Site icon ETHIO12.COM

የሪል ስቴት ገበያን ለመቆጣጠር ውሳኔ ተላለፈ

– ባንኮች በዘፈቀደ ብድር እንዳይሰጡ መመሪያ ወጥቷል

አልሚዎች በሚገመት ትርፍ ብቻ ለገበያ እንዲያቀርቡ ታዟል

Wudineh Zenebe/WZ news

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመኖሪያ ቤት እጥረት አስተዎፅዖ ይኖረዋል በሚል ለሪል ስቴት አልሚዎች ዝቅተኛ በሆነ የሊዝ ዋጋ ሰፋፊ መሬት ቢያቀርብም ፤ ገበያው ግን በየጊዜው እያበደ እና ብዙዎችን በእንባ እያራጨ የሚገኝ በመሆኑ አስተዳደሩ ገበያውን ለመቆጣጠር ውሳኔ አሳልፏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ረቡዕ ህዳር 8 ቀን 2015 ዓ.ም ሁሉንም ባንኮች በመጥራት ከዚህ በኋላ ባንኮች ለሪል ስቴት አልሚዎች በዘፈቀደ ብድር እንዳይሰጡ መመሪያ ሰጥተዋል።

በውይይቱ ወቅት አስተዳደሩ ባቀረበው ማስረጃ፣ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የአንድ ካሬ ሜትር የመገንቢያ ዋጋ 30 ሺህ ብር ነው። ነገር ግን የሪል ስቴት መኖሪያ ቤቶች እየተሸጡ ያሉት በአማካኝ በአንድ ካሬ ሜትር 120 ሺህ ብር ነው።

ይህን የቀወሰ የሪል ስቴት ገበያ ማስተካከል የሚያስፈልግ በመሆኑ የከተማው አስተዳደር ሦስት ጉዳዮች ላይ አፅንኦት ሰጥቶ ማብራሪያና አማራጮችን አቅርቧል።

የመጀመሪያው ባንኮች ራሳቸው ደጓሚ (subsidiary) ኩባንያ አቋቁመው ወደ ሪል ስቴት ልማት ገብተው ገበያውን እንዲያረጋጉ ቀዳሚው አማራጭ ሆኗል። ባንኮቹ በ70/30 ፕሮግራም ተሳታፊ ለመሆን ሲወስኑ አስተዳደሩ መሬት ያቀርብላቸዋል። ፣ ሁለተኛው ደግሞ ባንኮች የሪል ስቴት አልሚ ኩባንያዎች በሚያቀርቡት የብድር ጥያቄ ላይ ብቻ ተመስርተው ብድር እንዳይሰጡ፣ ይልቁንም ከአልሚዎቹ ጋር በጋራ አቅደው ግንባታ ከተካሄደ በኋላ በተወሰነ ትርፍ ሽያጭ እንዲፈፀም ማስቻልን የተመለከተ ነው፤ በሦስተኛነት በአማራጭነት የቀረበው ባንኮቹ ይዞታ ካላቸው ግለሰቦች ጋር በመነጋገር ኮንትራክተር በመቅጠር ግንባታ ማካሄድ እና በትክክለኛ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ ናቸው።

“እስካሁን ለተዘበራረቀው የአዲስ አበባ የሪል ስቴት ገበያ ባንኮች በዘፈቀደ የምትረጩት ገንዘብ ነዳጅ ሆኗል፤ ማህበራዊ ኃላፊነታችሁን መወጣት አለባችሁ” መባላቸውን ወዝ ኒውስ ያገኛቸው መረጃዎች አመልክተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በነጋታው ሐሙስ አንዳንድ ባንኮች ለሪል ስቴት ልማት የሚቀርቡ የብድር ጥያቄዎችን ሳያስተናግዱ መዋላቸው ታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በሚቀጥሉት አመታት የመኖሪያ ቤት ግንባታ በመንግስት ላይ መንጠልጠሉ ቀርቶ ፣ ወደግሉ ዘርፍ በጥልቀት መግባት አለበት ከሚል ፍላጎት ነው።

የፋይናንስ ሁኔታውም የሞርጌጅ ቅርፅ እንዲይዝና ለተፈጠረው የዋጋ ግሽበትም የሪል እስቴት ዘርፍ አስተዎፅዎ ከፍተኛ በመሆኑ ፣ የገንዘብ ዝውውሩን መቆጣጠር ያስፈልጋል በሚል ምክንያት መሆኑ ተመልክቷል።

የወዝ ኒውስ መረጃዎች እንደሚገልፁት ባንኮች አትራፊ ሰለሆኑ ብቻ ወደ ዘርፋ የሚያስገቡትን ገንዘብ በመግታት የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አኃዝ ዝቅ ማድረግ ፤ ብሎም የመኖሪያ ቤት መሸጫ ዋጋ ላይም ለውጥ ማምጣት እንዳለባቸው የመንግስት ፍላጎት መሆኑ በግልፅ መንፀባረቁ ተመልክቷል።

Wudineh Zenebe/ WZ news

Exit mobile version