Site icon ETHIO12.COM

“በተደራጀ ሌብነትና ሙስና ላይ የተጀመረው እርምጃ ሀገርን ከዘረፋ የማዳን ህዝባዊ ትግል ነው”

በተደራጀ ሌብነትና ሙስና ላይ የተጀመረው እርምጃ ሀገርን ከዘረፋ የማዳን ህዝባዊ ትግል መሆኑን የፌደራል ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነርና የጸረ-ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴው አባል ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ገለጹ።

በኢትዮጵያ ከኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ቀጥሎ የአገር ደህንነት ስጋት የሆነውን ሙስና ለመከላከል ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ እህመድ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡

ኮሚቴው ወደ ስራ በመግባት አርምጃ መውሰድ መጀመሩን ትናንት ያስታወቀ ሲሆን፤ በዚህም የፋይናንስ ድህንት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ በርካታ የመሬት አስተዳደርና የፀጥታና ፍትህ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይፋ ተደርጓል፡፡

የብሔራዊ ኮሚቴው አባልና የፌደራል ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሙስና እና የተደራጀ ሌብነት ህዝብን ያማረሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ መንግስት የጉዳዩን አሳሳቢነት በመገንዘብ የጸረ-ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል።

በዚህም መረጃዎችና ጥቆማዎች ከእጅ ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ ሲሰበሰቡ መቆየታቸውን ጥቅሰው፤ እስከ አሁን ባለው ሂደት 250 መረጃዎች ተለይተው ለምርመራ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኮሚቴው የህዝብ አመኔታ ያለው አሰራር እንዲከተል ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉንም ነው የገለጹት፡፡

በሙስና እና የተደራጀ ሌብነት ላይ የተጀመረው ትግል ሁሉን አቀፍ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ፤ የፌዴራል ተቋማት ኃላፊዎችን ጨምሮ በሙስና የተሳተፉ አካላት ላይ ያለርህራሄ እርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጠዋል፡፡
በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት የፋይናንስና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለንና ሌሎች የተቋማት ኃላፊዎችን በዚህ ረገድ በአብነት አንስተዋል፡፡

መንግስት የጀመረው የጸረ ሙስና ትግል ሀገርን ከዘረፋ የማዳንና ብሔራዊ ደህንነቷን የማረጋገጥ ስራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ትግሉ ህዝባዊ መሆኑን መገንዘበ ይገባል ብለዋል።

ሙሰኞች ለፍርድ ቀርበው ሀገር የምታጣውን ሀብት ማዳን የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም አመላክተዋል።

ኀብረተሰቡ በየጊዜው በሙሰኞች ላይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ ሲጠይቅ መቆየቱን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፤ የኮሚቴው መቋቋም ለህዝብ ጥያቄው ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ኮሚቴው በቀጣይ በተደራጁ የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪ ግለሰቦች ከወንጀል ተጠያቂነት ባሻገር በሙስና ያፈሩት ሀብት እንዲወረስ፣ ያሸሹትም እንዲመለስ ይሰራል ብለዋል፡፡

የጸረ-ሙስና ትግሉ የአንድ ወቅት ዘመቻ ብቻ ሳይሆን ተቋማዊ አደረጃጀትን በመያዝ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ኮሚሽነሩ ዶክተር ሳሙኤል አመላክተዋል። OBN NRWS

Exit mobile version