Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ ስድስት የታገቱ የጅቡቲ ወታደሮችን ነጻ አስለቀቅች

ከወራት በፊት በሰሜናዊ ጅቡቲ ተጠልፈው የነበሩ 6 የጅቡቲ ወታደሮችን በድርድር ማስለቀቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከጅቡቲ መንግሥት በቀረበለት ይፋዊ ጥያቄ መሠረት ወታደሮቹን ለማስለቀቅ ከጥቅምት ወር መጨረሻ አንሥቶ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል አምባሳደር ፍስሐ ሻውል ገልጸዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት አምሳደር ፍስሐ፣ በሂደቱ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም የአፋር ክልል ፖሊስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ወታደሮቹን በማስለቀቁ ሂደት ያደረገችው ተሳትፎም ከጅቡቲ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር በፀጥታ እና ደህንነትም ዘርፍ የደገመችበት ነው ብለዋል።

በሂደቱ በተለይም የአፋር የሀገር ሽማግሌዎች እና ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስልቶች መጠቀም ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸውም ነው አምባሳደር ፍስሐ ሻውል የገለጹት። ሂደቱም በከፍተኛ ጥንቃቄ የተመራ ነበር ብለዋል። ወታደሮቹን የማስለቀቁም ሂደት ያለምንም ጉዳት ተጠናቅቆ ወታደሮቹ ወደ ጅቡቲ መሸኘታቸው ተገልጿል ሲል የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ዘግቧል።

Exit mobile version