Site icon ETHIO12.COM

አሁን ላይ ያለው ኢኮኖሚያችን “ጤናው የተጓደለ ነው፤ መታከም ግን ይችላል” ፕሮፌሰር መንግስቱ ከኢኮኖሚክስ አሶሴሽን

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ለትርፍ ያልተቋቋመ፤ ከፖለቲካ እና ሃይማኖት ገለልተኛ የሆነና 5ሺ400 አባላትን ያቀፈ የሙያ ማህበር ነው። ዓላማዎቹም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማራጮች ላይ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ለፖሊሲ እና ኢንቨስትመንት ውሳኔ የሚረዱ የመረጃ ግብዓት መስጠት፤ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎችን የሙያ ፍላጎቶችና ጥቅሞች እንዲጎለብቱ ማገዝ፤ የምርምር ውጤቶች በኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሰራጩ ማድረግ፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዝግጅትና ትግበራን የሚያግዙ ስልጠናዎችን መስጠት፤ ሀገራዊና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረኮችን መፍጠር እና በኢትዮጵያ ውስጥ እና በውጭ ሀገር ባሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች መካከል ሙያዊ ግንኙነት እንዲዳብር ማበረታታት ናቸው።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሼሽን ለሚያቀርባቸው ትንታኔዎችና ጥናቶችም በዋናነት የማዕከላዊ ስታትስቲክስ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ ዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት፣ ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት እና ሌሎችን የመረጃ ምንጮች በዋናነት ዋቢ አድርጎ ይጠቀማል። የዝግጅት ክፍላችንም ከአሶሴሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር መንግስቱ ከተማ ጋር የሀገሪቱን ወቅታዊ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን አስመልክቶ ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሼሽን የሚያካሂዳቸው ጥናቶች ምን ላይ ያተኩራሉ?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡- የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ መዋቅር የሚዳስስ በተለይም ደግሞ ከዋጋ ግሽበት ጋር በተያያዘ ምን ላይ ማተኮር ይገባል የሚለው ጉዳይ ላይ ጥናት ተካሂዷል። ከዚህም በተጨማሪ በኢኮኖሚ ጋር ዝምድና ያላቸው በርካታ ጉዳዮችን ይዳስሳል። በዚህ ውስጥ የሀገሪቱ ምጣኔ /ሃብት ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል የራሱን ድርሻ የሚወጣ ይሆናል። ጥናቶቹ የሚለኩት ባላቸው ሀገራዊ ፋይዳ እና ዜጎች ተጠቃሚ መሆን በሚገባቸው አንኳር ጉዳዮች ላይ ነው። ለፖሊሲ አውጪዎችም እንደ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግል ነው።

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጤናማ ነው?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡- አሁን አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ስንገነዘብ ኢኮኖሚው ያለበት ሁኔታ ጤናው የተጓደለ ነው፤ ነገር ግን መታከም ይችላል። ጤናው የተስተጓደለ ነው የምንለው በርካታ ችግሮችን እያለፈ በመሆኑ ነው። በመጀመሪያ ኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ በሀገሪቱ ውስጥ የነበረው ግጭት አደገኛና በኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ጫና የፈጠረ ነው። በሦስተኛ ደረጃ በሀገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ነው።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ የራሺያ እና ዩክሬን ጦርነት በሀገራችን ምርቶች ላይ ያስከተለው የዋጋ ጫናም ከፍተኛ ነው። ሀገሪቱም ከፍተኛ የዕዳ ጫና አለባት። የገቢ እና ወጪ ንግድ ሚዛንም የተጣጣመ አይደለም። የመንግሥት በጀት፣ የመንግሥት ወጪ እና ገቢው ሲታይም ያልተጣጣመ ነው። ሙስናም የተንሰራፋበት ሁኔታ ይታያል። እነዚህ ሁኔታዎችን ደምረን ስናይ ጤናማ ነው ማለት ይከብዳል።

