Site icon ETHIO12.COM

የፌ.ቤ.ኮርፖሬሽን የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ግንባታ ለማከናወን ከኦቪድ ካምፓኒ ጋር ስምምነት ፈጸመ

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዘመናዊ ቴክሎጂን በመጠቀም በሁለት የግንባታ ሳይቶች የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን ለመገንባት ከኦቪድ ካምፓኒ ጋር ስምምነት መፈጸሙ ተገለጸ፡፡

ስምምነቱን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል እና የኦቪድ ካምፓኒ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ታደሠ ተፈራርመዋል፡፡ ግንባታውን ለማከናወን የአልሙኒየም ፎርምወርክ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፣ የሚክስድ አፓርትመንት ሕንጻዎቹ ግንባታ ቦሌ ኦሜዳድ እና ሾላ አካባቢ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የሾላ ሳይት B+G+12 የሆነ በለአራት ብሎክ ሚክስድ አፓርትመንት እንዲሁም ቦሌ አካባቢ የሚገነባው ኦሜዳድ ሳይት ደግሞ B+G+12 የሆነ ዘመናዊ ሚክስድ አፓርትመንት ሕንጻዎች እንደሆኑ የተገለጿል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ ከዚህ በፊት ከኦቪድ ካምፓኒ ጋር በ18 ወራት ውስጥ ግዙፍ የመኖሪያ መንደር እውን ማድረጉን አስታውሰው እንደአገር የአልሙኒየም ፎርምወርክ የግባንታ ቴክኖሎጂን ውጤታማነት ያስተዋወቀ ሥራ ነው።

ኮርፖሬሽኑ መንግስትና ሕዝብ የሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ እየተወጣ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ፣ ኮርፖሬሽኑ ከሚያካሂዳቸው ግዙፍ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎች በተጨማሪ በሌሎች በዓገርዓቀፍ ደረጃ በሚሰሩ መንግስታዊ የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክቶች ላይ ከኮንትራክተሮች በጋር በመስራትና በማማከር የግንባታ ቴክኖሎጂዎች እንዲሰፉ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በሾላ እና ኤሜዳድ ሳይቶች ከመኖሪያ ቤት በተጨማሪ የንግድ ቤቶችንም አካቶ የሚገነባ መሆኑንና ግንባታዎቹን ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደታሰበ አቶ ረሻድ ጠቅሰዋል፡፡

የኦቪድ ካምፓኒ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ታደሰ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ጠንካራ ፕሮጀክት አስተዳደርና አመራር ሥርዓት ያለው በመሆኑ የሳይቶችን ግንባታ በተያዘው ጊዜ ፣ጥራትና በጀት ለማካናወን እገዛ እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት፡፡

አያይዘውም ኦቪድ ካምፓኒ ያመጣውን የአልሙኒየም ፎርምወርክ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ውስጥ በገርጂ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ተግባራዊ ተደርጎ ውጤታማ እንዲሆን ድርሻ አለው ብለዋል።

ቴክኖሎጂው ውጤታማ የሚሆነው አስገንቢዎች ጠንካራ የፕሮጀክት አተስዳደር ሲኖራቸው እንደሆነም አቶ ዮናስ ተናግረዋል፡፡

ኦቪድ ካምፓኒ ሳይቶቹን በጥራትና በፍጥነት ገንብቶ እንደሚያስረክብ አረጋግጠዋል፡፡

በቀጣይም ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመሆን አዳዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ እንደሚሰራም ነው የጠቆሙት፡፡

ኮርፖሬሽኑ በዛሬው እለት ለማስገንባት ስምምነት የፈጸመባቸውን ጨምሮ የግንባታ ሳይቶቹ ቁጥር 12 የደረሱ መሆናቸውንና በስድስት የግንባታ ሳይቶች 23 ብሎክ ዘመናዊ አፓርትመንት ሕንጻዎችን ገንበቶ ማጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

ቀሪዎችም ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የማጠናቀቂያ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጠቅሶ ኢዜአ አስታውቋል።

Exit mobile version