Site icon ETHIO12.COM

የኑዛዜ አይነቶችና የኑዛዜ ማረጋገጫ

መግቢያ

በኢትዮጵያ የውርስ ህግ ሰው ህይወቱ ካለፈ በኋላ በህይወት ዘመኑ ያፈራቸው ንብረቶቹን ለወዳጅ ዘመዶቹ እንዲከፋፈል የሚያደርግበት ሁለት አይነት መንገዶች አሉ፡፡ እነሱም ያለኑዛዜ የሚደረግ ውርስ እና በኑዛዜ የሚደረግ ውርስ ናቸው፡፡ በሁለቱም ዘዴዎች የሚደረግ የንብረት ማስተላለፍ ሂደት በፍትሐ ብሔር ህግ የሚገዛ ሲሆን ለውርሱ ተፈፃሚነት ህጉ ያስቀመጣቸው መስፈርቶች መሟላት ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ አጭር ፅሁፍ የኑዛዜ አይነቶች እና የኑዛዜ ማረጋገጫ በዝርዝር ይዳሰሳሉ፡፡

የኑዛዜ አይነቶች

በኢትዮጵያ ህግ 3 የኑዛዜ ዓይነቶች አሉ፡፡ ሁሉም የኑዛዜ አይነቶች መከትል ያለባቸው ፎርማሊቲዎች ወይም ቅድመ ሁኔታዎች በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐ ብሔር ህጋችን ውስጥ በዝርዝር የተቀመጡ ሲሆን መስፈርቶቹ ያልተሟሉ እንደሆነ ኑዛዜው በህግ ፊት ውድቅ (ፈራሽ) ይሆናል፡፡ ህጉ የመስፈርቶቹን መሟላት በተመለከተ ጥብቅ (strict) ነው፡፡ ይህም የሆነበት ዋና ምክንያት የኑዛዜ ቃል በሚፈፀምበት ወቅት ተናዛዡ በህይወት ስለማይኖር ትክክለኛ ሀሳቡን ማወቅ የሚቻለው ትቶት ከሄደው የኑዛዜ ሰነድ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ሰነድ ደግሞ ለአፈፃፀም እንዲያመች መስፈርቶቹን በሙሉ ግልፅ በሆነ ሁኔታ መከተል አለበት፡፡ በፍ/ህ/አ 880 ስር እንደተደነገገው 3ቱ የኑዛዜ አይነቶች

  1. በግልፅ የሚደረግ ኑዛዜ (public will)
  2. በተናዛዡ ፅሁፍ የሚደረግ ኑዛዜ (holographic will)
  3. በቃል የሚደረግ ኑዛዜ (oral will) ናቸው

• በግልፅ የሚደረግ ኑዛዜ ( የፍ/ብ/ህገ/ቁጥር 881-883)

በግልፅ የሚደረግ ኑዛዜ ተናዛዡ እየተናገረ ሌላ ሰው የሚፅፈው ወይም ተናዛዡ ራሱ የሚፅፈው የኑዛዜ አይነት ነው፡፡ ይህ ኑዛዜ በተናዛዡ ወይም በሌላ ሰው ከተፃፈ በኃላ ተናዛዡ እና ምስክሮች ባሉበት መነበብ አለበት፡፡ በግልፅ የሚደረግ ኑዛዜ ተቀባይነት እንዲኖረው ተናዛዡና ምስክሮች ባሉበት መነበቡ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህ መስፈርት (formality) መሟላቱ በኑዛዜው ላይ መስፈር አለበት፡፡ ይኸውም በኑዛዜው ላይ “ይህ ኑዛዜ ተናዛዡ እና ምስከሮች ባሉበት ተነቧል” ተብሎ መገለጽ አለበት፡፡ በግልፅ በሚደረግ ኑዛዜ ላይ የምስክሮች ብዛት 4(አራት) መሆን ሲኖርበት አራቱም ምስክሮች ኑዛዜው ተነቦላቸው በኑዛዜው ላይ ፊርማቸውን ወዲያውኑ ማስፈር አለባቸው፡፡ በተጨማሪም በኑዛዜው ላይ ኑዛዜው የተደረገበት ቀን ማለትም ቀን፣ ወር፣ ዓመተ ምህረት መፃፍ አለበት፡፡