አዲስ ዘመን፡- ኢኮኖሚው መታከም የሚችል ነው ብለዋል። ችግሩ በምን ደረጃ ይገለፃል?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡- የዋጋ ግሽበቱ ቢታይ በጣም ከፍ ያለ ነው። ጥቅል የዋጋ ግሽበቱ 33 ከመቶ ነው። የምግብ 43 ከመቶ ደርሷል። ይህ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሯል። በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው፣ ምንም ገቢ የሌላቸው እና በጡረታ በሚተዳደሩት ላይ በጣም ጫና ይፈጠርባቸዋል። ይህ ሁኔታ ሄዶ ሄዶ ወደ ንጥቂያ ሊያመራ እና ዘረፋ ሊስፋፋ ይችላል። ወንጀሎችም ሊበራከቱ ይችላሉ። ህዝብ ውስጥ ከፍተኛ ብሶት አለ። ነገር ግን በሌላ ሀገር የሚታየው ህገ ወጥነት አይታይም። የኢትዮጵያ ህዝብ ታጋሽ ነው። ህዝብ መንግሥት ያለፈበትን የጦርነት ሁኔታ፣ የኮረና ቫይረስ ስርጭት የፈጠረውን ጫና በመገንዘብ መንግሥትን መፍትሄ ያመጣል በማለት በመጠበቅ ላይ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- በፆታ ረገድስ የኑሮ ውድነቱ ሴቶች ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ በጥናት ለማካተት ተሞክሯል?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡– ከፆታ አኳያ ተንትነን አላየንም። ያየነው በኑሮ ደረጃ ነው። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉት ይጎዳሉ። በአጠቃላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በጣም እየተጎዱ ነው። ገቢያቸው ሌላ ወጪ መሸፈን ቀርቶ የምግብ ወጪ አይሸፍንላቸውም። በሌላ ሀገር የሚስተዋለው እኛ ሀገር እየተስተዋለ አይደለም፤ ህዝብ ታጋሽ ነው። መፍትሄ ይመጣል በሚል በትዕግስት የሚጠብቅ ህዝብ ነው ያለው።

አዲስ ዘመን፡- የጎረቤት ሀገራት ቀጣናዊ ትስስርና የኢኮኖሚ አቅማቸው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በመደገፍ ረገድ እንዴት ይመለከቱታል?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡- መጠነኛ መደጋገፍ አለ። ነገር ግን ወደ ውጭ የሚልኩት ተመሳሳይ ምርቶችን ነው። ከእነርሱ የሚገባ ቢኖርም በቂ አይደለም። በዚያ ላይ ተመስርተን ኢኮኖሚያችን ማስቀጠል ይከብዳል፤ ግን እንደአማራጭ መጠቀም ይቻላል። ከውጭ የምናስገባቸውን በበቂ ደረጃ ከጎረቤት ሀገራት ማግኘት ከባድ ነው። ነገር ግን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል በሚገባ ሲያመነጭ ወደ ውጭ የመላክ ዕድላችን ሰፊ ይሆናል።

በሌላ በኩል ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች ለመተካት በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል። ለምሳሌ የአፈር ማዳበሪያ መቶ በመቶ የሚገባው ከውጭ ነው። በዚህ ላይ ማተኮር አለብን። የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ ሀገር ውስጥ ያሉ ፋብሪካዎች ዘይት በበቂ ደረጃ ማምረት አለባቸው። ይህን ማድረግ ከተቻለ የተመረተውን ዘይት ወደ ውጭ መላክ የበለጠ ገቢ ያስገኛል። በተቻለ መጠን በዚህ ዘርፍ ራስን ለመቻል ርብርብ ማድረግ ይገባል። በርካታ የሀገራችን ክፍሎች የቅባት አህል አምራች በመሆናቸው በዘይት ምርት ራሳችንን ችለን ወደ ጎረቤት ሀገራት የመላክ ዕድላችን ሰፊ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መታወክ የጀመረው መቼ ነው?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡- ችግሩ መዋቅራዊ ነው። ቀደም ብሎ የጀመረ ነው። የተለያዩ ዘርፍ የሚባሉ አሉ። የግብርናው እና ኢንዱስትሪ ዘርፍ አምርተው ምርታቸውን ማቅረብ ላይ ገና ናቸው። እነዚህ ነገሮች የመቀነስ አዝማሚያ እያሳዩ ነው። እኛ ሀገር አገልግሎት ዘርፍ እየጨመረ ነው። የአገልግሎት ዘርፍ ጨመረ ማለት ፍላጎት ይጨምራል እንጂ ምርታማነት አይጨምርም። ይህ ጤናማነት አይደለም። በቅርብ ዓመታት ደግሞ ብሶበታል። በሀገር ውስጥ በነበረው ጦርነት፣ በራሺያ እና ዩክሬን ጦርነት፣ በኮረና እና ሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ብሶበታል።

