Site icon ETHIO12.COM

የአገርና የመንግስትን ወድ መረጃ ለመጠበቅና ተጠያቂነትን ለማስፈን አዋጅ ተዘጋጀ

በመንግስት ሚስጥራዊ መረጃ ምደባና ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ተካሄደ

የመንግስት ሚስጥራዊ መረጃ ምደባና ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ እና የቴክኖሎጂ ዝግጁነት ላይ ውይይት ተካሄደ።

በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የካቢኔ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ተስፋዬ ዳባ እንዳሉት በመንግሥት ሚስጥራዊ መረጃ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍና የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንደ ሃገር የመንግስት ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለመመደብና ለመጠበቅ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ በማውጣት ረገድ የዘገየን ቢሆንም የሌሎች ሃገራትን መልካም ተሞክሮ በመቀመር የተሻለ የመንግስት መረጃ ጥበቃ አዋጅ ማውጣትና ማስፈጸም እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ አዋጁ ትላልቅ የሃገር መረጃዎችን ሚስጥራዊነት ጠብቆ እና ህዝብም ደግሞ ማግኘት ያለበትን የመረጃ ሚዛን ጠብቆ ለማስኬድ የሚያስችል ስርዓት ለመፍጠር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ መፍጠርን አላማ ያደረገ ነው ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው የመንግስት መረጃዎችን ከመጠበቅ አኳያ ሁሉን አቀፍ ስርአት መዘርጋት ያስፈላግል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ከሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት ባሻገር፣ ሃገር በቀል የቴክኖሎጂ ምርቶችን ማልማትና መጠቀም፣ ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአሰራር ስርአት መዘርጋት እንዲሁም የሕብረተሰቡንና የተቋማትን ንቃተ ሕሊና ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ኢመደአ የመንግስት መረጃዎች ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ሃገር በቀል የቴክኖሎጂ ምርቶችን በማልማት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው የአዋጁ መውጣት ሃገራዊ ቁልፍ መረጃዎችን በተጠናከረና በተቀናጀ መልኩ ለመጠበቅ ፋይዳው ከፍ ያለው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው መረጃ የአንድ ሃገር ቁልፍ ሃብት እንደመሆኑ መጠን ተገቢው ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል ብለዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ም/ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ በበኩላቸው የውውይት መድረኩን አስፈላጊነት አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ሚስጥራዊ የመንግስት መረጃዎችን በተደራጀና ወጥ በሆነ መልኩ ለማስተዳደር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ በሃገር ደህንነት ላይ ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮት ሲፈጥር ቆይቷል ብለዋል፡፡

በተለይም ባለፉት ሁለት አመታት በሃገራችን የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ተጋላጭነት መከሰቱ ለአዋጁ መዘጋጀት እንደ ገፊ ምክንያት የሚወሰድ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ም/ዳይሬክተር ጀነራሉ አያይዘው እንደገለጹትም፤ በጸጥታ መዋቅርም ሆነ በመንግስት የመረጃ ሚስጥራዊነት ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን ሚስጥራዊ የመረጃ ምደባ እና ጥበቃ ማድረግ ወሳኝ ነው።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ በበኩላቸው ሚስጥራዊ የመንግስት መረጃዎችን ለጥቃት ተጋላጭ ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል አንዱ የቴክኖሎጂ ክፍተት እንደሆነ ጠቅሰው ይህንን ለመቅረፍ ኢመደአ ደህንነታቸው የተረጋገጠ ሃገር በቀል የኮሚዩኒኬሽን ፕላትፎርሞችን ማበልጽጉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ሁሉን አቀፍ የሆነ (ቴክኖሎጂ፣ የአስራር ሥርአት፣ የሕግ ማዕቀፍ፣ እና የሰው ሃይል) ሥርአት በመዘርጋት ሃገራዊ ቁልፍ መረጃዎችን ከጥቃት መከላከልና የሃገርን ደህንነት ማስጠበቅ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ረቂቅ አዋጁን ለማዳበር የሚያስችሉ የተለያዩ ግብአቶች ከተሳታፊዎች የቀረቡ ሲሆን እነዚህን በማካተት በአጭር ጊዜ ውስጥ አዋጁ ወጥቶ ሥራ ላይ እንደሚውል በመድረኩ ላይ መገለጹን ከአስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

Ena

Exit mobile version