Site icon ETHIO12.COM

አዲስ አበባ – መሬት በሊዝ ወስደው ሳያለሙ አጥረው ያስቀመጡ ኩባንያዎችን ካርታ መከነ

የከተማው መሬት ልማት እና ማኔጅመንት ቢሮ ከኩባንያዎች እና ከግለሰቦች የነጠቀውን 90 ሄክታር መሬት ፣ መሬት ባንክ ማስገባቱን ዛሬ ህዳር 12 ቀን 2015 ዓም አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት እና ማኔጅመንት ቢሮ በሊዝ መሬት ወስደው ከአምስት አመት በላይ አጥረው ካስቀመጡ ግለሰቦች እና ኩባንያዎች ጋር በኔክሰስ ሆቴል ውይይት አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።

ከውይይቱ በኋላም ጥቅምት 10 ቀን 2015 ዓም 76 ኩባንያዎች እና ባለሃብቶች ግንባታ ያላካሄዱበትን በቂ ምክንያት እንዲያቀርቡ ጊዜ ሰጥቷቸው ነበር ። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ቢሮውን የሚያሳምን ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻላቸው ቦታቸው ተነጥቆ ፣ ካርታቸው መክኖ መሬት ባንክ ገቢ ተደርጓል።

ዛሬ ህዳር 12 ቀን 2015 ዓም የከተማው መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ቀነዓ ያደታ በሰጡት መግለጫ፣ 90 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ ተደርጓል።

‘’ ሳያለሙ አጥረው ከቆዩ ድርጅቶች የተወሰደው መሬት በግልፅ ሊዝ ጨረታ ለአልሚዎች ይቀርባል’’በማለት ዶ/ር ያደታ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ደ/ር ቀነዓ ጨምረው እንደገለፁት ፣ መሬት ዋጋው ይጨምራል በሚል ዕሳቤ ቦታ ከወሰዱ በኋላ ለረጅም ጊዜ አጥረው የሚያቆዩ ተቋማት እና ግለሰቦች ከተማው ሊያገኝ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያሳጡ ነው።

የከተማው አስተዳደር በመሬት እና መሬት ነክ ጉዳዮች ላይ ሲያካሂድ የቆየውን ጥናት ማጠናቀቁን የወዝ ኒውስ መረጃዎች አመልክተዋል።

የመሬት አስተዳደሩን ዘመናዊ ማድረግ አለመቻሉ ፣ ሌብነትና የመሬት ወረራ፣ ጠንካራ የፍትህ ስርዓት አለመኖር ሕዝቡን በዘርፉ የጸረ ሌብነት ትግል ላይ አለማሳተፍ እና ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ስራ አለመሰራቱ ተጠቃሽ ችግሮች መሆናቸው በጥናቱ ተመልክቷል።

በጥናቱ ላይ ትኩረት ካገኙ ነጥቦች መሃከል የከተማው መሬት ለምዝበራ የተጋለጠ መሆኑ ተጠቃሽ ነው። በቀጣይነትም ህበረተሰቡን በማሳተፍ ሙሰኞችን ለህግ የማቅረብ ጉዳይ ትልቁ የቤት ስራ መሆን አለበት ተብሎ መወሰኑን የወዝ ኒውስ መረጃዎች አመልክተዋል።

Via – WZ news / Wudineh Zenebe

Exit mobile version