አዲስ ዘመን፡-የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሼሽን በዓመት ምን ያክል ጥናት ያካሂዳል?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡- በአማካይ በዓመት እስከ 15 ጥናቶችን ያካሂዳል። እስካሁን ያሉት ጥናቶች ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሰጥተናል። በዚህ ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤትን ጨምሮ ለ10 የመንግሥት ተቋማት ተጠይቀን ሰጥተናል። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ እና በሦስት ሀገራት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ በተለይም በግድቡ ድርድር ላይ ኢትዮጵያ ምን ይዛ መቅረብ አለባት የሚለውንም አጥንተን አቅርበናል። ስደት ላይ እንዲሁም የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚያስከትለው ተጽዕኖ እና መደረግ ስለሚገባው መፍትሄም ጥናት አዘጋጅተን አቅርበናል። በተጨማሪም በዋጋ ግሽበት ላይም ጥናቶችን አቅርበናል።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሼሽን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የከፋ ማነቆ ይሆናል በሚል እንደ ሥጋት የሚመለከተው ነገር አለ?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡- አዎ! ስጋቱ ጦርነቱ ነው። ይህ ጦርነት የሚቀጥል ከሆነ እና እዚህም እዚያም ግጭቱ የሚቀጥል ከሆነ ኢኮኖሚው ወደ ጤንነት ይመለሳል ብለን አናምንም። ምክንያቱም ጦርነት ባለበት ቦታ ምርት ይቆማል። የተመረተም ቢኖር ስርጭቱ ላይ ችግር ይኖራል። ስለዚህ ይህ በዋጋ ንረት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል። የሰው ሕይወትም ሆነ ንብረት ውድመትም በተመሳሳይ ሁኔታ አደጋ ይገጥመዋል። ትልቁ ተግዳሮት ጦርነት ነው። ስለዚህ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞም ከሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት ሌላው ነው። አንዳንድ ሀገራት ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ሀገሪቱ ላይ ጫና እየፈጠሩ ነው። በመሆኑም ግጭቱ ትልቅ ፈተና ይሆናል ብለን እናስባለን።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ የህዝብ ብዛት መጨመር ኢኮኖሚው ላይ ጫና አይኖረውም?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡- ከህዝብ ብዛት ጋር በተያያዘ ጥናት አካሂደናል። የህዝብ ቁጥር መጨመር በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ስላለው በዚህ ላይ ትልቅ ሥራ መሠራት አለበት። የሥነ-ህዝብ ፖሊሲም መጠናት አለበት ብለናል። ሀገሪቱ ያላት የሥነ-ህዝብ ፖሊሲ ከ30 ዓመት በፊት የነበረው ነው። በመሆኑም አዲስ ፖሊሲ መውጣት አለበት። ነገር ግን ህዝብ መቀነስ ብቻ ውጤታማ አያደርግም። አሁን ባለው ህዝብ ምርታማነትን መጨመር ይቻላል። በዓመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ ማረስ ይቻላል።

የህዝብ ቁጥር መጨመር እንደ ጥሩ አጋጣሚ መውሰድ ይቻላል። ቻይናን እንደ አብነት ብንወስድ የአንድ ልጅ የመውለድ ፖሊሲ አወጣች። በመቀጠል ሁለት ልጅ መውለድ ይቻላል የሚል ፖሊሲ አወጣች። በመቀጠል ደግሞ ሙሉ ለሙሉ አነሳችው። ይህ የሆነው ህዝባቸውን ምርታማ በማድረጋቸው ነው። በመሆኑም የህዝብ ቁጥርን መቀነስ ብቻውን ግብ አይደለም። ጎን ለጎን ምርታማነት ላይ መሥራት ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- ለዋጋ ግሽበት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡- የዋጋ ግሽበት የሀገራችን የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡ የተፈጠረው የኑሮ ውድነት የህብረተሰቡን ህልውና እየተፈታተነ ይገኛል። የሁሉንም ህብረተሰብ ክፍል የመግዛት አቅም የሚቀንስ ሲሆን የድሃ ድሃ የሆኑትን ዜጎች ክፋኛ እየጎዳ ይገኛል። የዋጋ ግሽበት በጠባቡ ሲተረጎም በኢኮኖሚው ውስጥ የገንዘብ ፍሰት ሲበዛና የሚገዛው ዕቃ እና አገልግሎት ሲያንስ የሚፈጠር ክስተት ነው። ሲተነተን ግን በውስጡ ውስብስብ በሆኑ፤ የተሳሰሩ ኢኮኖሚያዊ የሆኑ እና ኮኖሚያዊ ያልሆኑ ጉዳዮችን የያዘ ነው ለምሳሌ፤ የኢኮኖሚ አስተዳደር (gov­ernance) በተመለከተ ኢኮኖሚውን መቆጣጠሪያ የህግ ማዕቀፎች መጥበቅና መላላት፤ የንግድ ህጎች፤ የመንግሥት መዋቅር ክፍተት አስተዋጽኦ አላቸው።

