Site icon ETHIO12.COM

መንግስት “የመቀለ ሕዝብ ደህንነት ያሳስበኛል” አለ፤ አስፈላጊ ያለውን እርምጃ እንደሚወስድ አስጥንቅቋል

“የኢትዮጵያ መንግሥት ለሕዝብና ለሀገር ሰላም ሲባል በሰላም ስምምነቱ የገባውን ቃል ሳይውል ሳያድርና ሳያንጣባጥብ በመፈጸም ላይ ይገኛል” ይላል መንግስት ያሳሰበውን የመቀለን ሕዝብ ደህንነት ጉዳይ ሲያነሳ። የመከላከያ ሃይል ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ዘረፋ ህዝቡን አማሯል። በዚህም የተነሳ የሕዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል አስፈላጊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ይህ ከማለቱ በፊት “ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል” ሲል በመንግስት በኩል የትሰራውን የስምምነቱ ፍሬዎች ሲዘረዘር በትህነግ በኩል ስለተፈጸመው ግን ያለው ነገር የለም።

“የመቀሌ ሕዝብ ደኅንነት ሊጠበቅ ይገባዋል” በሚል ርዕስ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባሰራጨው አጭር መግለጫ እንዳለው ” በፓትሮል የተደራጁ ዘራፊዎች የመቀለን ህዝብ እየዘረፉና እያሰቃዩ ነው”

ይህን የሽግግር ወቅት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም በአንዳንድ የመከላከያ ኃይላችን ባልደረሰባቸው የትግራይ አካባቢዎች ኅብረተሰቡን ሰላም የሚነሡ የተደራጁ ዘረፋዎች እየተካሄዱ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በተለይም በመቀሌ ከተማ በመንግስትና በንግድ ተቋማት ላይ በፓትሮል የታገዘ ከፍተኛ ዝርፊያ መኖሩን መረጃዎች እየጠቆሙ ነው። ሕዝቡም በከፍተኛ ምሬት ላይ መሆኑን በስልክና በሌሎችም መንገዶች እያሳወቀ ይገኛል።

በሰላም ስምምነቱ ምክንያት ከግጭት የሚያተርፉት ትርፍ የቀረባቸው አካላት ይሄንን እንደሚያደርጉ አያጠራጥርም። ህን ወንጀል የሚፈጽሙ ሁሉ ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ ሊገነዘቡ ይገባል።

መንግሥት በአካባቢው የሚገኙና የሕዝብ ደኅንነት የሚገዳቸው አካላት ከሕዝቡ ጎን ቆመው ወንጀለኞችን እንዲታገሉ ጥሪ እያደረገ የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ ያለበትን ኃላፊነት ለመፈጸም አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጥ ይወዳል።

ታኅሣሥ 8/2015 ዓ/ም

አዲስ አበባ

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Exit mobile version