Site icon ETHIO12.COM

የወረዳ 5 ቤቶች ኃላፊ እጅ ከፍንጅ

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የወረዳ 5 ቤቶች ኃላፊ የሆነው አቶ ኢዶሳ ለሜሳ ጎቦ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ የተያዘው ህዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ነው።

የስራ ኃላፊው መኖሪያቸውን በወረዳው ያደረጉ አንድ ግለሰብን የግል መኖሪያ ቤት እንዳለህ መረጃ ደርሶናል ቤቱን ለቀበሌ ማስረከብ አለብህ ይላቸዋል።

የግል ተበዳይም በጤና ምክንያት አልፎ አልፎ ልጆቻቸው ጋር እንደሚሄዱ እና የቀበሌ ቤት እንደሌላቸው ይገልፁለታል።

ቤት እንዳላቸው በቂ መረጃ እንዳለውና ነገር ግን 50 ሺህ ብር ከሰጡት ቤቱን እንደማያስለቅቃቸው ይነግራቸውና በድርድር 30 ሺህ ብር ሊሰጡት ይስማማሉ።

አቶ ኢዶሳ ህዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም አዲሱ ሚካኤል አካባቢ ከሚገኘው የግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት ተገኝቶ 2 ሺህ ብር የተቀበለ ሲሆን፤ የግል ተበዳይ ጉዳዩን ለፖሊስ አሳውቀው ፖሊስ ባደረገው ክትትል ቀሪውን 28 ሺህ ብር ሲቀበል እጅ ከፍንጅ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

የግል ተበዳይ መረጃውን ለፖሊስ በማሳወቃቸው ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ የገለፀው ፖሊስ፤ መንግሥት የጀመረው የፀረ-ሙስና ትግል ስኬታማ እንዲሆን ህብረተሰቡ ተሳትፎን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

Exit mobile version