የምርት ገበያ በተመለከተ የግብዓት ዋጋ፣ ቀረጥና ግብር፣ የኢኮኖሚ ድጎማ (subsidy)፤ የግብይት ሰንሰለትና መዋቅር (marketing chain and struc­ture) ይገኙበታል። የፋይናንስ ገበያ በተመለከተ የብድር አቅርቦት፤ የወለድ መጠን፤ የውጭ ምንዛሪ፣ እና የገንዘብ አቅርቦት ይገኙበታል። እነዚህን በሁለት ዋና ዋና ጎራዎች ከፍሎ ማየት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- የአቅርቦት ምንጮች እንዴት ይገኛሉ። የአቅርቦት ማነስ ከምን ይመነጫል?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡- አቅርቦት ከሁለት ምንጮች ይገኛሉ። ሀገራዊ ምርት እና ገቢ ንግድ (imports) ላይ ነው። የነፍስ ወከፍ የምግብ እህሎች ምርት መቀነስ ለዋጋ ግሽበት ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል። በ1990 ዎቹ አንድ ኩንታል ምርት በነፍስ ወከፍ የነበረው ዕድገት እያሳየ መጥቶ እ.ኤ.አ በ2016 ዓ.ም 2ነጥብ65 ኩንታል ደርሶ ነበር። ሆኖም ግን ከ2016 በኋላ ማሽቆልቆል ጀምሯል። የጥራጥሬ እህሎች ምርትም እንዲሁ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በመቀነስ ላይ ሲሆን፤ የቅባት እህሎች ምርት አነስተኛ ቢሆንም የተረጋጋ ምርት እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ። የአትክልት የነፍስ ወከፍ ምርት ዕድገት ለብዙ ዓመታት ከአንድ ኩንታል በታች ነበር። በ2005 አንድ ኩንታል ደርሶ በመቀጠልም 2012 ላይ ደግሞ 1ነጥብ5 ኩንታል ከደረሰ በኋላ በማሽቆልቆል ላይ ይገኛል። በሌላ በኩል ፍራፍሬ በመጠኑም ቢሆን መሻሻል በማሳየት በነፍስ ወከፍ አንድ ኩንታል ደርሷል።

የሥጋ ምርት ዕድገት ባለፉት በርካታ ዓመታት ከፍተኛ መዋዠቅ የታየበት ነው። እ.ኤ.አ በ2010 ላይ 8ነጥብ5 ኪሎ ግራም ደርሶ አሁን ሰባት ኪሎ ግራም ገደማ ነው። ለህጻናት ከፍተኛ አልሚ የሆነው የወተት ምርት እስከ 2010 እየዋዠቀም ቢሆን የመጨመር ሂደት ነበረው። እ.ኤ.አ ከ2010 በኋላ ከፍተኛ ማሽቆልቆል ላይ ይገኛል።

የእንቁላል ምርት ከሁሉም ምርቶች በበለጠ የመዋዠቅ ባህሪ የሚያሳይ መሆኑን የጥናቱ ውጤት ያመለክታል። አጠቃላይ የኢንዱስትሪ ምርት በነፍስ ወከፍ ዕድገት በተከታታይ እስከ 2010 ሲጨምር ቆይቶ እ.ኤ.አ ከ2016 በኋላ ማሽቆልቆል ላይ ይገኛል። ሦስቱን የኢኮኖሚ ዘርፎች ስንመለከት ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ሲነጻጸሩ ግብርናው እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ ከነበረበት 60 ከመቶ በግማሽ ወርዶ ይታያል።

የኢንዱስትሪው ድርሻ ከ10 ከመቶ በታች ከነበረበት ወደ 30 ከመቶ እየተጠጋ ይገኛል። በሌላ በኩል የአገልግሎት ዘርፍ ከነበረበት 30 ከመቶ ወደ 40 ከመቶ ዕድገት አሳይቷል። ይህ ዘርፍ የመሪነት ደረጃ መያዝ የሚያመለክተው ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ችግር እንዳለበት የሚጠቁም ነው።

