Site icon ETHIO12.COM

የኢኮኖሚ ወንጀሎች ፍሬ የሆኑ ንብረቶችን ማስመለስ

ወንጀሎቹ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ እና ለህዝብ አገልግሎት እና ለተለያዩ መሰረተ ልማት መዋል የሚችሉ ሀብቶችን የሚቀሙ እንዲሁም የኢኮኖሚ ስርዓቱን የሚያዛቡ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር በአለም ባንክና በተ.መ.ድ የእፆችና ወንጀል መከላከል ቢሮ የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት በየአመቱ ከ20 እስከ 40 ቢሊዮን ዶላር በሙስና ወንጀልና ሌሎች ኢኮኖሚ ወንጀል ተግባራት ምክንያት ያጣሉ፡፡

መግቢያ

የወንጀል ድርጊት የተለያዩ መነሻዎች መሰረት በማድረግ ወይም የተለያዩ ዓላማዎችን ለማሳካት ሊፈፀም የሚችል ሲሆን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማግኘት አንዱ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ አንድ ወንጀል አድራጊ ከወንጀል ድርጊት ያገኘውን ሀብት እንዲጠቀም መደረግ የለበትም የሚለው የህግ መርህ ስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ የዚህ መርህ ሌላ መገለጫ የሆነው ከወንጀል ድርጊት የተገኘው ሀብት ወደ ነበረበት ተመላሽ ተደርጎ የወንጀሉ ተጎጂ እና አጠቃላይ ኢኮኖሚው እንዳይጎዳ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የሀብት ማስመለስ ተግባር የሚያተኩረው ማንም ሰው ከወንጀል ድርጊቱ የገንዘብ ጥቅም እንዳያገኝ ማድረግ ነው፡፡

  1. የኢኮኖሚ ወንጀሎች እና የሚያስከትሉት ጉዳት

የኢኮኖሚ (የፋይናንስ) ወንጀሎች የኢኮኖሚ ወይም ፋይናንስ ጥቅም ለማግኘት የሚፈፀሙ ወንጀሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ወንጀሎች በህገ ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት፣ የእፆች ዝውውር፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የታክስ ማጭበርበር፣ የሙስና ወንጀል እና የመሳሰሉትን ያካትታሉ፡፡

ወንጀሎቹ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ እና ለህዝብ አገልግሎት እና ለተለያዩ መሰረተ ልማት መዋል የሚችሉ ሀብቶችን የሚቀሙ እንዲሁም የኢኮኖሚ ስርዓቱን የሚያዛቡ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር በአለም ባንክና በተ.መ.ድ የእፆችና ወንጀል መከላከል ቢሮ የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት በየአመቱ ከ20 እስከ 40 ቢሊዮን ዶላር በሙስና ወንጀልና ሌሎች ኢኮኖሚ ወንጀል ተግባራት ምክንያት ያጣሉ፡፡

  1. የኢኮኖሚ ወንጀሎች ፍሬ የሆኑ ንብረቶችን ማስመለስ

2.1. የወንጀል ፍሬ የሆነ ንብረት እና ንብረቱን የማስመለስ ምንነት

ሙስናን ለመከላከል እ.አ.አ 2004 የወጣው አለም አቀፍ ስምምነት የወንጀል ፍሬ ለሆነ ንብረት ትርጉም የሰጠ ሲሆን በተፈፀመ የወንጀል ድርጊት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተገኘ የትኛውም ንብረት የሚያካትት መሆኑ ተገልጧል፡፡ የወንጀል ፍሬ ንብረት ማስገኘት የሚችሉ (አመንጪ) ወንጀሎች ወንጀልነታቸው በህግ የተደነገገ እና የወንጀል ፍሬ ንብረትን ማስገኘት የሚያስችሉ የወንጀል ድርጊቶች ሲሆኑ ሙስናን፣ የታክስ ማጭበርበርን፣ የእፆች ዝውውርን፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ያካትታል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አዋጅ ቁጥር 780/2005 አመንጪ ወንጀል ማለት ማንኛውም ለወንጀል ፍሬ ምንጭ የሆነና ቢያንስ አንድ አመት ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል እንደሆነ ተገልጧል፡፡

የወንጀል ፍሬ የሆነውን ንብረት ማስመለስ ማለት ንብረቱን የመከታተል፣ የማሳገድ፣ የማስወረስ እና የተወሰደውን ንብረት ወደ ህጋዊ ባለቤቱ የመመለስ ሂደት ነው፡፡ ሙስናን ለመከላከል እ.አ.አ 2004 በወጣው አለም አቀፍ ስምምነት መሰረት ይህ ሂደት ከአንድ ሀገር ተወስዶ ወደ ሌላ ሀገር የተላለፈውን የወንጀል ፍሬ የሆነውን ንብረት ወደ ተወሰደበት ትክክለኛ ሀገር መመለስን ይጨምራል፡፡