የምስክሮችን ብዛት በተመለከተ በግልፅ ለሚደረግ ኑዛዜ ከምስክሮቹ መካከል አንዱ ዳኛ ወይም ውል ለማዋዋል ሥልጣን የተሰጠው ሰው ሆኖ ኑዛዜውም የተደረገው ይህ ዳኛ ወይም ለማዋዋል ሥልጣን የተሰጠው ሰው ሥራቸውን በሚያካሄዱበት ክፍል ውስጥ የሆነ እንደሆነ ለኑዛዜው ዋጋ ማግኘት ሁለት ምስክሮች ብቻ በቂ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ በግልፅ የሚደረግ ኑዛዜ የሚከተሉትን ፎርማሊቲዎች መከተል አለበት፡፡

 በተናዛዡ በራሱ ወይም እሱ እየተናገረ በሌላ ሰው ሊፃፍ ይችላል
 ተናዘዡና አራት ምስክሮች ባሉበት መነበብ አለበት
 በኑዛዜው ላይ ተናዛዡና ምስክሮቹ ባሉበት መነበቡ በግልፅ መፃፍ አለበት
 ኑዛዜው የተደረገበት ቀን፣ ወር እና ዓ.ም መፃፍ አለበት
 አራት ምስክሮች መኖር አለባቸው፣
 ተናዛዡና ምስክሮች ኑዛዜው እንደ ተነበበላቸው ወዲያውኑ ፊርማቸውን ወይም የጣት አሻራቸውን ማሳረፍ አለባቸው
 በግልፅ የሚደረግ ኑዛዜ ምስክሮች አካለመጠንን የደረሱ (18 ዓመት የሞላቸው) ወይም በህግ ያልተከለከሉ መሆን አለባቸው
 ምስክሮች ኑዛዜው የተፃፈበትን ቋንቋ ለማወቅና የተፃፈውን ለመስማት ወይም ለማንበብ ራሳቸው ችሎታ ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡

እነዚህ ከላይ የተመለከቱት መስፈርቶች ካልተሟሉ ኑዛዜው ፈራሽ ይሆናል፡፡ ፍርድ ቤቶችም የኑዛዜ ቃልን ለማስፈፀም መሟላት ያለባቸው መስፈርቶችን በጥብቅ የሚቆጣጠሩ ሲሆን መስፈርቶቹ ካልተሟሉ ኑዛዜውን ውድቅ ያደርጉታል፡፡

• በተናዛዡ ፅሁፍ የሚደረግ ኑዛዜ (የፍ/ብ/ህገ/ቁጥር 883-891)

በተናዛዡ ፅሁፍ የሚደርግ ኑዛዜ ሙሉ በሙሉ በተናዛዡ የሚፃፍ የኑዛዜ አይነት ነው፡፡ ይህን የኑዛዜ አይነት የሚያደርገው የተማረ ወይም ኑዛዜው የሚፃፍበትን ቋንቋ መፃፍና ማንበብ በሚችል ሰው ሲሆን የምስክሮችን መኖር የሚፈልግ አይደለም፡፡ በተናዛዡ ፅሁፍ የሚደረግ ኑዛዜ በተናዛዡ የእጅ ፅሁፍ ወይም በማሽን (በኮምፒዩተር) ሊፃፍ ይችላል፡፡ ተናዛዡ ኑዛዜውን በኮምፒዩተር የሚፅፈው ከሆነ በእያንዳንዱ ገፅ ላይ እራሱ ስለመፃፉ በእጅ ፅሁፉ ማመልከት አለበት፡፡ ይህም ኑዛዜውን ያደረገው ተናዛዡ እንደሆነ ለማረጋገጥ ይረዳል፡፡ ኑዛዜው በማሽንም ሆነ በእጅ ቢፃፍ ተናዛዡ በእንዳንዱ ገፅ ላይ ቀን ፅፎ ፊርማውን ማስፈር ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም በኑዛዜ ሰነድ ላይ ተናዛዡ ይህ ሰነድ “ኑዛዜ” ነው በማለት በግልፅ መግለፅ አለበት፡፡ እነዚህ መስፈርቶች ካልተሟሉ ኑዛዜው ፈራሽ ነው፡፡ በተጨማሪ በተናዛዡ ፅህፈት የሚደረግ ኑዛዜ ኑዛዜው በተደረገ በሰባት(7) ዓመት ውስጥ ውል ለማዋዋል ስልጣን በተሰጠው ሰው ወይም ፍርድ መዝገብ ቤት መቀመጥ አለበት፡፡

