ወደ ፕሪቶሪያ የሄደው የትግራይ መንግሥት ነው።

ስለዚህ ሊከሰት የሚችለው ተጽዕኖ ምንድን ነው. . . እኛ ሄደን የትግራይ ጦርን በተመለከተ እንደ ትግራይ መንግሥት ሆነን ሄደን የተቀበልነው ስምምነት አለ፤ ከዚያም የጦር አዛዦች መጥተው እንደገና ያየነው ነገር አለ። እሱን አይተን የትግራይን ደኅንነት በማይጎዳ መልኩ መደረግ ያለበትን ነገር ለመስራት መጥተናል። እየሰራን ያለነው ሥራ የትግራይን ሕዝብ ለከፋ አደጋ የሚዳርግ ከሆነ እኔ ስለፈለኩ ወይም ስላልፈለግኩ ሊሆን አይችልም። እኛ ግን እንዲሰራ እንፈልጋለን።

ህወሓት ነኝ፣ መንግሥት ነኝ ምናምን የሚል እነሱ ያልተቀበሉት ነገር የትግራይ ሕዝብ ማዕከል አድርገን፣ ሰላሙን እንዲያገኝ፣ ዕርዳታ እንዲገባ፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን በፖለቲካ ለመፍታት እድል ለመፍጠር፣ እና እርዳታ እንዲገባ የሚሉትን ለሕዝቡ የሚያስፈልጉ ነገሮችን እንዲገታ ስላልፈለግን ነው እንጂ ተደራዳሪው ህወሓት እንዳልሆነ ደጋግመን ገልጸናል። ህወሓት የሚያዘው ሠራዊትም የለውም። 

ቢቢሲ፡ የማትደራደሩበት ቅድመ-ሁኔታዎች ነበሩ፤ ስምንት፣ አምስት ብላችሁ አሁን ግን ሙሉውን ተዋችሁት። ለመተው ምን አስገደዳችሁ?

አቶ ጌታቸው፡ ምንም የተውነውነገር የለም። ለምንድን ነው ተደጋግሞ የተነሳውን፣ የከረመውን የትግራይን መሬት እንተወዋለን? በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቀይ መስመር የሚባሉ የሚሳሉ አሉ ማን እንዳላቸው የማይታወቁ። ቀይ መስመር የሚባለው የትግራይ ሕዝብ ደኅንነት ነው። የትግራይ ሕዝብ ህልውና ነው ዋናው ቀይ መስመር። ስለዚህ የትግራይን ሕዝብ ህልውና አሳልፈን ልንሰጥ አንችልም።

አሁንም እየሠራን ያለው ሥራ የትግራይን ሕዝብ ህልውና በአስተማማኝ ሁኔታ የሚጠብቅበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው። እኛ የምንታገለው የትግራይን ሕዝብ ለማዳን ነው። የትግራይ ሕዝብ በጦርነት የሚጠፋበት ሁኔታ ካለ መቆም አለበት። በረሃብ፣ በጠላት ጥይት፣ በመድኃኒት እጦት የሚሞት ሕዝብ አለን። ጀግኖች የትግራይ ሠራዊት ታጋዮች ጠላትን ለመውጋት ሲንቀሳቀሱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ከፊት ለፊታቸው ይመጣሉ። ይህንን ያድናሉ? ሥራቸውን ነው የሚሰሩት?

ስለዚህ ዋናው ቀይ መስመር የትግራይ ሕዝብ ህልውና ነው። የትግራይን ሕዝብ ህልውና ለማስጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ከዚያ ውጪ ሰባት ነጥብ የሚባለው፣ ሰባት ነጥቦችን እንዳቀረብን አላስታውስም፣ እንደዚህ ያለ ነገር የለም። በዚህ ጊዜ የትኛውንም መሬት የመመለስ ወይም መላውን የትግራይ ሕዝብ መያዣ ለማድረግ ኃላፊነት የለንም። ዋናው ትኩረታችን የትግራይ ሕዝብ ህልውና በጠላቶች ጥይት፣ በከበባ እና በመድኃኒት እጦት፣ በተቀነባበረ ሴራ በቀለብ እጦት ጨርሶ የሚጠፋበት ሁኔታ መፍጠር የለበትም። ይህንን ለማስቆም ከተፈለገ፥ ትንሽ ተረጋግቶ ይህንን ለመታገል ሁኔታዎችን ለመፍጠር፣ ከሁሉም መፈክራችን በላይ ነው . . .

