ETHIO12.COM

ስሉሱ ዞረ! ጉተሬዝ አብይ ቢሮ ገቡ፤ ትህነግ ለሰላም መስዋዕትነት እንደሚከፍል አስታወቀ፤ ጦሩን ሰበሰበ

– አዲስ አበባ የመሸገው ቢቢሲ ሌላ ዘመቻ በማቀጣጠል ተጠምዷል

አሁን ላይ የሰላም ስምምነቱ መሬት እየነከሰ ይመስላል። በአዲስ አበባ የአራት ኪሎ ግቢ ሱሉሱ መዞሩን የሚያሳይ ዜና ሲሰማ፣ በትግራይ ትህነግ ውሉን አክብሮ ጣጣቂዎቹን ከግንባር እያስወጣ መሆኑንን ይፋ ተናግሯል። እንዲህ ያለው የሰላም ዜናና የተባበሩት መንግስታት መሪ አዲስ አበባ አራት ኪሎ መድረሳቸው ቢቢሲ አማርኛውን ጨምሮ ዜናቸው አልሆነም በሚል እየተተቹ ነው።

ጉተሬዝ አዲስ አበባ ናቸው

በአዞ ቆዳ የሚመስለው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ከዛ ሁላ መከራና ዓለም ዓቀፍ አድማ በሁዋላ በሕዝብ የጸና ድጋፍ ጸንቶ የተባበሩት እመንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አዲስ አበባ መግባታቸው ታላቅ ዜና ሆኗል። ይህ ታላቅ ዜና ለቢቢሲ ከትህነግ አፈቀላጤ ጌታቸው አንድ ቲውተር አንሶ ለቢቢሲ ኮሶ ሆነበት ዜናውን ባልሰማ አልፎታል። ይልቁኑም “ኦነግ” እያለ የሚጠራው ሸኔ ሰርቶ አደሮችን ማፈኑንን ” የግርብ አዋቂ ምንጮቼ ነገሩኝ” ሲል ታላቁን ዜና ውሃ ሊቸልስበት ሞክሯል።

ይህን የታዘቡ ” ንጹሃን መታፈናቸው የሚወገዝ ፣የዓለም ድርጅት አዲስ አበባ መግባታቸው፣ እንዲሁም የትህነግ ሰራዊት ምሽጉን ለቆ እየወጣና መከላከያ እየተረከበ መሆኑ የተስፋ ዜና መሆን ሲገባው ቢቢሲና መሰሎቹ በመርዶና ሌላ ክፋት በማቀነባበር ዜና መጠመዳቸው ለወደፊት የተዘጋጀ መርዝ ስለመኖሩ አመላካች ነው” ብለዋል። አያይዘውም መንግስት በሃያ አራት ሰዓት ሊያባርራቸው እንደሚገባ አመልክተዋል። “የባንዳ ተከፋዮችና አፎች በርካታ ናቸው ምንም አያመጡም ይጩሁ” ሲሉ የሚሳደቡም አሉ። ሁሉም ሆኖ ግን ጉተሬዝ አዲስ አበባ ገብተው በአራት ኪሎ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር መነጋገራቸው ምንም ይባባሉ ሱሉሱ መዞሩን የሚያረጋግጥ ዜና እንደሆነ አብዛኞች ይስማማሉ።

ኢዜአ እንዳለው ኢትዮጵያ በሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትና በልማት ለምታደርጋቸው ጥረቶች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አስታውቀዋል። ለዚህም በመንግስታቱ ስር ያሉ የልማትና የተራድኦ ድርጅቶች አቅማቸውን አጠናክረው ድጋፍ እንዲያደርጉ ይሰራል ነው ያሉት።