የአቅርቦት ዕድገት በዋጋ ግሽበት ላይ ያለውን ተጽዕኖ ስንመለከት የግብርና አጠቃላይ ምርት ማደግ ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው የገበያ ዋጋውን የማረጋጋት ባህሪ አለው። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የኢንዱስትሪ ምርትና እና የአገልግሎት ዘርፍ ማደግ የዋጋ ግሽበትን እንደሚያባብስ መረጃዎች ያሳያሉ።

አዲስ ዘመን፡- የሀገሪቱ የንግድ ሚዛንስ እንዴት ይታያል?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡- የገቢ ንግድን በተመለከተ እስከ 2016 በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ወጥቶ 20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሶ ነበር። በአሁኑ ወቅት 18 ሚሊዮን ገደማ ይገኛል። ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ጋር ሲታይ ግን እ.ኤ.አ በ2010 ከነበረበት 30 በመቶ፣ በ2020 ወደ 17 ከመቶ ዝቅ ብሏል። ይህም ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ዝቅተኛ ገቢ ንግድ ተሳታፊ አራት ሀገራት አንዷ ያደርጋታል።

የወጪና ገቢ ንግድ ግብይት የሚካሄደው በውጭ ምንዛሪ እንደሆነ የምንዛሪው ውጣ ውረድ የዋጋ ግሽበት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ይታወቃል። እስከ 1990 ዎቹ መጀመሪያ ቋሚ የነበረው የምንዛሪ ዋጋ በመጠኑም ቢሆን በገበያ እንዲወሰን ተደርጓል። በመሆኑም የአንድ የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ከነበረበት 2ነጥብ07 ብር አሁን ከ50 ብር በላይ ደርሷል። ምንም እንኳ ቀደም ሲል የነበረው የብር ጥንካሬ የኢኮኖሚውን ጥንካሬ ባያመለክትም፤ አሁን ባለው ፍጥነት የብር ዋጋ ማሽቆልቆሉ የዋጋ ግሽበቱን ካባባሱት ጉዳዮች አንዱ ሆኗል።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ከውጭ ገቢ ምርቶች ላይ የሚጣለው ታሪፍ ተወዳዳሪ ያደርጋል?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡– በወጪ እና በገቢ ንግድ ላይ የሚጣለው ታሪፍ መንግስት ገቢ እንደሚጨምር ይታመናል። ከዚህም ከፍተኛ ገቢ በመሰብሰብ ኢትዮጵያ ከ10 የአፍሪካ ሀገራት ሠባተኛ ስትሆን፤ ከፍተኛ የታሪፍ መጠን በመጣል አራተኛ ላይ ትገኛለች። መረጃው እንደሚያሳየው ከፍተኛ የታክስ ገቢ ዋጋ ግሽበትን ያባብሳል። የወጪ ንግድን በተመለከተ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ተሳታፊ ከሚባሉ 10 የአፍሪካ ሀገራት ሦስተኛ ነች። የወጪ ንግድ እያደገ ሲመጣ የዋጋ ግሽበትን ሊያባብስ እንደሚችል ይታመናል። ይህን ማመጣጠን ከፍተኛ የፖሊሲ እሳቤ ይጠይቃል። በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚከሰቱ ግጭቶች የአቅርቦት ሰንሰለቱን (supply chain) በማስተጓጎል የዋጋ ግሽበትን አባብሷል። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሁለቱ ሀገራት ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸውን ሀገራት ኢኮኖሚ የሦስት መሰረታዊ ዕቃዎች አቅርቦት ማለትም ምግብ፣ ነዳጅና ማዳበሪያ አውኳል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በሦስቱም መሰረታዊ ዕቃዎች ራሳቸውን ያልቻሉ፤ የገበያ አማራጭና ክምችት የሌላቸው፤ ከግጭቱ በፊት በሌሎች ችግሮች የተወጠሩ ሀገራት ክፋኛ ተጎድተዋል።