ቢቢሲ፡ የትግራይ ሕዝብ ህልውና ቀዳሚ ነው ብትሉም ጦርነቱን ሲከታተሉ የነበሩ ባለሙያዎች ግን ስምምነቱን መቀበላችሁ የሠራዊታችሁ መዳከም ያስገደደው እንደሆነ ይናገራሉ። አዲስ አበባ አካባቢ ደርሳችሁ ከተመለሳችሁ በኋላ የሎጂስቲክስ እጥረት እንዳጋጠማችሁ የሚናገሩም አሉ። በሌላ በኩል የትግራይ ኃይል አዛዦች ከ200 ሺህ በላይ አቅምእንዳለው በቅርቡ ተናግረው ነበር። አቅማችሁ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

አቶ ጌታቸው፡ ስንቅ የሌለው ሕዝብ ያለውን ለሠራዊቱ የሚያካፍል ጀግና ሕዝብ ያላት ትግራይ ናት ያለችን። የትግራይ ሠራዊት ደግሞ ጀግና ሠራዊት ነው፣ ከአፍሪካ ታላላቅ የሚባሉ ሁለት ሠራዊቶች ገጥሞ ሊያንበረክኩት ያልቻሉት ሠራዊት ነው።

ቢቢሲ፡ ከሙሉ አቅማችንን ይዘን ነው እየተደራደርን ያለነው እያሉ ነው?

አቶ ጌታቸው፡ ስለ አቅማችን ለምን ማውራት እንዳለብኝ አይገባኝም። አቅም ኖረ አልኖረ አንጻራዊ ነው። ሠራዊታችን ጀግና ነው፤ ለመዋጋት ለማጥቃት የሄደ ሠራዊት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉ ሕጻናትን ከነከብቶቻቸው የሚንከራተቱ ሰዎች አይቶ ምን ዓይነት ጦርነት ነው የሚዋጋው? እነሱን ሊጠብቅ ነው ወይስ ሌላ ነገር ሊያደርግ? ከነአቅማቸው ናቸው የሚል ንግግር ከውጪ ሆነህ ስታስበው ቀላል ነው። ሠራዊታችን ጀግና ሠራዊት ነው።

. . . ዘር ሲጠፋ እያየ ግን ሠራዊታችን ተኩስ እንዲቆም ፍላጎት አለው። ሠራዊቱ የሚተኩስበት ምክንያት የሕዝቡን መጥፋት ለመከላከል፣ የሕዝቡን መፈናቀልለመከላከል ነው። ሠራዊቱ በተኮሰ ቁጥር ሕዝብ የሚፈናቀል ከሆነ ምን ማለት ነው? ይህ ሠራዊት የትግራይን ሕዝብ ህልውና ለማረጋገጥ፣ የትግራይን ሕዝብ ደኅንነት ለማስጠበቅ የታገለ ሠራዊት ነው። የሕዝቡን ሰላም የሚሻ ሠራዊት ነው። ሽባ አይደለም፤ ነገር ግን ከነአቅሙ የሕዝቡን ደኅንነት ይፈልጋል።

ቢቢሲ፡- በናይሮቢ ያደረጋችሁት ስምምነት ተከትሎ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የሰላሙን ስምምነቱን ህወሓትን ወክሎ የሚፈርም ተወካይ እንዳልላኩና እና ምንም አይነት የህወሓት ሠራዊት እንደሌለ በመግለጽ ይፋዊ መግለጫ አውጥቷል።

አቶ ጌታቸው፡- በህወሓት የተወከለ ተደራዳሪ የለም። የትግራይን መንግሥት ወክለን ነው የሄድነው።

ቢቢሲ፡ ለዓለም እና ሕዝብ የሚያውቀው ሰነድ ግን ስምምነቱ የተደረገው በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል እንደተደረገ ነው።ሁለተኛ የትግራይ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጠው መግለጫ የለም። ታዲያ ህወሓትን ወክለው ወደ ድርድሩ በሄዱት እና በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መካከል አለመግባባት መፈጠሩን ያሳያል የሚሉም አሉ?

አቶ ጌታቸው፡ ከመንግሥት ተወካዮች መካከል እኔ ብቻ የህወሓት አባል ነኝ። ፃድቃን የህወሓት አባል አይደለም። . . . መከፋፈል ሊኖር የሚችለው የተከፋፈለ ኃይል ካለ ብቻ ነው። ከህወሓት አመራር የመጣሁት እኔ ብቻ ነኝ። እኔም መንግሥትን ወክዬ ነው የመጣሁት። በመንግሥት ውክልና ተንቀሳቅሰናል። ህወሓት የሚል አለ፤ የህወሓት ሠራዊት የሚባል የለም። ለዚያ እዋጋለሁ፤ መቀየር አለባችሁ ብለናል። ነገር ግን በተኩስ አቁም ስምምነታችን እምቢ ስላሉ ግን በስም አናፈርስም ብለን ቀጥለናል።

ቢቢሲ፡ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ ከምን የመነጨ ነው?

አቶ ጌታቸው፡ የማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ ትክክለኛ መግለጫ ነው። ሠራዊት የለኝም ይላል፤ ሠራዊት ስለሌለው።

ቢቢሲ፡ ወኪሎችንም አልላኩም ይላል . . .

አቶ ጌታቸው፡ ህወሓት ተወካይ አልላከም፣ የትግራይ መንግሥት ነው ተወካይ የላከው . . .

ቢቢሲ፡ የትግራይ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ለምን መግለጫ አልሰጠም?

አቶ ጌታቸው፡ የትግራይ መንግሥት መግለጫ ይስጥ ብላችሁ ጠይቁ። የመጣሁት ለመደራደር ነው፣ እሱን ስጨርስ ለማኅበራዊ ሚዲያ ክርክሮች ምላሽ እየሰጠሁ ነው . . .