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዩ ጉቴሬዝ ይህን ያሉት 6ኛው የአፍሪካ ህብረት እና የተመድ ዓመታዊ ጉባዔ መጠናቀቅን በሚመለከት አዲስ አበባ ተገኝተው ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀማት ጋር በሰጡት መግለጫ ነው። በመግለጫቸውም ተመድ በአፍሪካ ሕብረት አመቻችነት ለተደረሰው የኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ተፈፃሚነት፣ ለመልሶ ግንባታ፣ ለሰብዓዊ ርዳታ ተደራሽነትና የመልሶ ማልማት እንቅስቃሴዎች ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካ የመፍታትን ሀሳብ በፅኑ ይደግፋል ያሉት ዋና ጸሃፊው ለሰላም ስምምነቱ ተፈፃሚነትም ለአፍሪካ ሕብረት እና ለሁሉም ባለድርሻ አካላት እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት። በዚህም የድርጅቱ የልማትና የተራድኦ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ እንደሚሰራ ተናግረዋል። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በኢትዮጵያ የሚደረገውን ሰብዓዊ እርዳታ እና የመልሶ ማልማት ጥረት እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል። የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ልማት፣ ለህዝቡ ሰላምና የኑሮ መሻሻል አማራጭ የሌለው ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ገልፀዋል።

ኤርትራና ኢትዮጵያ ተስማሙ

የትህነግ አመራሮች ከትግራይ መሬት እንዳልወጡ የሚከሱት የኤርትራ ሃይል ከመንግስት ጋር በተደረገ ስምምነት መሰረት እየወጣ መሆኑ፣ የቀሩትም ትህነግ ከባድ መሳሪያ ፈቶ ስጋት መሆኑ ሲያቆም ወደ ቀያቸው ለመመለስ መስማማታቸው ታውቋል። የቀድሞ ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ ስምምነት መደረሱን ገልጸው ማብራሪያ መስጠታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ትህነግ ከባድ መሳሪያ ከማስረከቡ በፊት እየቀበረና እየሰወረ መሆኑ እየተገለጸ ስለመሆኑ ያነጋገርናቸው እንዳሉት፣ ሊሆን ይችላል ግን ምንም ነገር ከመከላከያ እይታ ሊወጣ እንደማይችል፣ ብረት ያለበትን ቦታ ሁሉ የሚጠቁም ቴክኖሎጂ እንዳላቸው ጨምረው አስታውቀዋል። ሌላ ያነጋገርናቸው ግን ” ምን መሳሪያ አላቸው? ከባድ መሳሪያዎቻቸው በድሮን አረዋል። የተረፈ ቢኖርም እዚህ ግባ የማይባልና ያረጀ ነው” ብለዋል።

ትህነግ በይፋ ታጣቂዎቹን ከነበሩበት ግንባር ማንሳቱን አወጀ

“የትግራይ ሃይሎች” ሲል ትህነግ የጠራቸው ተዋጊዎቹ ከነበሩበት ግንባር ለቀው መውጣት መጀመራቸውን በፌስቡክ ይፋዊ ድረ ገጹ አትሟል።

ይህ የትህነግ ዜና የሰላሙን መንገድ ተስፋ የሰነቀ እንደሆነና ትህነግ ከሰላም አሳቡ የማፈንገጥ አዝማሚያ እንዳለው ሲናገሩ ለነበሩ ሁሉ መርዶ ሆኗል።

የሚታወቁ የትህነግ ደጋፊዎች ” ቦታ መልቀቅና ትጥቅ መፍታት የሚለያዩ ነገሮች ናቸው” በሚል በማህበራዊ አውዶቻቸው እያተሙ ሲሆን ለምንና ምን ፈልገው ይህን እንደሚሉ አላብራሩም።

በጨለማ፣ ከመገናኛ መሳሪያዎች ውጪ፣ ያለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች እንዲሁም ልጆቹን እየገበረ በስቃይና በርሃብ የከርመው የትግራይ ህዝብ ምን እንዲሆንለት በግልጽ የማያስቀምጡት እነዚህ ክፍሎች ” ትህነግ በትግራይ ህጋዊ መነግስት እንደሌለ ማመኑንና፣ አዲስ መንግስት እንዲቋቋም ቀን መቆረጡ ለምን እንዳስከፋቸው ሊገባን አልቻለም” በሚል በስፋት ለሚሰነዘር ጥያቄ መልስ አላዘጋጁም።