2.2. አለም አቀፍ የወንጀል ፍሬ ማስመለስ የህግ ማዕቀፎች

በወንጀል የተገኙ ንብረቶች በሀገር ውስጥ ወይም ከሀገር ውጭ ሊደበቁ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ያለአግባብ የተወሰደውን ንብረት ለማስመለስ በሀገር እና በአለም አቀፍ ደረጃ ስልቶችን መንደፍ ያስፈልጋል፡፡ የንብረት ማስመለስ ተግባርን ውጤታማ ለማድረግ በአለም አቀፍ ደረጃ ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል እ.አ.አ በ2004 የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የወጣው አለም አቀፍ ስምምነት፣ እ.አ.አ 2003 የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የወጣው የአፍሪካ ስምምነት፣ እ.አ.አ በ1988 ህገ ወጥ የእፆች ዝውውርን ለመከላከል የወጣው የተ.መ.ድ ስምምነት፣ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል እ.አ.አ በ2004 የወጣው የተ.መ.ድ ስምምነት እና የፋይናንስ ድርጊት ግብረ ሀይል (Financial Action Task Force) እ.አ.አ በ1989 በሀገራት የተቋቋመ አካል ዋነኞቹ ናቸው፡፡

እነዚህ ስምምነቶች እና ሌሎች እርምጃዎች የወንጀል ፍሬ ንብረቶች የሚያዙበት፣ የሚወረሱበትን እና ለባለቤቱ የሚመለሱበትን ሁኔታ የሚደነግጉ እና መወሰድ ያላባቸውን እርምጃዎች የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ደንግገዋል፡፡ የስምምነቶቹ አባል ሀገራት የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችን ለመለየት፣ ለመከታተል፣ ለመያዝ ወይም ለማገድ፣ ለመውረስ የሚያስችላቸውን እርምጃዎች መውሰድ እንዳለባቸው ይገልፃሉ፡፡ በእነዚህ ስምምነቶች መሰረት ንብረቱ የሚገኝበት ሀገር ንብረቱን የመያዝና ለጠያቂው ሀገር የማስረከብ እንዲሁም አጠቃላይ በንብረት ማስመለስ ሂደት የመተባበር ግዴታ አለባቸው፡፡

2.3. የንብረት ማስመለስ ሂደትና ተግባራት

የወንጀል ፍሬ የሆነውን ንብረት የመመለስ ሂደት ጥቆማን፣ የፋይናንስ ተቋማት ሪፖርትን ወይም ሌላ የመረጃ ምንጭን መነሻ በማድረግ ሊጀመር ይችላል፡፡ በአለም ባንክና በተ.መ.ድ የእፆችና ወንጀል መከላከል ቢሮ በተዘጋጀው ንብረት ማስመለስ ሀንድ ቡክ መሰረት ምርመራ ለማድረግ እና ያለአግባብ የተወሰደውን ንብረት ለማስመለስ ሀላፊነት የተሰጠው አካል የሚከተሉትን ሂደቶች ይከተላል፡፡

2.3.1. መረጃ መሰብሰብ እና ንብረት መለየት

በንብረት ማስመለስ ሂደት የመጀመሪያው እርምጃ ከተለያዩ ምንጮች ስለ ወንጀል አድራጊው ጨምሮ የተለያዩ መረጃዎች መሰብሰብና ንብረቱ የሚገኝበትን ሁኔታ መለየት ነው፡፡ በዚህ ሂደት የተለያዩ የመረጃ መሰብሰቢያ ልዩ የምርመራ ስልቶች ማለትም መገናኛዎችን መከታተል ወይም መጥለፍ፣ ንግግሮችን/ድርጊቶችን መቅረፅ፣ የደብዳቤ ልውውጦችን መጥለፍና መያዝ እና የመሳሰሉት ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ፡፡

2.3.2. የወንጀል ፍሬ ንብረት መያዝ ወይም ማሳገድ

ይህ እርምጃ ንብረቱ እንዳይንቀሳቀስ ወይም እንዳይጠፋ የሚደረግበት ተግባር ነው፡፡ ይህን ለማስፈፀም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡

2.3.3. ንብረት ማስወረስ

የሚወረሱ ንብረቶች ከወንጀል ድርጊት የተገኘ የወንጀል ፍሬ፣ የወንጀል ፍሬ ከሆነው ንብረት ጋር የተቀላቀለ ንብረት፣ በወንጀል ፍሬ ንብረት የተለወጠ ሌላ ንብረት፣ ከወንጀል ፍሬ ንብረት የተገኘ ገቢን ይጨምራል፡፡ ከወንጀል ድርጊት የተገኘው ንብረት በህገ ወጥ መንገድ የተገኘ መሆኑን ለማያውቅ እና በፍትሀዊ ዋጋ ለገዛው ሶስተኛ ወገን የተላለፈ ከሆነ የዚህ በቅን ልቦና የተላለፈለት ሰው ጥቅም ይከበርለታል፡፡

