Site icon ETHIO12.COM

የባህር በር የሌላት ሀገር ለምን የባህር ኃይል አስፈለጋት?

ይህ ጥያቄ በአንዳንድ አካላት ዘንድ እንዴት ኖራት ተብሎ ይነሳል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ሀገራችን አሁን ላይ እያደራጀችውና እየገነባችው ካለው የባህር ኃይል ጋር ተያይዞ በየትኛው የባህር በር ላይ ዘብ ሊቆም ነው የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ሀሳቦችን ያነሳሉ፡፡

ይህ በሀገር ውስጥ ባሉ ግለሰቦችም ይሁን በሌሎች ሀገራት ጭምር የሚነሳው ጥያቄ እንደየጠያቂዎቹ እሳቤ እና እይታ ሊለያይ ቢችልም አሁን ካለው ዓለም-አቀፋዊ አህጉራዊ ቀጠናዊ እና ሀገርዊ ሁኔታዎች ጋር ሲታይ ግን የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የባህር ኃይል እንዲመሰርቱ ግድ የሚሆኑባቸው ሁኔታዎች እንዲህ በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ወደማብራሪያዉ ከማለፋችን በፊት ስለ ቀድሞው ባህር ኃይላችን ጥቂት እናንሳ፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በንጉሱ ዘመን በ1948 ዓ/ም ሲመሰረት ከሶስቱ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት አንዱ ሆኖ ሙሉ በሙሉ ራሱን የቻለ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመ ሲሆን ዋነኛ ተልዕኮውም የቀይ ባህርን የባህር ዳርቻ ለመጠበቅ ነበር፡፡

በንጉሠ ነገስሥቱ ዘመን የነበሩት የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አባላት በወቅቱ ከነበሩ ምርጥ የዓለማችን የባህር ኃይል አባላት ጋር ተወዳዳሪና ብቁ ለመሆን የሚያስችላቸውን ስልጠናም ወስደዋል፡፡ በተለይም በመኮንን ደረጃ በባህር ኃይል ኮሚሽን እና በሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በምፅዋ በተቋቋመው ያልተማከለ የመኮነንነት ትምህርት ቤት እና በአሰብ የተቋቋሙት ማሰልጠኛዎች ለማሳያነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ለዓመታት የተመሰረተበትን ዓላማ በብቃት ሲወጣ የነበረው ስመጥሩ የኢትዮጵያ ባር ኃይል 1983 ዓ/ም በነበረው ለውጥና ኤርትራ ራሷን ችላ ሉዓላዊ ሀገር ስትሆን የባህር ኃይልሙ በዛው ከሰመ፡፡ የሆነ ሆኖ የዛሬ አራት ዓመት ዳግም የኢትዮጵያ ባህር ኃይልን የመመስረቱ ስራ ተጀመረ፡፡ ለመሆኑ ባህር ኃይልን ዳግም መመስረት ለምን አስፈለገ? ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ስለአስፈላጊነቱ ያሉትን እናስከትል፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን የረጅም ጊዜ ታሪክ ባለቤት ከመሆኗም በላይ ቅኝ ግዛትን የማታውቅ ታፍራና ተከብራ የኖረች በሰራዊት አመሰራረት ረገድም ዘመናዊ የባህር ኃይልን ቀድማ ያቋቋመች የራሷን ግዛት ከወራሪዎች በጀግንነት ጠብቃ ያቆየች ታላቅ ስለመሆኗ ያወሱት ሬር አድሚራል ክንዱ ባለፉት አራት ዓመታት እንደቀድሞው ሁሉ ያንን ገናና ስም ያለውን የባህር ኃይል መልሶ ለመገንባት እንደ ሀገር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የባህር በር የሌላት ሀገር የባህር ኃይል ለምን አስፈለጋት የሚለው ጥያቄ መነሳት ካለበት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለምአቀፍ ደረጃ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ነገር ግን ባህር ኃይል አቋቁመው ያሉትን ሀገራት በምሳሌነት መጥቀሱ አስፈላጊ መሆኑን በቀዳሚነት አንስተውልናል፡፡ ፓራጓይ አዘርባጃን እና ቦሊቪያ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ናቸው፡፡ ነገር ግን በቂ የባህር ኃይል አላቸው፡፡

የየሀገራቱ ፍላጎት እንዳሉበት ሁኔታና ቀጠናዊ ትስስር ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ዋናው ማጠንጠኛ ግን ጥቅምን መሰረት ያደረገ ነው ይላሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ዘጠና ከመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ የሚሳለጠው በውሃ ላይ በሚደረግ ጉዞ መሆኑን በማሳያነት ያወሱት ሬር አድሚራል ክንዱ በተለይም እ.ኤ.አ ከ2008 እስከ 2010 በምስራቅ አፍሪካ የነበረውን የባህር ላይ ውንብድና አስቸጋሪነት አውስተዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነት የሀገራትን ጥቅም የሚጎዱ ውንብድናዎችን ለመከላከል የባህር ኃይል ወሳኝ ነው ይላሉ፡፡ ምክንያቱም አሁን ባለው ዓለማቀፍ ሁኔታ በአንድ ቀጠና የሚፈጠር ችግር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ዓለማቀፋዊ ችግር ይሆናልና፡፡

በሌላ ረገድ እንደ ምክንያትነት ያነሱት ነጥብ ኢትዮጰያ ያሏትን የንግድ መርከቦችና ለሀገር ያላቸውን ፋይዳ ነው፡፡ የአስራ አንድ የንግድ መርከቦች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ባንዴራዋን እያውለበለቡ ከአህጉር አህጉር የሚዘዋወሩት መርከቦቿ ደህንነት ተጠብቆ በሰላማዊ ሁኔታ ስራቸውን ለማከናወን አስተማማኝ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ለዚህም በዘርፉ የሰለጠነ የባህር ኃይል መኖር ያስፈልጋል፡፡

በተለይም በዚህ ሉዓላዊ ዘመን ላይ በብዙ ሺህ ማይል ከሚርቋቸው ሀገራት ላይ አህጉራትን አቋርጠው በመምጣት የባህር ወደብ ጭምር በመከራየት የባህር ኃይላቸውን አስፍረው ይገኛሉ፡፡ ታዲያ ከባህር ከ60 ማይል ያነሰ ርቀት ላይ ለምትገኘው ኢትዮጵያ የባህር ኃይል መገንባቱ ለምን የሚለውን ጥያቄ ለሚያነሱት ሁሉ ምላሽ መስጠት ባይጠበቅብንም በዋነኝነት ግን ከዓለማችን አምስት ስትራተጂክ ቦታዎች መካከል አንዱ በሆነው የምስራቅ አፍሪካ የምተገኘው ኢትዮጵያ ጠንካራ የጦር ሰራዊት ግንባታ ልትግኝ ግን የግድ ይላታል እኛም ይህንኑ ግብ ለማሳካት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ በስተመጨረሻም የባህር ኃይልን በተቀመጡት የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅዶቻችን መሰረት ተገቢውን ስራ በማከናወን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለንን መልካም ጉርብትና በማጠናከርና በትብብር የመስራት ባህላችንን በማዳበር የኢትዮጵያን ባህር ኃይል ገናናነት እንመልሳለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አቢዮት ዋሚ

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት

Exit mobile version