Site icon ETHIO12.COM

ህፃን መጥለፍ 10 ሚሊዩን ብር ሲጠይቁ በነበሩ ሶስት ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ህፃን ሳሙኤል ዩሃንስ ይዘው በመሰወር 10 ሚሊዩን ብር ሲጠይቁ በነበሩ ሶስት ግለሰቦች ላይ በፈፀሙት ከባድ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን መጥለፍ ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተው በ1ኛ መሪጌታ ምስጥሩ ይግዛው፣ 2ኛ ዘውዲቱ ገብሬ እና በ3ኛ ብሩክ ቸኮል የተባሉ ተከሰሾች ላይ ነው፡፡

ተከሳሾች ህጻን ሳሙኤልን በተቀናጀ አካሄድ ይዘውት መሰወራቸውን ተከትሎ ጉዳዩ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስ እና የደህንነት መስርያ ቤት ከፍተኛ ኦፕሬሽን በማካሔዳቸው ህጻኑን ከቤተሰቦቹ ጋር እንዲገናኝ ማድረግ የተቻለ ሲሆን በተጨማሪም ወንጀል ፈጻሚዎቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ፖሊስና ዐቃቤ ህግ በጋራ የምርመራ ስራዎችን ሲያካሂዱ ቆይተው የምርመራ ሂደቱ ተጠናቆ ነው ዐቃቤ ህግ ወደ ክስ ምስረታ የገባው፡፡

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 1ኛ መሪጌታ ምስጥሩ ይግዛው፣ 2ኛ ዘውዲቱ ገብሬ እና 3ኛ ብሩክ ቸኮል የተባሉት ተከሳሾች ባቀናበሩት የወንጀል ድርጊት ሁለተኛ ተከሳሽ ከዚህ በፊት ተቀጥራ ስትሰራበት በነበረ የመኖሪያ ቤት ውስጥ እድሜው 2 ዓመት ከ11 ወር የሆነው ህጻን መኖሩን ለ1ኛ ተከሳሽ በጠቆመችው መሰረት ህፃን ሳሙኤል ዩሃንስን በ2ተኛ ተከሳሽ አማካኝነት ከቤት በማስወጣት ጠልፈው በመሰወር ከግል ተበዳይ ቤተሰቦች ብር ለመቀበል ተነጋግረው በድጋሜ ስራውን ለቃ ከቆየችበት የመኖሪያ ቤት ተቀጥራ እንድትገባ ይስማማሉ፡፡

ለዚህ ወንጀል ዓላማ ሲባልም 2ኛ ተከሳሽ ተመልሳ በቤት ሰራተኝነት በግል ተበዳይ ወላጆች መኖሪያ ቤት በመቀጠር ስትሰራ ከቆየች በኃላ ወንጀሉን ለመፈጸም ምቹ ጊዜና ሁኔታን ስትጠብቅ ቆይታ ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ለሚኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 10 ክልል ልዩ ቦታው አያት ጣዕመ ዳቦ ቤት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው ተቀጥራ ከምትሰራበት የመኖሪያ ቤት ውስጥ ህጻን ሳሙኤልን ማስቲካ ልግዛለት ብላ በማታለል ይዛው ከቤት በመውጣት በወቅቱ እዛው አካባቢ ይጠብቁዋት ከነበሩ 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በመገናኘት ከአዲስ አበባ ውጭ ይዘውት ተሰውረዋል፡፡

በኋላም አንደኛ ተከሳሽ ለህጻኑ አባት በመደወል ህጻኑ ከእነሱ ጋር እንዳለ እና 10 ሚሊዮን ብር ካላመጡ እንደሚሸጡት እንዲሁም ሌሎች ማስፈራሪያዎች እየዛተ በመናገር ሲደራደር ሶስተኛ ተከሳሽም በተመሳሳይ በመደወል ብሩን ቶሎ ካልከፈላችሁ ህጻኑን ወደ መተማ ሊወሰዱት ነው በማለት ገንዘቡን አስፈራርተው ለመቀበል ሲደራደሩ ቀናት ያስቆጠሩ ሲሆን በተደረገው ከፍተኛ ክትትል ጥቅምት 16 ቀን 2015 ዓ.ም 1ኛ ተከሳሽ በፖሊስ ከተያዘ በኋላ የግል ተበዳይ ጨምሮ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በኦሮሚያ ክልል ኢጅሬ ወረዳ አዲስ አለም ከተማ ጨረቃ ሠፈር በሚገኝው 1ኛ ተከሳሽ ተከራይቶት በነበረው ቤት ውስጥ በፖሊስ እጅ ከፍንጅ ሊያዙ ችለዋል፡፡

ጉዳዩ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የልዩ ልዩ ወንጀል ችሎትም ተከሳሾች በፈፀሙት ከባድ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን መጥለፍ ወንጀል ህዳር 13 ቀን/2015 ዓ.ም ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑን ተከትሎ የተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት ከባድ በመሆኑ ከጠበቃ ጋር ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ለህዳር 20 ቀን/2015 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል

Via በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር

Exit mobile version