በአጠቃላይ በተናዛዡ ፅሁፍ የሚደረግ ኑዛዜ በህግ ፊት ተቀባይነት እንዲያገኝ እና ተፈፃሚነት እንዲኖረው የሚከተሉት መስፈርቶች በሙሉ መሟላት አለባቸው፡፡

 ሙሉ ለሙሉ በተናዛዡ መፃፍ አለበት
 በኑዛዜው ላይ በግልፅ “ይህ ሰነድ የኑዛዜ ሰነድ ነው “ተብሎ መገለፅ አለበት
 በተናዛዡ በአያንዳንዱ ገፅ ላይ ቀን እና ፊርማ መስፈር አለበት
 ኑዛዜው በተደረገ በሰባት አመት ውስጥ ውል ለማዋዋል ስልጣን በተሰጠው አካል ዘንድ መቀመጥ አለበት፣( የፍ/ብ/ህገ/ቁጥር 903)
 ተናዛዡ ግልፅ በሆነ ፊርማው ካላፀደቃቸው በስተቀር የተናዛዡን ፈቃድ ለመለወጥ የሚችል ፍቀት፣ ስርዝ ወይም ድልዝ ያለባቸው ኑዛዜዎች ፈራሽ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ከላይ ከተገለፁት መስፈርቶች ውስጥ አንዱ ወይም ከአንድ በላይ ካልተሟላ ኑዛዜው ፈራሽ ይሆናል ወይም ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ ነገር ግን ኑዛዜ ፈራሽ ሆነ ማለት ወራሾች ንብረት አያገኙም ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ውርሱ በቁጥር 842 እና ተከታዮቹ መሰረተ ሳይናዘዝ የሞተ ሰው ውርስ በሚተላለፍበት ሂደት የሚተላለፍ ይሆናል፡፡

የቃል ኑዛዜ (የፍ/ብ/ህገ/ቁጥር 892-894)

የቃል ኑዛዜ ማለት አንድ ሰው የሞቱ መቃረብ ተሰምቶት የመጨረሻ የፍቃድ ቃሎቹን ለሁለት ምስክሮች የሚሰጥበት የኑዛዜ አይነት ነው፡፡ ከፍ/ህ/ ቁጥር 892 እንደምንረዳው የቃል ኑዛዜ በመደበኛ ሁኔታ (under normal circumstances) የሚደረግ አይደለም፡፡ ተናዛዡ ይህን የኑዛዜ አይነት የሚያደርገው በቅርብ ጊዜ እሞታለው ብሎ ሲያስብ ለምሳሌ አደጋ ደርሶበት ፅኑ ህመም ውስጥ ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ ባለጊዜ ሌሎቹን የኑዛዜ አይነቶች ማለትም በግልፅ የሚደረግ ኑዛዜን ወይም በተናዛዡ ፅሁፍ የሚደረግ ኑዛዜን ለማድረግ ሁኔታዎች አይፈቅዱለትም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም በቃል የሚደረግ ኑዛዜ ላይ ተናዛዡ የሚናዘዘው በተገደበ ሁኔታ (restricted testamentary disposition) ይሆናል፡፡ በዚህ የኑዛዜ አይነት ተናዛዡ ሙሉ ፍላጎቱን ለማንፀባረቅ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ህጉ ገደቦችን አስቀምጧል፡፡

በፍ/ሕ/ቁጥር 893 መሰረት አንድ ሰው የቃል ኑዛዜ ማድረግ የሚችለው በተለይ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ነው፡፡