ቢቢሲ፡- በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰማው ቅሬታ ስላለ ነው፤ ዝምታ ስለበዛ ነው ብለው ያስባሉ?

አቶ ጌታቸው፡ ስጋቶቹ ይገባኛል። 

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ

ቢቢሲ፡- በመጨረሻ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብና በግድያ ሞተዋል። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችም የፆታዊ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል። የተለያዩ ጥሰቶችም ተፈጽመዋል። ትግራይ ከዚህ ሁሉ በኋላ ምን አተረፈች?

አቶ ጌታቸው፡- ትግራይ ጦርነት አልጀመረችም፤ በላይዋ ላይ ነው የተጀመረው። የትግራይ ሠራዊት የትግራይን ሕዝብ በላዩ ላይ የተከፈተውን ጦርነት ለመከላከል ተዋግቷል። ይህ ሁሉ ጥፋት ደርሷል። ጦርነት በሚኖርበት ጊዜ ምንም ትርፍ ሊኖር አይችልም። ትግራይን ማትረፍ አይቻልም። ማንም ሊያተርፍ አይችልም። የትግራይ ሕዝብ ተሰቃይቷል፤ የነበረው ልማትም ጠፍቷል። ህጻናት ትምህርት ቤት ሳይማሩ ከሦስት ዓመታት በላይ ተፈናቅለዋል። ከጦርነት ምን ጥቅም ሊኖር ይቻላል? ከጦርነት ምን አይነት ትርፍ ሊገኝ ይችላል? ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ የለም። ህልውናችንን ለማረጋገጥ የሚያስችል አቋም ይዘን ትርፍ ሳይሆን ቢያንስ እንካሳለን ብለን እናምናለን።

ቢቢሲ፡ የትግራይ ካሳ ምን ይሆናል? የትግራይ ሕዝብ ምን ይካሳል?

አቶ ጌታቸው፡ ሕዝቡ ምኞቱን እና ፍላጎቱን፣ ወይ አገር ይሁን ወይ የሆነው ይሁን እኔ መወሰን ስለማችል፥ ሙሉ በሙሉ የሚያረጋግጥበት ሁኔታ መፍጠር ነው ነው ካሳው። ይህንን ለማድረግ በሰላማዊ መንገድ ወይም በጦርነት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። የትግራይ ሕዝብ ይህንን ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም።

ቢቢሲ፡ የፌዴራል መንግሥት ያቀረባቸውን ነጥቦች በሙሉ ተቀብላችሁ ስታበቁ ይህንን እንዴት ማረጋገጥ ትችላላችሁ?

አቶ ጌታቸው፡ በደንብ ይቻላል። የተቀበልኩት የተኩስ አቁም ነው። ተኩስ ከቆም በኋላ የፖለቲካ ውይይት ይቀጥላል። በፖለቲካ ውይይት የትግራይን ሕዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ካላረጋገጥኩኝ ተኩስ ለማቆም ስለወሰንኩ ብቻ የሚቀበለኝ ሰው ይኖራል? የትግራይ ሕዝብ እና የትግራይ ሠራዊት እኔ እንደፈለኩ የምነዳው አይደለም።

ፌዴራል መንግሥትም ይሁን ዓለም አቀፍ መንግሥታትም ይሁኑ ማንም ይሁን የትግራይን ሕዝብ ፍላጎት ከማሟላት ውጪ አማራጭ ያለው አይመስለኝም። . . . ዋናው ተኩሱ ይቁም፣ የትግራይ ሕዝብ እርዳታ ይቅረብለት፣ አገልግሎት ያግኝ፣ በፖለቲካዊ ውይይት በሰላማዊ መንገድ የሚፈታ ነገር ካለ እናያለን። መፍታት ካልተቻለ ትጥቅ ይፍታ ስላልኩት የሚፈታ ሠራዊት የለም።

ቢቢሲ፡ በስምምነት አብቅቷል፣ ይህ የሁለት ዓመት ጦርነት እና . . .

አቶ ጌታቸው፡ አላበቃም። ተኩስ አቁመናል እና . . .ጦርነቱ አለቀ ማለት አይደለም. . .

ቢቢሲ፡ እንደ የትግራይ መሪዎች ወደዚህ ጦርነት መግባታችሁ ይጸጽታችኋል?

አቶ ጌታቸው፡ ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም። ጦርነት በእኔ ላይ ታወጆ የትግራይን ሕዝብ ክብር ለማስጠበቅ ስለታገልኩ እኮራለሁ እንጂ ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም። ሊፈታ የሚችል ነገር ቢኖር ኖሮና ባደርገው ኖሮ የምለው ነገር ቢኖር፣ አንዴ ፈትሼ ልቆጭ እችላለሁ። በትግራይ ሕዝብ ላይ የታወጀውን ጦርነት በላዩ ላይ የተደረገው ከበባ ለመከላከል ከሕዝቤ ጋር ስለታገልኩ የሚቆጨኝ ነገር የለም።

Exit mobile version