“ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ጋር ያላትን ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ የማስቀመጫው ጊዜ አሁን ነው”

“የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያወጣው መረጃ በበጎ መልኩ የሚታይ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያወጣው መረጃ በበጎ መልኩ እንደሚያየው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላትን ትብብር በአዲስ መልክ እንደገና ለማደስ አበክራ እየሠራች እንደምትገኝም ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ካደረገው ስብስባ በኋላ ከትናንት በስቲያ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ዙሪያ የፕሬስ መግለጫ አውጥቷል።

ሚኒስቴሩ ምክር ቤቱ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ ላይ የተገኙ ውጤቶችን ጨምሮ ለሌሎች ጉዳዮች ዕውቅና መስጠቱን ገልጿል።

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላትን ትብብር በአዲስ መልክ እንደገና ለማደስ አበክራ እየሠራች እንደምትገኝና የምክር ቤቱ መግለጫም ይሄንኑ ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን አመልክቷል።

ሕብረቱ በዘላቂ ግብርናና የምግብ ዋስትና ላይ ያተኮረውን ዓመታዊ የባለብዙ ዘርፍ የድጋፍ ፕሮግራም በድጋሚ ለመጀመር ያሳየውን ዝግጁነት፣ አበዳሪ አገራት ባቋቋሙት የጋራ ማዕቀፍ ስር የሚከናወነው የኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ የድርድር ሂደት በአፋጣኝ እንዲቋጭ ያቀረበው ጥሪና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማረጋጊያና ማሻሻያ አጀንዳ እንዲደግፉ የሰጠው ጠንካራ ማበረታቻ መልካም የሚባል እንደሆነ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረትና ሌሎች ወዳጆቿ ጋር ያላትን ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ የማስቀመጫው ጊዜ አሁን ነው ብሏል ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ።

የኢትዮጵያ አጋሮች ከአገሪቷ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በአዲስ መልክ እያደሱ ይገኛል ያለው ሚኒስቴሩ ይህ እየሆነ ያለው ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ለማጽናት የተጀመረው ሂደት አስደማሚ ለውጦች በተመዘገቡበት፣የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች፣በግጭት የተጎዱ ማህበረሰቦችን መልሶ ማቋቋምና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ ውጤቶች እየተገኙ ባሉበት ወቅት መሆኑን ገልጿል።

ከአሚኮ

See also  የንብረት መሻሻጥና ማስተላለፍ አገልግሎት ዕግድ ተነሳ

Leave a Reply