የወንጀል ፍሬ የሆነውን ንብረት ለማስመለስ ያለው የህግ አማራጭ፡-

i. የወንጀል ክስ ማቅረብ እና ንብረቱን ማስወረስ- በዚህ አማራጭ መሰረት በኢኮኖሚ ወንጀሎች ያለአግባብ የተወሰደውን ንብረት ለማስመለስ መረጃ መሰብሰብ፣ በአድራጊው ላይ ክስ ማቅረብና የጥፋተኝነት ውሳኔ ማሰጠት እና ይህን ውሳኔ ተከትሎ የወንጀል ፍሬ የሆነውን ንብረት እንዲወረስ ማስወሰን ነው፡፡

ii. የጥፋተኝነት ውሳኔ ሳይሰጥ ንብረት ማስወረስ- ይህ የወንጀል ክስና የጥፋተኝነት ውሳኔ ሳይፈለግ ቀጥታ ንብረቱን ለማስወረስ ውሳኔ የሚሰጥበት አካሄድ ነው፡፡ ይህ ወንጀል አድራጊው ካልተገኘ ወይም ካልታወቀ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል አማራጭ ነው፡፡

iii. የፍትሐብሔር ክስ ማቅረብ- ይህ ከውል ውጭ የሚኖር ሀላፊነት፣ የውል ጥሰት ወይም ያለአግባብ መበልፀግን መነሻ በማድረግ የፍትሐብሔር ክስ የሚቀርብበትና የመውረስ ውሳኔ የሚሰጥበት ሂደት ነው፡፡

iv. በአስተዳደራዊ እርምጃ ማስወረስ- ይህ አማራጭ እንደ ሌሎቹ አማራጮች የፍርድ ቤት ሂደት የሚፈልግ አይደለም፡፡ በህግ ስልጣን በተሰጠው ባለስልጣን ወይም አካል የሚወሰን የማስወረስ ውሳኔ ነው፡፡

2.3.4. ንብረት ወደ ባለቤት ማስመለስ

በዚህ የማስመለስ ደረጃ እንዲወረስ የተወሰነ ንብረት ወደ ተወሰደበት ባለቤት ተመላሽ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ ይህም እንዲያዝ ወይም እንዲወረስ የተወሰነውን ንብረት አስመልክቶ የሚሰጠውን ትዕዛዝ የማስፈፀም ስራ የሚከናወንበት ነው፡፡ ንብረቱ ከሀገር ውጭ ከሆነም ትዕዛዙ ንብረቱ ባለበት ሀገር እንዲፈፀም ጥያቄ ይቀርባል፤ በህግ ድጋፍ ወይም በትብብር እንዲፈፀም ይደረጋል፡፡

  1. የወንጀል ፍሬ ንብረት ማስመለስ በኢትዮጵያ

3.1. የህግ ማዕቀፍ

በኢትዮጵያ በህገ ወጥ መንገድ የተወሰዱ ንብረቶችን የማስመለስ ሂደት የሚገዙ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተዋል፡፡ ከህግ ማቀፎቹ መካከል በህገ ወጥ መንገድ የተገኘ ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀልን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንዱ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ መሰረት ወንጀሉን ለመከላከል ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተለይ የፋይናንስ ተቋማት የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች (የደንበኞችን ማንነት በአግባቡ ማጣራትና የንግድ እንቅስቃሴ መረጃዎችን መያዝ፣ አጠራጣሪ የባንክና ንግድ እንቅስቃሴዎችን ሪፖርት የማድረግ እና የመሳሰሉትን) እንዲወስዱ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ከዚህ አልፎ ወንጀሉ ከተፈፀመ በህገ ወጥ መንገድ የተወሰዱ ንብረቶች የሚወረሱበት/የሚመለሱበት አሰራር ተደንግጎ ይገኛል፡፡

ይህም የወንጀል ክስ ቀርቦ የጥፋተኝነትና ንብረቱ እንዲወረስ ውሳኔ በማሰጠት (ጥፋተኝነት ላይ የተመሰረተ) የወንጀሉ ፈጻሚ ካልታቀ፣ ከጠፋ ወይም ከሞተ እና የጥፋተኝነት ውሳኔ መስጠት ካልተቻለ ንብረቱ የወንጀል ፍሬ መሆኑ በፍ/ቤት በማስወሰን (ጥፋተኝነት ላይ ያልተመሰረተ) የመውረስ ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚችል የአዋጁ አንቀፅ 35 ያሳያል፡፡

