Site icon ETHIO12.COM

በአዲስ አበባ ት.ቤቶች የኦሮሚያ ባንዲራ እንዲውለበለብና መዝሙሩ እንዲዘመር የሚደረገው ጥረት እንዲቆም አብን አሳሰበ

በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ላይ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ እንዲውለበለብና መዝሙሩ እንዲዘመር የሚደረገው ጥረት እንዲቆም አብን አሳሰበ፡፡

ፓርቲው በአዲስ አበባ ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ትናንት ማምሻውን መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫውም፣ላለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት በአገራችን ሰፍኖ የኖረውን የአፓርታይድ አገዛዝ ለውጦ ዲሞክራሲያዊ ሥርአትን በማስፈን እኩልነትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ እንደሀገር በርካታ መስዋዕትነት የተከፈለ እና በብዙ ውጣውረዶች ውስጥ የታለፈ ቢሆንም፣ ሁኔታወች ዛሬም ከድጡ ወደ ማጡ እየሆኑ፣ ፈተናዎቻችን እየበረቱ እና አዳዲስ ችግሮች እየተፈጠሩ በአሁኑ ወቅት በአገራዊ ኅልውና እና አገራዊ አንድነታችን ላይ አደጋ የጋረጡ ፈተናዎች ለማያባራ ቀውስ ዳርገውን እንደ አገር እየታመስን እንገኛለን ብሏል፡፡

ይህን በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለ ምስቅልቅል የማስቆም ኃላፊነት ያለበት መንግስት በአሸባሪና አፍራሽ ሀይሎች ላይ ጨርሶ የበላይነት መያዝ ባለመቻሉ፣ ህግና ስርአት እንዲሁም ተጠያቂነትን ለማስፈን ቁርጠኛ ባለመሆኑና ፍላጎትም የሌለው በመሆኑ፣ እኩልነትና ፍትህን ለማስፈን ዳተኛ በመሆኑና ሃላፊነቱን ባለመወጣቱ፤ እንዲሁም ውስጠ መዋቅሩ የአፍራሽ ሀይሎች መደበቂያ ዋሻ በመሆኑና እኒሁ መንግስታዊ ሽፋን የተላበሱ አፍራሽ ሀይሎች የችግሮቻችን መነሻና አባባሽ በመሆናቸው ችግሮች እየተወሳሰቡ እንዲሄዱ አድርጓል።

በአሁኑ ወቅት በፌዴራል መንግስት መዋቅር ውስጥ በመሸጉ እኒሁ አፍራሽ አካላት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በኦሮሚያ ክልል የመንግስት መዋቅርን የሚዘውሩ አካላት መካከል የተናበበ ቅንጅት ምክንያት እየተባባሱ ካሉ ቀውሶች አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መዝሙር እና ባንዲራን በኃይል ለመጫን እየተሄደ ያለው የማን አለብኝነት አፍራሽ ዘመቻ ቀዳሚው ነው ብሏል ፓርቲው፡፡

በመሆኑም:-

1:- የኦሮሚያ ክልል መገለጫ የሆኑትን መዝሙር እና አርማን የአዲስ አበባ ከተማ ህጻናት ተማሪዎች በግድ እንዲዘምሩ እና እንዲያውለበልቡ በማድረግ የመላው ሀገሪቱ መዲና እንዲሁም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አፍሪካዊ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችን ከተማ የግጭትና የብጥብጥ ማዕከል እንድትሆን የሚደረገውን ጸብ አጫሪ አካሄድ አብን ያወግዛል፣ በአስቸኳይ እንዲቆምም ይጠይቃል::

2:- የችግሩ ጠንሳሽ እና አስፈጻሚው የኦሮሚያ ክልልን ህገወጥ እና ኢ-ፍትሐዊ የፖለቲካ ፍላጎት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ላይ በግዴታ በመጫን የከተማዋን ሰላም እየረበሹ እና የህዝብ-ለህዝብ ግንኙነቱን እያሻከሩ የሚገኙት ዋነኛ ተዋናዮች በፌዴራል መንግስት የተለያዩ እርከኖች መሽገው የሚገኙ፣ ህዝብ ታግሎ የጣለውን የትላንቱን የጭቆና አገዛዝ መልሶ እንዲመጣ በተለያየ አካሄድ ሀገርና ህዝብን የማተራመስ አጀንዳን ባነገቡ አካላት እና መሠል በኦሮምያ ክልል አስተዳደር ውስጥ በገሀድ የሚታይ ሸኔአዊ መዋቅር በቅንጅት የሚፈጽሙት ሆኖ ሳለ ችግሩን በሌሎች አካላት ላይ ለማላከክ መሞከር ተቀባይነት የሌለው እና ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት የማያስችል መሆኑን አብን ያምናል፡፡

3:- በተያያዘም በአድርግ አታድርግ ውዝግቦች የተነሳ በተፈጠሩ ግጭቶች ለእስር የተዳረጉ አካላትን በአፋጣኝ በመፍታት መንግስት ሰላም የማውረድ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አብን ይጠይቃል፡፡

4:- የአዲስ አበባ ከተማን የአፍሪካ እና የመላው አለም የዲፕሎሚሲ ማዕከልነትን የሚጻረር በብሄር ፖለቲካ ቅኝት የሚዘወር የአንድ ክልል አስተሳሰብ በኃይል ለመጫን የሚደረገው ጥረት እንዲቆም እና በመዲናችን የሚገኙ የዓለም አቀፋ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ አባላት ከደህንነት ስጋት ነጻ እንዲሆኑ እና የሀገሪቱ ገጽታ እንዳይጠለሽ መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ አብን ይጠይቃል፡፡

5:- በሥራ ላይ ባለው ሕገ-መንግስት እና በአዲስ አበባ ቻርተር ድንጋጌዎች በአዲስ አበባ ላይ የአንድን ክልል አርማ እና መዝሙር በግድ መጫንን የማይፈቅድ በመሆኑ የፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለችግሩ የማስተካከያ እርምጃ እዲወሰድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አብን ይጠይቃል፡፡

በመጨረሻም ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አዲስ አበባ ከተማን የቀውስ ማዕከል ለማድረግ እየተውተረተሩ ያሉት አካላት ምኞት በአጭር ይቀጭ ዘንድ ሰላማዊ ትግሉን እንዲቀጥል እና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድነቱን እንዲያጠናክር ለመላው የአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪውን ያስተላልፋል ሲል በመግለጫው አብራርቷል፡፡

Exit mobile version