Site icon ETHIO12.COM

በራይድ ታክሲ ሹፌሮች ላይ የሚፈፀም ግድያንና የከባድ ውንብድና ወንጀልን በተመለከተ የተጣሩ የምርመራ መዛግብትን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

የፕሬስ መግለጫ

በራይድ ታክሲ የትራንስፓርት አገልግሎት በሚሰጡ ሹፌሮች ላይ የሚፈፀም ግድያንና የከባድ ውንብድና ወንጀልን በተመለከተ የተጣሩ የምርመራ መዛግብትን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

በራይድና በሌሎች የትራንስፓርት አገልግሎት ድርጅቶች አማካኝነት የሚሰጡ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ለከተማው ማህበረሰብ ቀልጣፋ የሆነ ትራንስፖርት በመስጠት የከተማውን ማህበረሰብ ችግር በመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡

አገልግሎቱ በትራንስፓርት ዘርፉ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት በዚህ ዘርፍ ተሰማርተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በሚደግፉ አሽከርካሪዎች ላይ በተለያየ ጊዜ አሰቃቂ ወንጀሎች ተፈጽመዋል፡፡ ወንጀሎቹ ከተፈፀሙበት ጊዜ ጀምሮ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር አኳያ፤ በተቋሙ የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ከአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን በጉዳዩ ላይ በርካታ የወንጀል ምርመራዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ በቅርቡም ከነሀሴ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ከዐቃቤ ህግና ከመርማሪ ፖሊሶች የተውጣጣ የጋራ ቡድን በማዋቀር 9 የምርመራ መዝገቦችን በማደራጀት ጥልቅ የሆነ ምርመራ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

በምርመራ ግኝቱ ማረጋገጥ እንደተቻለውም በራይድ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡ ሹፌሮች ላይ የወንጀል ተግባሩን የሚፈፅሙት የውንብድና ቡድኑ አባላት አብዛኛውን ጊዜ ወንጀሉን ከመፈፀማቸው በፊት የትራንስፖርት አገልግሎት ፈላጊ በመምሰል፣ መልካም ግንኙነት በመፍጠር ተበዳይ በሆኑት ሹፌሮች ላይ እምነት እንዲያድርባቸው ካደረጉ በኋላ አብዛኛውን ጊዜ ከአዲስ አበባ ወደ ዝዋይ መስመር በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ ከተሞች የትራንስፓርት አገልግሎት እንዲሰጣቸው ያደርጋሉ፤ በኋላም አገልግሎቱን ወደ ሚያገኙበት አካባቢ ሹፌሮቹን በመውሰድ እና በአንዳንድ ሁኔታዎችም አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ራቅ ወዳሉና ሰዎች ወደማይበዙባቸው ቦታዎች በምሽት በመውሰድ ሹፌሮቹን ለሽንት አቁምልን በማለት ካስቆሙ በኋላ ወንጀሉን የሚፈጽሙ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡

የምርመራ ግኝቱ እንደሚያመላክተው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡትን አሽከርካሪዎች በጋራ በመሆን በስለት በመውጋት፣ በገመድ አንገታቸውን በማነቅና በሽጉጥ ተኩሰው በመግደል አስክሬናቸውን በመጣል ተሽከርካሪዎቹንና ሌሎች ንብረቶችን እንደሚወስዱ ተረጋግጧል፡፡

በቡድን የተደራጁ የወንበዴ ቡድኖች በሹፌሮቹ ላይ ጥቃት በመሰንዘር የሚያሽከረክሩትን ተሽከርካሪና ሌሎች ንብረቶች ከወሰዱ በኋላ የወሰዱትን ተሽከርካሪ በዝቅተኛ ዋጋ ያለምንም ህጋዊ ሰነድ በመግዛት አይነታቸውን በመቀየር፣ ታርጋ በመለጠፍ ለሽያጭ የሚያቀርብ ሌላ የተደራጀ ቡድን መኖሩም በምርመራ ተረጋግጧል፡፡ የምርመራ ቡድኑ በዚህ የውንብድና ቡድን ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹን ወንጀል ፈፃሚዎንና በውንብድና ተግባር የተወሰዱ ተሽከርካሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

ምርመራቸው በተጠናቀቁና ክስ በተመሰረተባቸው መዝገቦች ላይ እንደታየው ቡድኑ ሶስት የሚሆኑ ሰዎችን በመግደል ሟቾች ሲያሽከረክሩት የነበሩትን ተሽከርካሪና ሌሎች ንብረቶችን የወሰዱ ሲሆን በዚህም ሂደት ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት ጠፍቷል፡፡ በተመሳሳይም በሌሎች ምርመራቸው በሂደት ላይ ባሉ መዝገቦችም ንብረት ከመዘረፉ ባለፈ የሰው ህይወት መጥፋቱ ተረጋግጧል፡፡

የምርመራ ቡድኑ ባደረገው እልህ አስጨራሽና ጠንካራ ምርመራ በዚህ የወንበዴ ቡድን ውስጥ ሆነው ወንጀሉን በተደራጀ ሁኔታ ሲፈፅሙ የነበሩ ሰዎችን በመያዝ ከተደራጀው 9 የምርመራ መዝገቦች ውስጥ 6 መዝገቦችን በማጠናቀቅ በ12 ተከሳሾች ላይ እስከ ሞት ፍርድ ድረስ በሚያስቀጣ በከባድ የውንብድና ወንጀልና በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀል ክስ የተመሰረተ ሲሆን በቀጣይም ምርመራቸው እየተከናወኑ በሚገኙ መዝገቦች ላይ ጥልቅ ምርመራ በማድረግ አጥፊዎችን በህግ የማስጠየቅ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

በራይድና በሌሎች ድርጅቶች አማካኝነት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ሹፌሮች በቡድን በመሆን አገልግሎት በሚጠይቁ ሰዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜም ስለደንበኛው ሙሉ መረጃ መጠየቅና መያዝ የሚኖርባቸው ሲሆን፤ ከአዲስ አበባ ውጭ ወይም አዲስ አበባ ውስጥም ሆኖ ጭር ወዳለ ቦታ አገልግሎት በሚጠይቁ ሰዎች ላይ አጠራጣሪ ሁኔታ ካዩባቸው ለጥንቃቄ የሚረዱ ተግባራትን በመፈፀም፣ በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላቶች መረጃዎችን በመስጠት፤ በተደጋጋሚ እንደሚታየውም አገልግሎት በመስጠት ሂደት የተለየ ግንኙነት የሚፈጥሩ ደንበኞች ላይ ትውውቅ አለን በሚል መዘናጋት መፈጠር የሌለበት መሆኑን እና መሰል ክስተቶችም ሲያጋጥሙ ማህበረሰቡ አገልግሎቱን ለሚሰጡ ሹፌሮች ድጋፍ እንዲያደርግና ለፀጥታ አካላት መረጃ በመስጠት የዘውትር ትብብር እንዲያደርግ ስንል እንጠይቃለን፡፡ በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ

Exit mobile version