በዚህ ሂደት የሚወረሱ ንብረቶች የወንጀል ፍሬ ንብረት፣ ከሌላ ንብረት ጋር ተቀላቅሎ ወይም ተለውጦ የተገኘ ንብረት፣ ከወንጀል ፍሬ ንብረት የተገኘ ገቢ፣ ለወንጀሉ አፈፃፀም የዋለ ንብረት ያካትታል፡፡ እንዲወረስ የተወሰነው ንብረት በሌላ ሀገር የሚገኝ ከሆነ ከሀገሪቱ ጋር በሚደረግ የጋራ የትብብር የህግ ድጋፍ መሰረት ማስፈፀም እንደሚቻል ተደንግጓል፡፡ ሌላው የህግ ማዕቀፍ የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 እና የተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የስነ ስርዓትና ማስረጃ ህግ አዋጅ ቁጥር 882/2007 ሲሆን በሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ የተባለው ሰው ከሚጣልበት ቅጣት በተጨማሪ የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶች እንደሚወረሱ ወይም ለባለቤቱ እንደሚመለሱ ይደነግጋሉ፡፡

በፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 1176/2012 መሰረት ከሽብር ወንጀል ጋር የተገናኘ ንብረት፣ በአሸባሪነት የተሰየመ ድርጅት ንብረት እንዲሁም በሽብር ወንጀል ላይ ተሳትፈው የተገኙ ድርጅቶች ንብረት እንደሚወረስ የሚገልፅ ሲሆን የ2006 ዓ.ም ወንጀል ህግ አንቀፅ 98 በወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ሰው ከወንጀል ድርጊቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ያገኘው ንብረት በፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት እንደሚወረስ ይገልፃል፡፡

3.2. የወንጀል ፍሬ ንብረት የማስመለስ ሀላፊነት ያለባቸው አካላት

ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት በተለይ የፋይናንስ ተቋማት የኢኮኖሚ ወንጀሎችን ለመከላከል በህግ የተቀመጡ የመከላከልና ጥንቃቄ እርምጃዎችን (የደንበኞችን ማንነት የማጣራት፣ መረጃዎችን የመያዝ፣ የህገ ወጥ ገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ስልት መቀየስና ተግባራዊ ማድረግ) የመውሰድ እና በንግድና ሙያ ስራ ዙሪያ ጥርጣሬዎች ሲያጋጥሙ ለሚመለከተው ሪፖርት የማቅረብ ግዴታቸውን እንዲወጡ ይጠበቃል፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሀብትን ከማስመዝገብ አንጻር እንዲሁም የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል የፋይናንስ ሪፖርቶችና መረጃዎችን ከመቀበልና ከመተንተን አንፃር ሀላፊነታቸውን መወጣት፣ ለምርመራ ስራም ተገቢውን መረጃና ድጋፍ የመስጠት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

የኢኮኖሚ ወንጀሎች ተፈፅመው ሲገኙ ተጠያቂነትን ከማረጋገጥና የወንጀሉ ፍሬ የሆኑ ንብረቶችን ከማስመለስ አንፃር ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና ፌዴራል ፖሊስ ሚና ትልቅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና ፌዴራል ፖሊስ ወንጀሎቹን የመመርመር እና ተጠያቂነትን የማስፈን እንዲሁም የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችን የማስወረስ/የማስመለስ ሀላፊነት ከላይ በተጠቀሱት የሀገራችን ህግ ማዕቀፎች ተሰጥቷቸዋል፡፡ በሌላ በኩል የመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ኤጄንሲ የተወረሱ ንብረቶችን ከማስተዳደር አንፃር ሀላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

ማጠቃለያ

በኢኮኖሚ ወንጀሎች ከፍተኛ መጠን ያለው የህዝብ እና የግለሰብ ንብረት ያለአግባብ ይመዘበራል፡፡ የግልፀኝነት እና የተጠያቂነት ማነስ ንብረት ያለአግባብ እንዲወሰድ/እንዲሰረቅ እንደ ዋና ምክንያት ይጠቀሳሉ፡፡ ንብረቶቹን ለማስመለስ የሚያስችሉ አለም አቀፍና ብሔራዊ የህግ ማዕቀፎች የተዘጋጁ ሲሆን ንብረት በማስመለስ ሂደት የቁርጠኝነት ችግር፣ ወጥነት ያለው የህግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ በአለም አቀፍ ትብብር የሂደቱ መራዘም እና ንብረቶቹ ያሉበት ሁኔታ የመለየት ችግር የሚታዩ እንቅፋቶች እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ስለዚህ አመንጪ ወንጀሎችን መከላከልና ተጠያቂነትን ከማስፈን ጎን ለጎን የተወሰደውን ንብረት የማስመለስ ስራ ውጤታማነት የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና የአለም አቀፍ ትብብር ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡

በንቃተ ህግ፣ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

Exit mobile version