“መሪ ድርጅታችን” በሚል በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጧል” ሲሉ የነበረው ትህነግ ” ህገመንግስቱን ንጃለሁ” ብሎ አምኖ መቀበሉና አዲስ ጊዜያዊ የክልል ምርጫ እንደሚደረግ መስማማቱን የሚቃወሙ ወገኖች ለትግራይ ህዝብ አማራጭ አሳብ የላቸውም። ኦባሳንጆ በቅርቡ ስድስት መቶ ሺህ የሚጠጉ የትግራይ ታታቂዎች መሞታቸውን ማስታወቃቸውን የሜገልጹ እነዚህ ወገኖች ለትግራይ ህዝብ ምን እየተመኙለት እንደሆነ ማሰብ በራሱ አድካሚ እንደሆነ የሚናገሩ ” በአመክንዮ ማሰብ እዛ ሰፈር ሃጢያት ነው” የሚል ስላቅ ነው የሚሰነዝሩት።

ትህነግ በፊስ ቡክ ገጹ ይህን አስፍሯል

የትግራይ ሰራዊት በስሩ ከነበሩ የውግያ ግምባሮች ለቆ መውጣት ጀመረ

የትግራይ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጫት አልሞ በትግራይ እና ኢትዮጵያ መንግስታት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተከተሎ በኬንያ ናይሮቢ ከተማ ላይ በትግራይ ሰራዊት እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዋና አዛዦች መካከል ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት በፈረሙት የመተግበርያ ሰነድ መሰረት የትግራይ ሰራዊት ግጭት ለማስወገድ በሚያስችል መልኩ እንቅስቃሴ በማድረግ በስሩ ከነበሩት ግንባሮች ማለትም የደቡብ ፣ ማይ ቅነጣል፣ ዛላምበሳ፣ ነበለት ፣ ጨርጨር ፣ ኩኩፍቶ ፣ ሕጉምብርዳ ፣ በሪተኽላይ እና አበርገለ ለቆ መውጣት ጀምራል።

ከናይሮቢው ስምምነት ብኋላ የትግራይ ሰራዊት እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዋና አዛዦች ወደየ ቦታቸው ከተመለሱ ብኋላ ለአመራሩ እና ለመላው የሰራዊት አባላት ኦሬንቴሽን በመስጠት ግጭት ሊፈጥሩ ይችላሉ ከሚባሉ የውግያ አካባቢዎች እንዲለቁ በተፈረመው ስምምነት መሰረት፣የትግራይ ሰራዊት ስምምነቱ በቁርጠኝነት ለመተግበር በተሰጠው ኦሬንቴሽን እና መመርያ መሰረት ግጭት ሊፈጥሩ ከሚችሉ ግምባሮች ለቆ እየወጣ ነው።

የትግራይ ሰራዊት ቀድሞውንም ለሰላም እና ለህዝቡ ህልውና ብሎ ነው የታገለው ያሉት የትግራይ ሰራዊት አመራሮች እና አባላት ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፋት እና ሰላም አንደኛ ምርጫው መሆኑን በመግለፅ፤ በሰላም ስምምነቱ መሰረት ሰላም ከተፈጠረ፣ ውግያ የሚመርጡበት አንዳችም ምክንያት እንደሌላቸው ገልፀዋል።

የትግራይ ህዝብ ሰላም ፈላጊ ህዝብ ነው፣ እኛም የህዝባችን ጠባቂዎች እና ሰላም ፈላጊዎች ነን፣ ያሉት የትግራይ ሰራዊት አመራሮች እና አባላት ለዚህ ሲባል አብረን መስዋእት(ዋጋ )ስንከፍል ቆይተናል ብለዋል። ይህ የሰላም ስምምነት ወደ ተግባር ገብቶ ህዝባችን እውነተኛ ሰላም እንዲያገኝ ደግሞ በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል። ሲልየትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር አስታውቋል። መሬት ላይ ያለው እውነታ ይህ ነው።

ይህ መግለጫ ከመውታቱ በፊት ባተምነው ዜና ባጫ ደበሌ ” መሬት ላይ እየሆነ ያለውን መመለከት እንጂ ወሬ መስማት ዋጋ የለውም” ሲሉ ነገሮች በተሰመረላቸው መስመር መሰረት እየሄዱ መሆናቸውን አመልክተዋ እንደነበር ይታወሳል።

Exit mobile version