Site icon ETHIO12.COM

ቦቆጣቦ – ዘረኝነትን በፍቅር የወጋች መንደር!

ቦቆጣቦ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን በቁጭ ንዑስ ቀበሌ የምትገኝ የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦችን መተሳሰብና መደጋገፍ በተግባር ያሳየች መንደር ናት። ይች መንደር ከቡሬ ከተማ 55 ኪሎሜትር ላይ ተገኛለች። ከቡሬ ጉትን እስከ ነቀምት በሚዘልቀው መንገድ ከአባይ ወንዝ ድልድይ መዳረሻ ላይ ትገኛለች። ቦቆጣቦ በማደግ ላይ የምትገኝ አነስተኛ መንደር ብትኾንም፣ መተሳሰብ እና መተባበር የነገሰባት መንደር ናት።

የዘር ፓለቲካ የወለደው ዳፋ ንጹኀን ዜጎችን ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል እየዳረገ በሚገኝበት በዚኽ ወቅት ቦቆጣቦ “እምቢ ለዘረኝነት” በማለት ኢትዮጵያን በፍቅርና መተሳሰብ በማጽናት ላይ ያለች መንደር ናት።

በቦቆጣቦ የአማራ እና ኦሮሞ ሕዝቦች ዘመንን በተሻገረ የማይናወጥ መተሳሰብ እና ፍቅር ይኖሩባታል። በዚች አነስተኛ መንደር የሚስተዋለው ብሔርና ማንነት ሳይቆጠር አንዱ ለአንዱ የመኖር ምስጢር በዘረኝነት በሽታ ለታመመ ሁሉ ትምሕርት ሰጭ ነው።

አቶ በላይ በቀለ የኦሮሞ ማንነት ያላቸው የቦቆጣቦ ነዋሪ ናቸው። ቦቆጣቦ የአማራ እና ኦሮሞ ሕዝቦች የዓባይ ወንዝ ሳይገድባቸው በጋራ ሠርተው፣ በጋራ ደስታና ችግርን ተካፍለው ይኖራሉ፣ በቅርብ ርቀት በሚገኘው ወለጋ ላይ የዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው በጥላቻ የሰከረ የዘር ፖለቲካ ልባቸውን ቢሰብረውም ተሳስበው የሚኖሩባትን ቦቆጣቦ ሲያስቡ ደግሞ ይጽናናሉ። አማራነት እና ኦሮሞነት የቦቆጣቦ ባለብዙ መልክነት እና ጌጥ ናቸው ሲሉም ይገልጻሉ። ቦቆጣቦ ሁለቱ ሕዝቦች በፍጹም ወንድማማችነት እና መተሳሰብ የሚኖሩባት ስለመኾኗም አቶ በቀለ ተናግረዋል።

ወደ ቡሬ እና ባሕር ዳር እንዲኹም ዓባይን ተሻግሮ ወደ ጉትን እና ነቀምት ምርት የሚጫንባት፣ ንግድ የሚካሄድባት የልማት መንደር ስለመኾኗም ይመሰክራሉ። ይኹን እንጅ በወለጋ አሸባሪው ሸኔ በንጹኀን ላይ በሚደርሰው ጥቃት ነቀምት ለመሻገር የሚያስችለው የዓባይ ወንዝ ድልድይ ዝግ መደረጉን ገልጸዋል። የመንገዱ መዘጋት ለሁለቱም ክልል ሕዝቦች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እና ማኅበራዊ መስተጋብር እንቅፋት መኾኑንም አቶ በላይ አስረድተዋል።

አቶ በላይ በወለጋ እየደረሰ ያለው የአማራዎች ሞትና እንግልት፤ አሸባሪው ሸኔን በሚታገሉ ኦሮሞዎች እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ዘላቂ እልባት አግኝቶ ሰላም እንዲሰፍን መንግሥት ቁርጠኛ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጠይቀዋል። ከባሕር ዳር እና ቡሬ አካባቢ ወደ ነቀምት ከፍተኛ የኾነ የእህል እና ሸቀጣሸቀጥ ጉዞ እንደነበር ያስታወሱት አቶ በላይ ሁለቱም ሕዝቦች ወደተለመደው የንግድ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ መንግሥት የአካባቢውን ሰላም አስጠብቆ መንገዱን ለትራፊክ ክፍት ማድረግ አለበት ነው ያሉት።

የፖለቲካ ነጋዴዎች የተለያየ ስም እየተሰጣቸው በወለጋ ውስጥ በአማራዎች ላይ የሚፈጽሙት ግድያ እና እንግልት ባስቸኳይ መቆም እንዳለበትም መልእክት አስተላልፈዋል።

አቶ ኑርልኝ ገላው የአማራ ማንነት ያላቸው በቁጭ ንዑስ ወረዳ ቦቆጣቦ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ከአቶ በላይ ጋር ኾነው የጋራ ሰላማቸውን ለመጠበቅ በዓባይ ድልድይ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ነው ያገኘናቸው። አቶ ኑርልኝ ልክ እንደ አቶ በላይ በቦቆጣቦ የሚኖሩ የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦች ለዘመናት ስለዘለቀው አንድነትና ፍቅር አንስተው አይጠግቡም። ነዋሪዎች በደስታም ኾነ በሐዘን ጊዜ የማይለያዩ፣ ለዘመናት የተጋመደ መስተጋብር እና ፍቅር ያለቸው መሆኑን ተናግረዋል። አማራው ወደ ነቀምት ኦሮሞው ወደ ቡሬ በመንቀሳቀስ ከፍተኛ የኾነ የንግድ ልውውጥ ሲያደርግ ቦቆጣቦ መገናኛ ድልድይ መኾኗንም ገልጸዋል።

አቶ ኑርልኝም የመንገዱ መዘጋት እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል። ከወለጋ በመፈናቀል ረጅም እና እንግልት የበዛበት የእግር ጉዞ አድርገው ወደ አማራ ክልል የሚገቡ ወገኖችን እየተቀበሉ እንደሚያሳርፉም ተናግረዋል። “ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ነው” ያሉት አቶ ኑርልኝ መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ በማስቀመጥ ዜጎችን ከግድያ እና እንግልት መጠበቅ አለበት ብለዋል።

የቦቆጣቦ ነዋሪዎች መተሳሰብ እና ፍቅር ወደ ወለጋ ተሻግሮ በኢትዮጵያም በዝቶ፣ የዜጎች ግድያ እና እንግልት በፍቅር በሻረ ብለን ተመኘን። ቦቆጣቦ ዘረኝነትን በፍቅር የወጋች የሀገር ተምሳሌት መንደር!።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው (አሚኮ)

Exit mobile version