አዲስ ዘመን፡- በየጊዜው የፍላጎት መጨመር ኢኮኖሚያዊ እሳቤውና ትርጉሙ ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡- የፍላጎት መጨመር ከላይ እንደተጠቀሰው የገንዘብ ፍሰት አለመመጣጠን የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል። የገንዘብ ፍሰትን የሚያመጣጥነው ከተቀማጭ ገንዘብ የሚከፈለው ወለድና ከብድር የሚጠየቀው ወለድ ነው። ከተቀማጭ ከፍተኛ ወለድ ከተሰጠ ገንዘብ የማስቀመጥ ዝንባሌ ይጨምርና በኢኮኖሚው ውስጥ የገንዘብ ፍሰት ይቀንሳል። ወለዱ ዝቅተኛ ከሆነ ገንዘብ የማስቀመጥ ዝንባሌ ይቀንስና በኢኮኖሚው ውስጥ የገንዘብ ፍሰት ይጨምራል። ይህም የዋጋ ግሽበትን ያባብሳል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ለተቀማጭ (ቁጠባ) ዝቅተኛ ወለድ ከሚሰጡ 10 የአፍሪካ ሀገራት ስምንተኛ ደረጃ የያዘች መሆኑን መረጃው ያሳያል።

አዲስ ዘመን፡-ከምግብ ፍጆታዎች ለዋጋ ግሽበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉት ያሉት የትኞቹ ናቸው?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡- ከግብርና ምርቶች የእህል ዋጋ እስከ 39 ከመቶ፤ የቁም ከብቶችና የእስሳት ተዋጽኦ 18 ከመቶ ድርሻ አላቸው። ቀጥታ ከምንመገባቸው ውስጥ ዳቦ 42 ከመቶ፤ አትክልትና ፍራፍሬ 19 ከመቶ ድርሻ አላቸው። ምግብ ነከ ካልሆኑት የቤት ኪራይ፤ ውሃ እና መብራት 35 ከመቶ፤ ህክምና፤ ትራንስፖርት፤ የቤት ዕቃ 13 ከመቶ፤ ልብስና ጫማ እንዲሁ 13 ከመቶ ድርሻ አላቸው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ካላቸው 10 የአፍሪካ ሀገራት ዘጠነኛ ላይ ትገኛለች።

አዲስ ዘመን፡-የኢትዮጵያን ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ለፖሊሲ አውጪዎች የሚሰጠው ምክር ሐሳብ ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር መንግስቱ፡- ተግዳሮቶች ለፖሊሲ እርምጃ መንደርደሪያ ናቸው። በመሆኑም የግብርና ምርታማነትን የሚያፋጥኑ የአሰራር ዘዴዎችን ለአነስተኛ አርሶ አደሮች ማቅረብ፤ የገቢ ንግድ ላይ የሚጣለው ታሪፍ ተመጣጣኝ የሚሆንበትን መንገድ መፈለግ፤ ከተቀማጭ ገንዘብ የሚሰጠው ወለድና ከብድር የሚጠየቀው ገንዘብ የዋጋ ግሽበትን ያገናዘበ እንዲሆን ማድረግ ሊወሰዱ ከሚችሉ እርምጃዎች ጥቂቶቹ ናቸው። በመንግሥት አካላትና በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታዩ ብክነቶች ማስወገድ፤ የኃይል አጠቃቀም ማሻሻልና በዋጋ ግሽበቱ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ መደገፍ ያስፈልጋል። የዓለም አቀፍም ሆነ ሀገራዊ ሠላምና መረጋጋት ማስፈን፤ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ስለሚያሳልጠው የዋጋ ግሽበቱን ይቀንሳል፤ ቢያንስ ዋጋውን የማረጋጋት ሚና ይኖረዋል።

እነዚህ የፖሊሲ እርምጃዎችን ሥራ ላይ የማዋል ኃላፊነት የመንግሥት ቢሆንም ጉዳዩ በመንግሥት አቅም ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ መንግሥትን ሊያግዝ የሚችል ነፃ የሆነ የአቅርቦትና ዋጋ ማረጋጊያ ቦርድ (Supply and Price Stabilization Board) ቢቋቋም ጠቃሚ ይሆናል። ይህ ቦርድም ከሚያከናውናቸው ተግባራት ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል። የሀገር ምርትና የገቢ ንግድ አቅርቦት አስተዳደር (ሚዛን ማስጠበቅ)፤ የዋጋን ማረጋጋት ካልሆነም የዋጋ ግሽበትን ግብ ማስቀመጥና ከዚያ እንዳያልፍ መከታተል፤ የዋጋ ግሽበት በማህበረሰቡ ላይ በተለይም የድሃ ድሃ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ የሚቀንሱ የፖሊሲ እርምጃዎችን ማቅረብ፤ የተለያዩ ሴክተሮችን ማስተባበር ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ምክረ-ሐሳብ ይሰጣል፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን  ሚያዝያ 26 /2014

Exit mobile version