 የቀብሩን ሥነ-ሥርዓት የሚመለከቱትን ትዕዛዞች ለመስጠት
 እያንዳንዱ ውርስ ከአምስት መቶ የኢትዮጵያ ብር የማይበልጥ የኑዛዜ ስጦታ ለማድረግ፣
 አካለ መጠን ላላደረሱ ልጆቹ አስተዳዳሪን ወይም ሞግዚትን የሚመለከቱ ውሳኔዎችን ለመስጠት ነው፡፡

በቃል የሚደረግ ኑዛዜ ውስጥ ከብር አምስት መቶ በላይ ኑዛዜ ተደርጎ ከሆነ ከአምስት መቶ ብር በላይ ያለው ተቀናሽ ይሆናል፡፡ በቃል የተደረገ ኑዛዜ ከተደረገበት ከሶስት ወር በኋላ ተናዛዡ በህይወት የቆየ እንደሆነ ኑዛዜው ተፈፃሚ አይሆንም ወይም ፈራሽ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ተናዛዡ ያንያህል ጊዜ ሳይሞት ከቆየ በግልጽ የሚደረግ ኑዛዜን ወይም በተናዛዡ ፅሁፍ የሚደረግ ኑዛዜን ለማድረግ እድል አለው ተብሎ ይገመታል፡፡

በሌላ በኩል ብዙ ኑዛዜዎች ካሉ አብሮ ተፈፃሚ ሊሆኑ በሚችሉበት መጠን ልዩ ልዩ ኑዛዜዎች አብረው ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን የሁለት ኑዛዜዎች ቃላት ሁለቱም ሊፈፀሙ ያልቻሉ ወይም የተቃረኑ እንደሆነ በኋላ የተደረገው ኑዛዜ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡

በአጠቃላይ ንብረቱን በኑዛዜ ማስተላለፍ የሚፈልግ ሰው ሶስቱን የኑዛዜ አይነቶች ፎርማሊቲያቸውን በሟሟላት እንደየሁኔታው ሊጠቀምባቸው ይችላል፡፡ ኑዛዜ አድራጊው የኑዛዜ ቃላት ተፈፃሚነት እንዲያገኙ በህጉ የተቀመጡትን መስፈርቶች በጥንቃቄ መከተል አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ኑዛዜው ውድቅ ስለሚሆን የተናዛዡ ፍላጎት ተፈፃሚ አይሆንም ማለት ነው፡፡

 የኑዛዜ ማስረጃ ወይም ማረጋገጫ

በኑዛዜው የሰፈረውን ቃልና ኑዛዜው መኖሩን ማስረዳት ያለበት በዚህ ኑዛዜ ተጠቃሚ ነኝ የሚለው ሰው ነው፡፡ በግልፅ የሚደረግ ኑዛዜ ወይም በተናዛዡ ፅሁፍ የተደረገ ኑዛዜ መኖር የሚረጋገጠው የኑዛዜውን ፅሁፍ ዋናውን በማቅረብ ወይም ለማዋውል ስልጣን በተሰጠው ሰው ዘንድ ወይም ፍርድ መዝገብ ቤት ሹም ተክክለኛ ሆኖ የተመሰከረ አንድ ግልባጭ በማቅረብ ነው፡፡ ኑዛዜዎቹን ለማስፈፀም በማናቸውም ሌላ መንገድ ለማስረዳት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በጥፋት ወይም በቸልተኝነት ኑዛዜው እንዲጠፋ ካደረገ ሰው የጉዳት ኪሳራ ለማግኘት ከሆነ በማናቸውም አይነት መንገድ ኑዛዜዎችን ማስረዳት ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ በአንድ ኑዛዜ ተጠቃሚ ነኝ የሚል ሰው ሁለት ነገሮችን በመሰረታዊነት ማስረዳት ያለበት ሲሆን እነሱም በተናዛዡ የተደረገውን ኑዛዜ በማቅረብ የኑዛዜን መኖር እና የኑዛዜውን ይዘት በማስረዳት ማለትም እሱ የኑዛዜው ተጠቃሚ (beneficiary) መሆኑን ማስረዳት ናቸው፡፡

በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልተጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

Exit mobile version