Site icon ETHIO12.COM

የስኳር በሽታ ዓይነቶች

የስኳር በሽታ ዓይነቶች መልክቶች እና ማድረግ ያለብን ጥንቃቄ፡-ከመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ፡፡
የስኳር በሽታ የሚባለዉ በሰዉ ደም ዉስጥ የስኳር ወይም የጉሉኮስ መጠን ሲበዛ ማለትም /100-120ሚግ/ዲኤል/ እና ከዛ በላይ ሲሆን ነዉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዓለም አቀፍ ደረጃ 380 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በስኳር በሽታ ተይዘው ይገኛሉ። የዓለም ጤና ድርጅት እንደተነበየዉ በ2030 ይህ ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል ተብሎ ይገመታል፡፡

የስኳር በሽታ ሊከሰት የሚችለዉ
• በሰውነታችን ኢንሱልን በብቃት ሳይመረት ሲቀር ወይንም ፈፅሞ ኢንሱሊን ማምረት ሲያቆም
• ሰውነታችን የተመረተውን ኢንሱሊን በአግባቡ መጠቀም ሳይችል ሲቀር ወይም ሁለቱም ባንድ ላይ ሲከሰት ነው።

የስኳር ዓይነቶች አይነት አንድ እና አይነት ሁለት በመባል ይታወቃሉ፡፡

አይነት አንድ (Type 1)
አይነት አንድ የስኳር በሽታ በጣም ከባዱ የስኳር በሽታ አይነት ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተው በሕፃናት እና በጉርምስና (teenagers) ጊዜ ነው። ሆኖም ግን በሌላ የእድሜ ክልል ውስጥም ሊከሰት ይችላል። በዚህ በሽታ የተጠቁ ሰዎች በሰዉነታቸዉ ዉስጥ ኢንሱኒን ምክንያቱ ባልታዎቀ ምክንያት አይመረትም ፡፡

አይነት ሁለት (Type 2) የስኳር በሽታ
ሁለተኛው አይነት የስኳር በሽታ ብዙውን ጊዜ የሚያጠቃው ከ35 ዓመት በላይ ያሉ ጎልማሶችን ነው። በዚህ በሽታ የተጠቁ ህመምተኞች ለሰውነታቸው የሚያስፈልገውን ኢንሱሊን በከፊል ማምረት የሚችሉ ሲሆን ችግሩ ብዙውን ጊዜ የኢንሱሊኑ መጠን በቂ ሆኖ አለመገኘቱ ነው።
ለስኳር በሽታ ሊያጋልጡ የሚችሉ ምክንያቶች
• የሰዉነት ክብደት መጨመር /ከልክ በላይ መወፈር
• ሰዉነት እንቅስቃሴ አለማድረግ (ስፖርት) አለመስራት
• ስጋ እና የእንስሳት ተዋዕፆን አዘዉተሮ መመገብ
• አልኮል መጠጦችን አዘዉትሮ መጠጣት
• የተለያዩ ሱሶችን እና አደንዛዥ ዕፆችን መጠቀም
• ጣፋጭ ነገሮችን አዘዉትሮ መጠቀም
• ቀደም ሲል በቤተሰብ ወይንም በዘር የስኳር በሽታ የተጠቃ ካለ

የስኳር በሽታ ምልክቶች
• ሽንት ቶሎ ቶሎ መሽናት • ቶሎ ቶሎ ዉሃ መጠማት
• ቶሎ ቶሎ መራብ • የሰዉነት ክብደት መጨመር እና መቀነስ
• በሰዉነት ላይ የሚያጋጥም ቁስል ቶሎ አለመዳን
• ስሜት አልባ መሆን • የአይናችን የእይታ መጠን መቀነስ (ብዥ ማለት)
የስኳር በሽታ የሚያስከትለዉ ጉዳት
• ድንገት የሚከሰት ህልፈተ ህይወት • ኩላሊት መድከም
• የእይታ ችግር ብሎም የአይን እይታ ማጣት
• የቆስል አለመዳን ብሎም አካል እስከመቆረጥ መድረስ

የስኳር በሽታ መከላከያ መንገዶች
• ከላይ የተጠቀሱትን ለስኳር በሽታ ሊያጋልጡ የሚችሉ ነገሮችን ታሳቢ በማድረግ የአኗኗር ዘይቤን ጤናማ ማድረግ
• ማንኛዉም ሰዉ እድሜዉ ከአርባ ዓመት በላይ ከሆነ በየጊዜው ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ መታየት (check up)
• የስኳር መጠን በደማችን ከታየ ጤና ሙያተኛ የሚሰጠንን መድሃኒት እና ምክር በሚገባ መጠቀም፡፡

ከመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ጤና ማበልፀግ በሽታ መከላከል መምሪያ
ሌ/ኮ ማናህሎሽ ታደለ

የኢፌዴሪ መከላከያ ታህሣሥ 13 ቀን 2015 ዓ.ም

Exit mobile version