Site icon ETHIO12.COM

የመንግስት ያልተቋረጠ የሰብአዊ ድጋፍ ከችግር ታድጎናል-የሽሬ ነዋሪዎች

የመንግስት ያልተቋረጠ የሰብአዊ ድጋፍ ከችግር ታድጎናል ሲሉ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሽሬ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

መንግስት ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያደርጋቸውን መልካም ጥረቶች በማድነቅ ከሰብአዊ ድጋፍ ባሻገር መሰረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ በመገንባት ወደ ስራ ለማስገባት የሚያከናውነው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በትግራይ ክልል ሁሉም አካባቢዎች መንግስት ያልተቋረጠ የሰብአዊ ድጋፍና የመልሶ ማቋቋም ስራ እያከናወነ ሲሆን መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመርም በከፍተኛ ጥረት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በሰጠው መረጃ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ 32 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ለክልሉ ተደራሽ አድርጓል።

ከሽራሮ እስከ አድዋ ባለው አካባቢ ብቻ ከ535 ሺህ በላይ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙም ተደርጓል።

በአጠቃላይ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በመንግስት እየተደረገ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነትና ሌሎች ስራዎችን በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሽሬ ከተማ ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አስተያየት የሰጡት የአካባቢው ነዋሪዎች በትግራይ ክልል የመንግስት ያልተቋረጠ የሰብአዊ ድጋፍ ከችግር ታድጎናል ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በመንግስት በኩል የምግብ፣ የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁሶች በስፋት ባይገቡ ኖሮ የበርካቶች ህይወት ከፍተኛ ችግር ላይ ይወድቅ እንደነበርም ተናግረዋል።

በመሆኑም የመንግስት ቁርጠኝነትና እያደረገ ያለው ያልተቋረጠ ድጋፍ የሚመሰገንና የሚደነቅ ተግባር መሆኑን አስተያየት ሰጭዎቹ ገልጸዋል።

መንግስት ለዜጎቹ እያደረገ ያለው ያልተቋረጠ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳለ ሆኖ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ስራ ለማስጀመር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የኮሚሽነሩ ጽህፈት ቤት ሃላፊና የድጋፉ ጊዜያዊ አስተባባሪ ዘሪሁን ዘውዴ፤ ከሽራሮ እስከ አድዋ ባለው አካባቢ ብቻ ለ535 ሺህ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ መደረጉን አረጋግጠዋል።

በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍን ተደራሽ ለማድረግ የመንግስት ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።

Exit mobile version